>

በተከታታይ ቀናት አልገኝ ያሉቱ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ዛሮም አልተገኙም!! ባልደራስ

በተከታታይ ቀናት አልገኝ ያሉቱ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ዛሮም አልተገኙም – ሌላ ቀጠሮ…?!!
ባልደራስ

      የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የጸረ ሽብር ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በእነ እስክንድር ነጋ የክስ መዝገብ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ናቸው ተብለው የተመዘገቡ “እማኞች” ቀርበው ይመሰክራሉ ተብለው ከተጠበቀበት ቀን ለ1 ሳምንት ያህል በስልክ እና በአካል “አልገኝ” ማለታቸውን ዛሬ በዋለው ችሎት ተነገረ።
       የዐቃቤ ሕግ ምስክር የሆኑት 4ኛ ምስክር
” ፍጹም ተሰማ ” በኮሮና በሽታ ታመው እንደነበረ ፤ ሆኖም ግን የተሻላቸው ስለሆነ ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ ከተባለበት ከኅዳር 7 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ እስክ ኅዳር 9 ቀን 2014 ዓ.ም በዐቃቤ ሕግ የተለያየ ምክንያቶች እየተሰጠ ያለቀረቡ ሲሆን ዛሬ በዋለው ችሎት እኚህ  ምስክር አለመገኘታቸውን አስመልክቶ ” ዛሬ እመጣለሁ ብለውን ነበር ፤ አልመጡም ልናገኛቸው አልቻልንም። ስልካቸው ላይ የደወልን ቢሆንም ማግኘት አልቻልንም” በማለት ዐቃቤ ሕግ ለፍ/ቤት ምላሽ ሰጥቷል ።
    ቀሪዎች 8ኛ እና 9ኛ ምስክር የሆኑት “ጌትነት ተስፋዬ እና ትንሳኤ ማሞ”ን በተመለከተ ለባለፉት 5 ቀናት ቀረበው ምስክርነታቸውን መስጠት አልቻሉም ። በተደጋጋሚ አለመገኘታቸውን የተመለከተው ፍ/ቤት ኅዳር 7 ቀን 2014 ዓ.ም መጥሪያ እንዲደርሳቸው ትዕዛዝ ሰጥቷል ። ሆኖም ግን የፌደራል ፖሊስ አባል የሆኑት ረ/ሳ ቢኒያም አፈወርቅ ለፍ/ቤት በደብዳቤ እንደገለጹት የፍርድ ቤት መጥሪያ የደረሳቸው “ኅዳር 9 ቀን 2014 ዓ.ም ከቀኑ 9 : 00 ሰዓት መጥሪያ ዘግይቶ እንደደረሰው እንዲሁም በተደጋጋሚ ስልክ ቢደወልላቸው አለመገኘታቸው” ፖሊስ ለፍ/ቤት ገልጿል ። በተጨማሪ ዐቃቤ ሕግ ” የሚቻለንን ሁሉ ጥረት ያደረግን ቢሆንም ምስክሮችን ማግኘት አልቻልኩም ፤ ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠኝ ” በማለት ለፍርድ ቤት አቤት ብሏል ።
     በዐቃቤ ሕግ እና በፌዴራል ፖሊስ በኩል  የቀረበውን ምክንያቶች አስመልክቶ የተከሳሽ ጠበቃ የሆኑት ጠበቃ ቤተማርያ አለማየሁ ” ፖሊስ በጻፈው የደብዳቤ ምላሽ መጥሪያ ኅዳር 9 ቀን ትዕዛዝ እንደደረሰው ገልጿል ።ይህ ሆን ተብሎ የተደረገ ነው። ትዕዛዙ አስቀድሞ ኅዳር 7 ቀን ወጪ መሆኑንና  ዐቃቤ ሕግ ከዚህ ቀደም በነበረው ችሎት ገልጿል ፤ዛሬ እንዴት  ሆኖ ነው ትዕዛዙ ኅዳር 9 ቀን የፌዴራሉ ፖሊስ ደረሰኝ የሚለው ?! ከዚህ ቀደም ከችሎት ዘገባ ጋር በተያያዘ የተሰጠ ትዕዛዝ ከሌሎች ትዕዛዝ በመለየት መጥሪያ በቶሎ እንዲደርስ አድርጓል ። በተደጋጋሚ የተከሳሾችን መብት የሚጠብቁ ትዕዛዞችን ሆነ  ተብሎ እንዲጎተት እየተደረገ ነው። የፍርድ ቤት ትዕዛዝ በአግባቡ እየተፈጸመ አይደለም ፤ዐቃቤ ሕግ ሆነ  ብሎ ለሚሰራው ፍትሕን የማጎተት ተግባር የሥነ ሥርዓት ሕጉ አይፈቀድም ። ችሎቱ ተደጋጋሚ ዕድል ለዐቃቤ ሕግ ሰጥቷል ፤ ከዚህ በኋላ እንዲህ አይነቱ ምክንያቶች ፍ/ቤቱ ሊቀበል አይገባም ።ዐቃቤ ሕግ ምን ያህል ጥረት እንዳደረገ አንዳችም ነገር የሚያመላክት ነገር የለም። ዐቃቤ ህግ  በህግ ከተሰጠው ሰፊ ስልጣኖች የቱንም አልተጠቀመም ፤ ለምስክሮች የስልክ ጥሪ ሙከራ አድርጊያለው ከማለት ውጪ ።ስልክ ብቻ በቂ አይደለም ፤ዐቃቤ ሕግ ግዴታውን አልተወጣም ። ዐቃቤ ህግ ትልቅ ተቋም ነው ትልቅ በጀት ይመደብለታል፣ ከፍተኛም የሰው ሃይል አለው። ስለዚህ ትልቅ ስራ ይጠበቅበታል ። ትልቁን ነገር እየተወ ትንንሽ ነገሮች ላይ ነው የሚያተኩረው፤ ዋናውን ነገር ትቶ የሰናፍጭ ቅንጣት ላይ ነው የሚያተኩረው። እስካሁን በተሰሙት ምስክሮች ላይ ብይን ይስጥ የቀሩት ይታለፉ። ” በማለት ጠበቃ ቤተማርያ አለማየሁ ለፍርድ ቤት አቤት ብለዋል ።
    ሌላኛው የተከሳሾች ጠበቃ የሆኑት ፤ ጠበቃ ሔኖክ አክሊሉ  በበኩላቸው :- ” ዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ትናንትና  እና ከዛ በፊት መምጣት እንደሚችሉ ነግሮን ነበር፤  ስልክ አያነሱምም ብሏል፤ አሁን ደግሞ ስልካቸው ዝግ ነው እያለን ነው።  ምስክሮች አድራሻቸውም አይታወቅም። ይምጡ አይምጡ በዚህ ሁኔታ የሚታወቅ ነገር የለም ፤ የዐቃቤ ሕግ ስራ እጅግ የሚያሳፍር ነው።  በዚህ እስር ጊዜ  አቶ እስክንድር ሁለት ጊዜ  ተደብድበዋል፣ አቶ ስንታየሁ የኩላሊት በሽተኛ ሆነዋል መድሃኒት ይዘው ነው የሚንቀሳቀሱት፣ ወ/ሮ ቀለብ ህፃን ልጃቸው ከእናታቸው በመራቃቸው በደረሰባቸው ጭንቀት ምን እንደሆኑ ለዚሁ ፍርድ ቤቱ ቀርበው አስረድተዋል፣ ወ/ት አስካለም ርቀው ከሚገኙት ታማሚ እናታቸው ጋር በሳምንት አንድ ጊዜ  ለ10 ደቂቃ በስልክ እንዲያገኟቸው የተፈቀደው ገና አሁን ነው። ይሄ ሁሉ ዋጋ እየተከፈለ ያለው
ፍትህ ይገኛል ተጠያቂነት ይኑር ተብሎ ነው።
   ለዐቃቤ ሕግ  ተደጋጋሚ እድል ተሰጥቷል። አሁን ግን ከቀን ወደ ቀን አሳፋሪ ነገር ነው እያደረገ ያለው። ‘ምንም አይፈጠርም’ በሚል ትዕዛዝ እየፈፀመ አይደለም። አሁን ግን በቃህ ሊባል ይገባል። በቂ ቀጠሮዎች ተሰጥተውታል ። ምስክሮቹ ስልካቸውን አጥፍተው ሊገኙ አልቻሉም። ደምበኞቻችን ከዚህ በላይ መጉላላት የለባቸውም። መዝገብ ተመርምሮ የቀሩት ምስክሮች ታልፈው ባለው ላይ ውሳኔ ይሰጥልን። ” በማለት በዐቃቤ ሕግ በኩል ለቀረበው አቤቱታ ምላሽ ሰጥተዋል ።
   በዐቃቤ ሕግ በኩል የቀረበው ምክንያት አስመልክቶ በጠበቆች በኩል የተሰጠው ምላሽ እንዳለ ሆነ ፤ አቶ ስንታየሁ ቸኮል ፣ ወ/ሮ ቀለብ ስዩም እና ወ/ሪ አስካለ ደምሌ የችሎቱ ታዳሚ ልብ የሚነካ እጅግ ምርር ባለ መልኩ ፤ ” በፍትሕ እጦት እየተንገላቱ እንደሆነ፣ ዐቃቤ ሕግ በቂ ምክንያት ሳይኖረው በተደጋጋሚ አሰልቺ ምክንያቶች እያቀረበ እያንገላተቸው እንደሆነና ፤ ፍርድ ቤቱ በፍትሕ እጦት እየደረሰባቸው ያለውን በደል በአግባብ ተገንዝቦ
አፋጣኝ ፍትሕ ” እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል ።
   ሰሞኑን በዋለው ችሎት እና እየሆነ ባለው ነገር ከምንም በላይ በዐቃቤ ሕግ በኩል እየቀረቡ ያሉ  ምክንያቶችን አስመልክቶ ፤ አንደኛ ተከሳሽ የባልደራስ ፕሬዚደንት አቶ እስክንድር  ነገ ሳምንቱን በሙሉ እጅግ ጥልቅ በሆነ ዝምታ እና ትዝብት አንዳችም ነገር ሳይናገሩ ፤ የሳምንቱ ችሎት ተጠናቋል ።
    ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ፤ ” ፖሊስ ያለምን ምክንያት ምስክሮችን ኅዳር 16 እና 17 ቀን 2014 ዓ.ም ይዞ እንዲቀርብ ” በማለት  ትዕዛዝ የሰጠ ሲሆን ፤ በችሎት ለተገኙት የፌደራል ፖሊስ አባል ለሆኑት  ረ/ሳ ቢኒያም አፈወርቅ ጥብቅ ትዕዛዝ በመስጠት ፣ ይህ ችሎት ካበቃ በኋላ መጥሪያ ይዘው እንዲሄዱ  ፍርድ ቤቱ አፅንኦት በመስጠት አሳስቧል።
Filed in: Amharic