>

“አገባሻለሁ ያለ ሁሉ ላያገባሽ ከባልሽ ጋር ሆድ አትባባሽ” ( ይነጋል በላቸው)

“አገባሻለሁ ያለ ሁሉ ላያገባሽ ከባልሽ ጋር ሆድ አትባባሽ”

ይነጋል በላቸው


ጆሮ አይሰማው፣ ዐይንም አያየው የለምና ብዙ አስደናቂና አስገራሚ፣ አሳሳቢና አስደንጋጭም ነገር እየሰማንና እያየን ነው፡፡ የጊዜ ባቡር የማያመጣው ኮተት ባለመኖሩ በተለይ ያለንበት ዘመን የበርካታ ጉዶች መገለጫ ሆኗል፡፡ ይሉኝታና ሀፍረት ከሀገር ተሰደው አገር ምድሩ በዐይን አውጣዎች ተወሯል፡፡ በዱሮ ዘመን “ከእንጨት መርጦ ለታቦት፣ ከሰው መርጦ ለሹመት” ይባል ነበር፡፡ አሁን ደግሞ የዚያ ብሒል የተገላቢጦሽ ሆነና ምርጥ ምርጥ ውሸታሞችና አስመሳይ ትያትረኞች ቤተ መንግሥቱን ሳይቀር በግላጭ ተቆጣጥረው መቋጫ በሌለው ለዛቢስ ድራማቸው ራሳቸውን በማታለል በሀገርና በሕዝብ እየተሳለቁ ነው፡፡ ይሁን፡፡ ንግርትም እንበለው ትንቢት በተግባር ካልታዬ ነቢያትን ዋሾ ያደርጋልና ለወደፊትም ቢሆን ቀጣይ ነቢያት የሚታያቸውን እንዳይናገሩ ተግዳሮት እንዳይጥል በግምባር የምናየው ሁሉ ሊሆን የግድ ነው፤ መቻል ነው እንግዲህ፡፡ ለማለዘብ ግን በፈጣሪ መንገድ የሚራመዱ ሃቀኛ ሃይማኖተኞች በትጋት ቢጸልዩ እግዚአብሔር በአመክሮ የታዘዘውን መቅሰፍት በረድ ሊያደርግልን ይቻለዋል፡፡ 

ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በተለይ ባለፉት 31 ዓመታት ተነግሮ የማያልቅ ስቃይና መከራ ውስጥ መኖራቸው ከሰማይም ከምድርም የተሠወረ አይደለም፡፡ ሀገራችንና ዜጎቿ የፈረንጆች ቤተ ሙከራ ነበሩ፤ አሁንም ድረስ ናቸው፡፡ የሰይጣናዊ ንድፈ ሃሳቦችና የአዳዲስ ጦር መሣሪያዎች መሞከሪያ፣ የግድያና የሞት ዓይነቶች መፈተኛ፣ የቫይረሶችና የዘርፍሬ አምካኝ ንጥረ ነገሮች መፈተሻ … ሆነው ዘልቀዋል፡፡ እነግፍ አይፈሬዎች ያላደረጉን የለም፡፡ 

ይህ ሁሉ ለማመን የሚከብድ ዘግናኝ ታሪክ የተፈጸመባቸው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በተለይም አማሮች ከተደገሰላቸው ዕልቂት ነፃ የሚወጡበት የብሥራት ዘመን ከፊት ለፊታችን መኖሩ ተስፋችንን ያለመልመዋል፡፡ ይህን ተስፋ ማየት የሚችሉ አሉ፤ ማየት የማይችሉም አሉ፡፡ በመጪው የነፃነት ዘመን የሚጎዱ አሉ፤ የማይጎዱም አሉ፡፡ የአሁኑ ዘመን በሚሰጣቸው በደም የተነከረ ብልጭልጭ ነገር የሚማረኩና ለአሁኑ ዘመን የአገዛዝ አበጋዞች የሚታዘዙ ኅሊናቢሶች ጎርፉን አያልፉትም እንጂ ካለፉ አንገታቸውን ደፍተው ለመኖር ይገደዳሉ፡፡ እመለስበታለሁ፡፡

ሰሞኑን በቤተ ክህነት አካባቢ የሚወራው ነገር አስቂኝ ነው፡፡ በተንሻፈፈና በድራማ መልክ በተጎላበተ ማለትም በድብቅ በተጨማመረ የጥይት ጋጋታ ኦርቶዶክስን ለማፍረስ የሚደረገው ጥረት ግልጽ ነውረኝነት መሆኑን ሁሉም ወገን ሊገነዘብ ይገባል፡፡ ስንትና ስንት ሽዎች አብያተ ክርስቲያን የምታስተዳድር ቤተ ክህነት ለክሳቸው ማዳበሪያ እንዲሆን በኋላ የጨመሩትን ወደ 500 ገደማ ጥይት ትተን በቃለ ጉባኤ የተያዘውና ኃላፊ በተለዋወጠ ቁጥር በህጋዊ የርክክብ ሰነድ ወደቀጣይ ኃላፊ የሚተላለፈው ወደ 1300 ገደማ የሚገመት ጥይት በግምጃ ቤት መኖሩ ምንም ማለት አይደለም፤ ይህ ለጥበቃ ሥራ የሚውል ጥይት ዋጋው ቢሰላ አማራን ከርቀት እንዲቀነድብበት አቢይና ሽመልስ ለአንድ ኦነግ ሸኔያቸው በብር 500 ሽህ ገደማ የሚገዙትን ስናይፐር ዋጋ አንድ አምስት መቶኛ አይሆንም፤ ለጥበቃ ሥራ የሚውል የሀገር ሀብት መሆኑም ያለና የነበረ እንጂ እንዲህ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚያስብል ነገር አይደለም፡፡ እመት አህይት “አያ ጅቦ ሳታመካኝ ብላኝ” ያለችው ወድዳ አልነበረም – እንደዚህ ያለ ግራ አጋቢ ነገር ቢገጥማት እንጂ፡፡ ኦርቶዶክስን ማፍረስ እስከዚህን ቀላል ከመሰላቸው ይበርቱ ከማለት ውጪ የምለው የለም – በበኩሌ፡፡ ግን ተሳስተዋል፡፡ ወጥ እየረገጡና ጉድጓዳቸውን እያራቁ ነው፡፡ ለካንስ ለመዋሸትና ለማስመሰልም ዕውቀትን ይጠይቃል! ለካንስ ሰውን በሀሰት መክሰስና መወንጀልም በማንአለብኝነት የተሞላ ድፍረትን ብቻ ሳይሆን ብልሃትንም ይሻል! ሙት ወቃሽ አያድርገኝና ወያኔ በዚህ ረገድ ብልጥ ነበረች፡፡ ማስመሰል እንኳን ታውቅት ነበር – በተለይ በመጀመሪያው አካባቢ፡፡ እነዚህ ግን የለየላቸው ፋራዎች ሆኑና በኬኛ ፖለቲካ ታውረው የማያሳዩት ነውር ላይኖር ነው፡፡ “ይብላኝ ለወለደሽ ያገባሽስ ይፈታሻል” ብሎ የተረተው ሰው ልጅ ይውጣለት፡፡ ከነዚህ ጋር እንደሰው መቆጠር ራሱ እንዴቱን ያህል ያሳፍራል ግን!! እነሱ ብቻ ሁሉንም ለመሆን፣ ሁሉንም ለመያዝና ሁሉንም ለማድረግ ያላቸው ፍላጎት ቅጥ አጣ፡፡  

የሚገርመው ደግሞ የአጨብጫቢያቸው ብዛት፡፡ ከኢሳት ቴሌቪዥን እስከ ማንትስ ዩቲዩብ፣ ከፕሮፌሰርና ዶክተር ማንትሶች ጀምሮ እስከ ከርስ-አምላኩ ጋዜጠኛ እንትና … በሚገርም ሁኔታ ሁሉም የነሱ አፋዳሽ ሆኖ መገኘቱ በርግጥም ይህ አቢይ የሚባል ሁሉ-አማረሽ ሰውዬ የቆሌ-ባዲገዞቹ የነጠቋር ቡሌና የነአዳል ሞቲ፣ የነዋስ አንጋችና የነአንበሦ የዛር አውሊያዎች ይረዱታል የሚባለው እውነት ሳይሆን አይቀርም፡፡ እነዚህ አደሽዳሾች በሰውዬው ፍቅር ብን ብለው በዐይናችን ሂድ ሲሉት መታዘብ በእጀጉ ያስደንቃል – በሀሰት የትምህርትና የወታደራዊ ማዕረጎች የተብለጨለጨና ከጥራዝ ነጠቅ ዕውቀት ውጪ ይህ ነው የሚባል ሥነ መንግሥታዊ የአስተዳደርም ይሁን የአካዳሚ ጥበብና ዕውቀት የሌለው አንድ ሞላጫ ጎልማሣ ይህን ሁሉ የምሁርና የአክቲቪስት መንጋ እንዴት እንደሚጋልበው ሳይ ግርም ይለኛል – መታደል እንዳልለው የሁሉም መጨረሻ ወለል ብሎ ይታየኛልና አልልም፤ እንዲያው በሞቴ ይሁንባችሁና አሁን ያ ለሀገሩ ስንትና ስንት የደከመ ፕሮፌሰር አልማርያም የሚሉት ወንድማችን እዚህም ደሞ ዶክተር ዳኛቸው የሚባለው ወገናችን በሀገራችን ያለውን ተጨባጭ እውነታ መረዳት አቅቷቸው ነው ልጃቸው ለሚሆን ለዚህ ሮጦ ያልጠገበ አገር አማሽ ውርጋጥ የሚሰግዱት? ታዲያ እሱ ምን ያድርግ? ሰጋጅ ከተገኘ፣ አማኝ ከተፈጠረ አምላካ አማልክት መሆን ምን ያቅታል? የአፍሪካ ሕዝብ ዱሮም ጀምሮ እየተበጠበጠ ያለው ቁጭ ብሎ በሚሰቅላቸው  አምባገነን መሪዎች ነው፡፡ ልብ አድርጉ – ትልቁ ዳቦ ሊጥ ከሆነ የኔ ቢጤው ተራ ዜጋ አቢይ ባለፈበት ሁሉ ጫማውን እያወለቀ፣ ጋቢውን እያጣፋ በ“ኦ አምላክነ ወመሓረነ ኩልነ በእንተ አቡከ አህመድ አሊ…” እያለ በትዕምርተ መስቀል በማማተብ እግሩ ሥር ቢነጠፍለት ምኑ ይገርማል? ኧረ እንዲያውም ጽላት ይቀረጽለትና በነቢይት ብርቱካን ተባርኮና በዘማሪት ዝናሽ ታያቸው መዝሙር ተሟሽቶ በአንዱ “ቸርች” ይደበርለት! ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ፡፡

ለማንኛውም “ገንዘብ የተሸከመች አህያ የማትደረማምሰው ምሽግ የለም” የሚባለው እውነት ነው፡፡ ገንዘብና ሥልጣን ዱሮም የሰውን ልጅ አጥፊው መሆናቸው ቢታወቅም ለምሣሌ የት ይደርሳል የተባለው አብን በጥቃቅን ሹመት በመነሁለል እንዲህ የማሽላ እንጀራ ሆኖ አቢይ ሥር መሽመድመዱ በሰዎች ምንነት ብያኔ ላይ አዲስ ጥናት እንዲካሄድ የሚጋብዝ ነው – ዐይን ገባው ማለት ነው – አካሄዳቸው ዱሮውንም አላማረኝም ነበር፤ “የማያድግ ልጅ በአባቱ ምንትስ ይጫወታል” ነውና ተረቱ አጀማመራቸው እንዳይሆን እንዳይን ነበረ – እንዲህ ባጭር ሊቀሩ፡፡ የሌሎቹን ቀደም ብለን ስለምናውቀው ኢዜማ ቁዘማ እያልን እዚህ መደጋገሙ አያስፈልግም፡፡ በውነት፣ በውነት ሰውዬው እጅግ አደገኛ ነው! አደን ያውቅበታል፡፡ ለሥልጣኑና ለድብቅ ዓላማው ሥጋት ይፈጥሩብኛል ብሎ የሚገምታቸውን አንድም በዘብጥያ አንድም በገንዘብና በሥልጣን እየጠረነፈ ጉድ ይሠራቸዋል – ወንድ የአባቱ የወያኔ ልጅ! ምነው እኔንም ባገኘኝና ትንሽዬም ብትሆን – ለምን መጫወቻ አሻንጉሊቶቹንና ቤተ መንግሥቱ አጠገብ ያስገነባውን መናፈሻ መጠበቅ አይሆንም – ሥልጣን ሰጥቶ ማኖ ባስነካኝ፤ ያኔ እንዲህ መቀላመድ የለ፤ በየሣምንቱ እንደጣቃ መተርተር የለ – ዝም ብዬ ውጫጮቼን ማሳደግ፡፡ … እውነቱን ለመናገር እንደዚህ ያለ ብላቴና እንኳን በታሪክ በህልምና በልቦለድ ዓለምም መኖሩን አላውቅም፤ ሲነገር ብንሰማ እንኳን ማመን ይከብዳል፡፡ ከሰይጣን የሚበልጥ ሰይጣን ማን እንደሆነ ብጠየቅ አቢይን ከወያኔ ጋር ደምሬ በአንደኛነት አስቀምጣለሁ፤ አይበላለጡማ! ይህ አቢይ – ለሤራው ስኬት የቀን ዕረፍት የሌት ዕንቅልፍ የለውም፤ ሦስቱን ልጆቹን እንዴትና ምን ጊዜ አግኝቶ እንደወለዳቸው አንድዬ ይወቅ – እመት ዝናሽ ካልተከፋችብኝ ይቺን ጥያቄየን ሁለቱንም ጠይቁልኝ እስኪ፡፡  

ወያኔ ሸዋሮቢት ደረሰች ይላሉ፡፡ ትድረስ፡፡ ስትፈልግ ደብረ ብርሃንን አልፋ ሸኖን ትጠጋ፡፡ ችግር የለውም፡፡ “በሰሜን ይመጣሉ፤ በስተመጨረሻ ግን እንደጉምና እንደጭስ ብን ብለው ይጠፋሉ” ሲባል የሰማሁት ዛሬና ትናንት ሳይሆን ያኔ ዱሮ ጢነኛ ሳለሁ ነበር፡፡ አሁን የምገኝበትንና በቀጣይ ጥቂት ወራት የሚከናወኑትን ዘግናኝ ሁኔታዎችንም እንደዚሁ ከረጂም ዘመን በፊት ጀምሮ በፍርሀት ቆፈን ውስጥ ሆኜ ልክ እንደክርስቶስ “እባክህን ጌታ ሆይ! ይህንንስ በኔ ዘመን አታድርገው!” እያልኩ በመጸለይ የምጠብቃቸው እንጂ ለኔ አዲስ አይደሉም፡፡ አዲስ እየሆነብኝ ክፉኛ እየደነገጥኩ ያለሁት ይልቁንስ ትልቅ ሰው የምለው ሁሉ፣ የነገ የሀገር አለኝታ የምለው ሁሉ፣ በንግግሩ ማማር ኢትዮጵያን አፍርሶ ይሠራታል የምለው ታዋቂና ዝነኛ ሁሉ …. በፀረ ኦርቶዶክሱና በፀረ ኢትዮጵያው የኦሮሙማ ጎራ እየተሸበለለ የአቢይ ካዳሚና አጋፋሪ መሆኑ፣ የፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ውታፍ ነቃይ ሆኖ እንደይሁዳ ሀገሩን ባወጣች የሚቸበችብ ሆዳም አጋሰስና የአቢይን ዝግንትል ተሸካሚ ጌኛ መሆኑ ነው፡፡ ሌላው የዘመኑ መገለጫ የሆነው የሙስናና የእምነት መላላት፣ የሞራል ዝቅጠትና ብሔራዊ የሀገር ስሜት እንዲሁም በሰዎች ዘንድ የመተሳሰብና የመፈቃቀር ባህላችን መጥፋትም ሁሉ በእጅጉ እያስደነገጠኝ አለሁ፡፡ ዙሪያ ገባውን ሁሉ ስመለከት አብዛኛው ነገር ያስፈራኛል፡፡

እመለስበታለሁ ወዳልኩት ተመለስኩ፡፡ ክፉ “የላይ ላይ” አለብኝና እርሱ ሹክ የሚለኝን ነው የምናገረው፡፡ ማን ከማን ያንሳል? እነሱስ “ጌታ የሱስ አናገረኝ …” እያሉ አርቲ ቡርቲ ይቀበጣጥሩ የለም እንዴ? – “እነሱ” ስል እነጩፊቲን ማለቴ እንጂ ትክክለኛዎቹን የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች እንዳልሆነ በእግረ መንገድ መጠቆም እፈልጋለሁ ታዲያ፡፡ ኧረ ቅድስት ማርያምን እንደቆሎ ጓደኛዋ የምትቆጥርና በየሰዓቱ ወደጓዳዋ ወጣ ገባ እያለች “ማርያም እንዲህ ብላሻለች” እያለች ባልና ሚስትን ሁሉ የምታፋታ ተንከሲስም አለችልህ፤ ወይ የኛ ሀገር ጉዳጉድ አበዛዝ!!

“አገባሻለሁ ያለ ሁሉ ላያገባሽ ከባልሽ ጋር ሆድ አትባባሽ” ይባላል፡፡ አቢይ በሥልጣን የሚዘልቅ መስሏቸው በልቶ ለማይጠረቃ ሆዳቸው ሲሉ ከርሱ ቂጥ ሉጥ ሉጥ የሚሉ ሁሉ አቢይ እንደማያዋጣቸው አሁኑኑ ተገንዝበው ወደሕዝብ እንዲመለሱ፣ ወደኢትዮጵያዊነት ካምፕ እንዲቀላቀሉ ጨለማው ከዚህም ሳይበረታ አሁንና ዛሬ ላሳስባቸው እወዳለሁ፡፡ አቢይን ማመን ጉም መዝገን መሆኑን የማይረዳ ሰው የሰውነት ተፈጥሮና ባሕርይ አለው ብዬ አላምንም፡፡ አቢይ እንዲህ ነው እንዲያ ነው የሚል ዝባዝንኬ ውስጥ መግባት አልፈልግም – ብዙ ጊዜ ተብሏል፡፡ እንደመሪ ሃሳብ ግን አቢይ ማለት ኢትዮጵያን ለሚያጠፉ ኃይሎች ዋና መሪና ሰብሳቢ ሆኖ በጨለማው ንጉሥ የተሾመ ሥልጣኑም ግፋ ቢል ከአምስት ዓመት የማይበልጥ የሂትለርና የሙሶሊኒ ዘረመላዊ ተቀጥላ ነው፡፡ ሰማያዊና ምድራዊ የጊዜ ሥሌት በእጅጉ የተለያዬ በመሆኑ ማሣጠሩን ፈርቼ እንጂ የዚህ ሰውዬ የሥልጣን ዕድሜ ከአሁን በኋላ በዛ ቢባል አንድና ሁለት ሰዓት ቢሆን ጠልቼ አይደለም፡፡ መጨረሻው ግን ከሂትለርና ከሙሶሊኒም የከፋ ስለመሆኑ አልጠራጠርም፡፡ ምክንያቱም እርሱ አራት ኪሎ ከገባ በኋላ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የደረሰባቸው ግፍና በደል፣ ዕልቂትና ወድመት፣ ስደትና መፈናቀል በወያኔ የ27 ዓመታት የሰቆቃ ዘመን ከደረሰው በእጅጉ የከፋ ነው፡፡ ይህን መካድ የእውነትን ዐይኖች እንደመጠንቆል ነው፡፡ የዚህ ሰውዬ የደም እጆች ያላንኳኩት በተለይ የአማራ ቤት መኖሩ አጠራጣሪ ነው፡፡ 

ለሥልጣንም ይሁን ለሀብት አቢይንና ኦሮሙማን ጠጋ ጠጋ የምትሉ የማንኛውም ነገድ አባላት በተለይም በአማራ ስም የምትነግዱ ብአዴኖች ራሳችሁን ጠይቁ፡፡ አሁን ሚሊዮንና ቢሊዮን ቢኖርህ መቼና የት ሆነህ ትጠቀምበታለህ? በወያኔና ኦሮሙማ እንዲሁም በምዕራባውያንና በአሜሪካ ሲአይኤ የተናበበ ሤራ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ በገዛ የትውልድ ቀየውና በመላዋ ሀገራችን ልክ እንደዝምብ ተቆጥሮ በገፍ እያለቀና እየተፈናቀለ ያንተ የይስሙላ ሹመትና የማትጠቀምበት ሀብትና ገንዘብ ምን ያደርግልሃል? ከሦርያና ከየመን፣ ከዩጎዝላቪያና ከሶማሊያ ተማር፡፡ ለአጭሯ ምድራዊ ዕድሜ ብለህ ለትውልድ የሚተርፍ ፀፀት አትሸምት፡፡ ጎመን በጤናን ልመድ፡፡ 

አቢይና ሽመልስ ጋር የሚተባበር ኢትዮጵያን እየገደለ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያን የሚገድል ሁሉ ደግሞ በጥቂት ወራት ውስጥ የማያዳግም መለኮታዊ መቅሰፍት እንደሚደርስበት ይረዳ፡፡ ማንም የዘራውን ነው የሚያጭደው፡፡ የምናገረው አዲስ ነገር ሳይሆን በደርግም በወያኔም በመጠኑም ቢሆን በወዲያኛው የአፄው ዘመን የተገነዘብኩትን እውነት ነው እየነገርኩህ ያለሁት፡፡ ለአብነት ኦሮሙማ ሰሞኑን የነካው ቀፎ የፈጣሪን ትግስት የሚፈታተንና መጨረሻን የሚያቃርብ ለመሆኑ ጥርጥር የለኝም፡፡ ዐይጥ ለሞቷ የድመትን አፍንጫ ታሸታለች፤ ፍየልም ሲሰባ ሾተል ያሸታል፡፡ የኦሮሙማ ጥጋብ ተራውን እስክንድር ነጋንና በርካታዎችን በሀሰት ክስ ያለፍርድ ከማሰር፣ ከማሳደድና ከመግደልም አልፎ የኢትዮጵያን መሠረት የኦርቶዶክስን እምነት እንዲህና እስከዚህ ለማዋረድ ከተነሳ የኢዩ ጩፋና የእስራኤል ዳንሳ የምዕራብ አፍሪካ የመተት ፓኬጅ ያዋጣው እንደሆነ እናያለን፤ ጥጋብን ልክ ካላበጁለት አዋራጅ ነው፤ እንደጥጋብ ያለ የሰው ልጅ ጠላት ደግሞ የለም – “ከተራበ ለጠገበ አዝናለሁ” መባሉም ለዚህ ነው፡፡ ጥጋብ ዐይንን በዕብሪት ሞራ ይጋርዳል፡፡ መሸነፍን አርቆ ማሸነፍን ደግሞ እጅግ አቅርቦ የሚያሳይ አጉሊ መነፅርን ለከንቱዎች እያደለ ብዙዎችን በማይጨበጥ ህልም ያናውዛል – ልክ እንደስፔናዊው ደራሲ ሰርቫንቴስ የምናብ ፍጡር ዶንኪሾት፡፡ ጥጋብ ወለድ ድንቁርናን የሚቆጣጠር ትልቅ ሰው ነው፡፡ ብዙዎች ግን ለዚህ አልታደልንም፡፡ 

የሆነ ሆኖ ቀጣዩ ዓመት የፀሐይ ዓመት ነው፡፡ ምልክቶቹ በአብዛኛው ታይተዋል፤ ገና የሚታዩም አሉ፡፡ ማንም ቢፍጨረጨር የቀጣዩን ዓመት ፀሐይ ከመውጣት ሊያግድ አይችልም፡፡ ለዚህም ነው በእርግጠኝነት ምድረ አሽቃባጭን ከአሁኑ በጎልዳፋ አንደበቴ የማስጠነቅቀው፡፡ ጭንቅላታችንን ሆዳችን ውስጥ የወተፍን ሁሉ በጊዜ እንንቃና ወደየኅሊናችን በቶሎ እንመለስ – ጊዜ የለንም፡፡ ኦሮሙማና ትግሩማ እንደሆኑ ከስንኩል ዓላማቸውና ከመርፌ ቀዳዳም ከጠበበው አስተሳሰባቸው በስተቀር ወዳጅ ዘመድ አያውቁም፤ ሰይጣን ቋሚ ጠላት እንጂ ቋሚ ወዳጅ እንደሌለው ደግሞ መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ላለቀ ጊዜ፣ ለተፈጸመ ዘመን ለሆድ ስለሆድ በሆድ አንገዛ፡፡ የሚያዋጥህን የምታውቀው አንተ ብትሆንም ከጥፋት ጋር መተባበር መጨረሻው ምን ሊሆን እንደሚችል ካላወቅህ ግን ገደል ትገባለህና አሁኑኑ ወስነህ የእውነትን ዘገር ጨብጥ፡፡ ከነገ ፀፀት ራስህን አድን፡፡ ነገም ዛሬን እንዳይመስልህ አትሞኝ፡፡  ዐይነ ልቦናህን ገርበብ አድርግና ዓለምን ተመልከታት … ምን ቀራት? መስሎን እንጂ ሁሉም ነገር አልቋል እኮ! አሁን ስለእውነት እንነጋገር ከተባለ ለፎቅና ለመኪና አቅልን ስተው የሚራወጡበት ዘመን ነው? በፍጡም!! ቢሆንም …. ቢሆንም …. ስደት ወደ ኢትዮጵያ ሊሆን ጊዜው ቀርቧልና “ማምሻም ዕድሜ ነው” መባሉን አትዘንጋ፡፡ ትግስት ኖሮህ እስከዚህ ያነበብከኝ ካለህ በቸር ያገናኘን ወንድማለም፡፡ ቸር ስንብቺልኝ እህታለም፡፡ እንደጨለመ አይቀርም – አይዞን ይነጋል!   

Filed in: Amharic