>

የወሎ ሕዝብ አሁናዊ ሁኔታ.. !!! (ወንድወሰን ተክሉ)

የወሎ ሕዝብ አሁናዊ ሁኔታ.. !!!

ወንድወሰን ተክሉ

ሕዝባችን በወሎ ሰማይ ስር የተጋፈጠው የኑሮ ውድነት፣አጠቃላይ ውድመትና አቅጣጫውን የሳተው የዘመቻ መምሪያ፦
*** ***
፠ የወሎ ሕዝብ አሁናዊ ሁኔታ
 ከትራንስፖርት አገልግሎት እንጀምር ከደሴ ራያ ቆቦ ትራንስፖርት 2000 ብር፣ ከደሴ ወልድያ 1500 ብር፤ ከደሴ መርሳ 1200 ብር የሚከፈልባቸው ሆኗል።
ወደ የፍጆታ እቃዎች ስናመራ  ሃያ ሊትር ነዳጅ 7000 ብር፤ ቤንዚን በሊትር 300 ብር፤ ጋዝ በሊትር 250 ብር፤ አንድ ሻማ ትልቁ 25 ብር፤ አንድ ፍሬ የባትሪ ድንጋይ 83 ብር፤ አንድ ለምለም እንጀራ 45 ብር፤ ክርቢት 60 ብር ፤ 50ኪሎ ጤፍ ማስፈጫ 500 ብር ሆኖ ይህንንም አገልግሎት ለማግኘት  የወረፋው ብዛት ቀናትን የሚያሳድር ሲሆን እንደዚያም ተሆኖ ሳይፈጭ ሊመለስም ይችላል።
በአጠቃላይ አገልግሎት ውሃ ፣መብራት፣የስልክ፣የባንክና መሰል አገልግሎቶች በሙሉ ፈጽሞ የለም።
የተፈጸመውና ዛሬም እየተፈጸመ ያለው  ጥቃት እጅግ ዘርፈ ብዙ የሆነ  በስነልቦና ፤ በኢኮኖሚ ፤ በፖለቲካና በጠቅላላው በአማራዊነት ህልውና ላይ ያነጣጠረ ጦርነት ነው።
ባለፈው ሳምንት የአማራ ክልል ኢኮኖሚና ልማት ቢሮ ባወጣው መግለጫ በወያኔ ተወርረው በተለቀቁ 46 ወረዳዎች ውስጥ  ብቻ በተደረገ ጥናት ከ280ቢሊዮን በላይ ብር ንብረት መውደሙን አሳውቌል። ይህ እንግዲህ በጦርነቱ የተሰዋውን እና ዛሬም እየተሰዋ ያለውን የሰው ኋይል ብዛት ሳይጠቅስ የተገለጸ ውሱን ክፍል ብቻ የሚገልጽ ነው።
በዚህ ጦርነት አማራው ይንንን ዓይነቱን አስከፊ ዋጋ እንዲከፍል የተደረገውና ዛሬም እየከፈለ ያለው በጠላታችንና በወራሪው የወያኔ ሰራዊት ኋይልና ጥንካሬ ሳይሆን በራሳችን በኦህዴድ/ብ አዴን ብልጽግና ተብዬው የጨነገፈ መንግስት ሆን ብሎ የአማራን ሕዝብ በኢኮኖሚ በሰው ኋይልና በመሰረተ ልማት ለማድቀቅ በወሰደው መሰሪያዊ አመራር ምክንያት የመጣብን መከራ ሲሆን ለዚህ አስከፊ መከራ ተግባራዊነት የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው ባሕርዳር ላይ ተጎልቶ የጠላትን ሴራ እያስፈጸመ ያለው የብአዴን/ብልጽግና ቡድን መሆኑን አስረግጠን መግለጽና ማሳወቅ እንወዳለን።
፠ እንዴት ነው እዚህ ደረጃ ላይ የደረስነው???
እያንዳንዱ አማራ ብቻ ሳይሆን መላው ኢትዮጲያዊ የሆነ ሁሉ ለምንድነው ይህ ሁሉ ውድመትና ብሎም ስቃይ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ላይ በአማራ፣በአፋርና ብሎም በትግራይ ሊደርስና ሊፈጸም የቻለው እያለ እራሱን በመጠየቅና በማሰለሳል እንዲያስብና እራሱንም እንዲጠይቅ ይገባል።
ከላይ በወሎ ያለውን አሁናዊ ሁኔታን እና በ46 የተለቀቁ ወረዳዎች ውስጥ የደረሰውን የውድመት መጠንን ስንመለከት ይህንኑ ሁኔታ በመላው የሰሜን ጎንደር፣አፋርና ብሎም በትግራይ ያለውን ሁኔታ በንፅጽሮሽ እንድንመለከትና ብሎም እንድናስብ ሊያደርገን ይገባልና ለምን እና እንዴት ሆኖ ነው ይህ ሁሉ ውድመትና እልቂት እጅግ በአጭር ግዜ ውስጥ ሊደርስ የቻለው ብለን ስንጠይቅ ይበልጥ የሚያሳምመን የጦርነቱ እልባት ላይ ያልደረሰ ሙሆንና የውድመት አድማሱን እያሳፋ ሄዶ ዛሬ ሰሜን ሸዋ እነ አጣዬ ማጀቴ ከሚሴና ብሎም ሚሌ አካባቢ የጦር አውድማ ሆነው የማየታችን መራር ሀቅ – በዚሁ ቀጠና ውስጥ ያሉት እንደነ ደብረብርሃን ደብረ ሲና እና ብሎም  አዲስ አበባና አከባቢዋ ተመሳሳይ እጣፈንታ አይገጥማቸውም እንዳንል የሚያበቃ ተስፋ ሰጪ አመራር እያየን ያለመሆናችን ሁኔታ ይህ ዛሬ በሰሜን ሸዋ፣ወሎ፣ጎንደር፣አፋርና ብሎም ትግራይ እያየን እና እየሰማን ያለነው እልቂትና ውድመት ነግ በአይናችን ስር የመላ ኢትዮጲያ እጣፈንታ የሚሆን ነው ብለን ስንገልጽ መጥፎ ናፋቂ አሊያም በቀቢጸ ተስፋ የተሞላን ሆነን ሳይሆን ባንወድም በግድ የገሀዱን ሀቅ የተቀበልን ስለሆንን ነው።
፨ ለዚህ ሁሉ ውድመትስ ዋና ተዋናዩና ተጠያቂው ማን ነው ??
ለዚህ ሁሉ ውድመትና ብሎም ለቀጣይ ሀገር አቀፋዊ ውድመት የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው አሸባሪውና ወራሪው ወያኔ ነው ብሎ አብዛኛው ሕዝብ ጣቱን ቢቀስርም እውንታው ግን ተገላቢጦሽ በሆነ ደረጃ የወያኔን ተስፋፊነትና ብሎም በትግራይ ሲካሄድ የነበረውን ጦርነት በአግባቡ መምራት ባልቻለው የብልጽግና መራሹ ጭንጋፍ መንግስት መሃይማዊ እቅድ፣ ፖሊሲና መሰሪነት ባጀለው አቌሙ የተነሳ ጦርነቱን ሆን ብሎ ወደ አማራ ግዛት ጎትቶ በማምጣት ጭምር ግንባር ቀደም ተጠያቂው ስልጣን ላይ ያለው የብልጽግናው መንግስት ነው።
ለምሳሌ ያህል በሁሉም ግንባሮች እስከአሁኗ ድረስ መከላከያውም ሆነ የአማራ ልዩ ኋይል የአማራ ሕዝባዊ ኋይል ፋኖ እና የአማራ ሚሊሺያ የማጥቃት ዘመቻ እንዲፈጽም ሲታዘዝ አልታየም። ጦርነቱ በሙሉ በወያኔ አጥቂነትና በእኛ ኋይሎች ተከላካይነት እየተካሄደ ያለበትን አመራር ተሸክሞ ይህንን ጦርነት በአሸናፊነት እንወጣለን አሊያም በአጭር ግዜ ከእልባት ላይ እናደርሳለን ብለን ተስፋ እንዳናደርግ አድርጔል።
በዚህም መሰረት መላው የኢትዮጲያ ሕዝብ በተለይ በተለይ የጦርነቱ ገፈት ቀማሽ የሆነው የአማራና የአፋር ሕዝብ ጦርነቱን የሚመክትበትን አጠቃላይ እስትራቴጂና የእዝ ተቌም በአዲስ መልክ ለመያዝ የተገደዱበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ሊያውቁ ይግባል ባይ ነኝ። ይህ አዲሱ እይታዊ አሰላለፍም ጦርነቱን እስካሁን ድረስ እየመራ ካለው ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራር በተለየ ሁኔታ እና በተለይም የፌዴራሉን እዝ ያላካተተ የጦርነት ዘመቻ መምሪያን በማቌቌም ይህንን ጦርነት ለመምራት ካልተወሰነ በስተቀር የፌዴራሉ መንግስት አሸባሪ ብሎ ከፈረጀው የወያኔ ቡድን የእውቅና ይስጠኝን ልመናውን እንደ የመደራደሪያነት አጀንዳ አድርጎ ላለው ድርድር ላይ አትኩሮቱን የሰጠ ከመሆኑም በላይ ጦርነቱን በአግባቡ ለመምራት አቅም ብቃትና ፈቃደኝነትም የሌለው መሆኑን ያረጋገጠ ስለሆነ ተስፋ ማድረግ እጅግ የከፋ ዋጋ ያስከፍለናል እንጂ የተሻለን ሁኔታ የሚያመጣልን እንዳልሆነ መረዳት ይገባል።
፠ የጭንጋፉ መንግስት የመደራደሪያ ሶስት ቅድመ አጀንዳዎች 
አቢይ መራሹ መንግስት ከዚህ ሁሉ ውድመት በኋላ ከወራሪው ወያኔ ጋር ለመደራደር ያቀረባቸው ሶስት መሰረታዊ ቅድመ  ሁኔታዎች
፨ 1ኛ/ ህወሓት ለብልጽግና መንግሥት እውቅና እንዲሰጥ
፨ 2ኛ/ ጦርነት ማቆም
፨ 3ኛ/ ህወሓት ከወረራቸው የአማራ እና የአፋር አካባቢዎች ለቆ መውጣት የሚሉ ናቸው፡፡
(ተመልከቱልኝማ-ይህንን መንግስት ነኝ ባዩ አሸባሪ ብሎ ከፈረጀው እውቅናን ሲማጸን)
በሚደንቅ ሁኔታ ወያኔ ለመደራደሪያነት ካቀረበቺው ቅድመ ሁኔታዎች ውስጥ የደምና ለወደመ ንብረት  ካሳ የሚጠይቅ ሲሆን መንግስት ነኝ ባዩ ግን በአንደኛነት ያስቀመጠው እራሱ አሸባሪ ብሎ በፈረጀው ቡድን እውቅና ይሰጠኝ የሚል ሆኖ እያየን ነው።
ይህ መንግስታዊ አቌምና የመደራደሪያ ጭብጥ ነጥቦች ለአማራው በቁሱሉ ላይ አሲድ የመነስነስ ያህል እጅግ የሚጎዳበት እንጂ ቅንጣትም የሚጠበቅበትና መብቱ የሚከበርበት ያለመሆኑን በተጨባጭ አመላካች ማስረጃ በመሆኑ የራሱ የሆነ አሰላለፍን ከማእከላዊው የፌዴራል መንግስት ማእቀፍ ውጪ አደርጅቶ እንዲንቀሳቀስ ሁኔታው ያስገድደዋል። በእርግጥ ይህንን ለማድረግ መጀመሪያ ባህርዳር ከአቢይ የቀጥታ ታዛዥ አገልጋይነት ነጻ መውጣት ይገባታልና ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል-እንዴትስ ሊፈጸም ይችላል በቀጣይ የምመለስበት አርእስቴ ነውና አማራው ከኦህዴድ መራሹ ብልጽግና አመራር ነጻ የሆነ የራሱን ኋይል የመመስረቱ ወይም የተመሰረተውንም አጠንክሮ ለዚህ ተግባር ብቁ ማድረግ ለጥያቄ እማይቀርብ መሆኑን በመግለጽ መጣጥፌን እቌጫለሁ።
Filed in: Amharic