>

ሀገሬ፤ ሰው አጣሽ ወይ??? ያሬድ ሀይለማርያም

ሀገሬ፤ ሰው አጣሽ ወይ???

ያሬድ ሀይለማርያም

ሀገራችንን የምንወድ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ እንቅልፍ አልባ ሌሊቶችን ማሳለፍ ከጀመርን ወራቶች ተቀጥረዋል። አዎ፤ ኢትዮጵያ ዛሬ ያለችበት ሁኔታ የሚወዷትን ብቻ ሳይሆን የሚጠሏትና ሊያፈርሷት እስከ ገሀነም ለመዝለቅ የቆረጡትንም እኩይ ልጆቿን እንቅልፍ የሚነሳ ነው።
እንደወትሮዮ ሌሊቱን ጣራ ጣራ እያየሁ ሀሳቤን ሳወጣና ሳወርድ የንዋይ ደበበ ‘ሀገሬ ሰው አጣሽ ወይ? … ገና ሀገር ማለት ትርጉሙ አልገባንም’ የሚለው ዘፈኑ ትውስ አለኝና ከፍቼ የእያደመጥኩ ቁዘማዮን ቀጠልኩ። (https://youtu.be/rc33kJHaWzc )
ሀገሬ፤ ከውስጥም፣ ከውጭም በሳት እየተለበለብሽ ነው። እኩይ ልጆችሽ የጫሩት እሳት ውስጥሽን ከመለብለብ አልፎ ታሪካዊ ጠላቶችሽ ክርናቸውን አፈርጥመውና፣ ጥርሳቸውን አሹለው ዙሪያሽን እንዲከቡሽ ምክንያት ሆነዋል። እንደ ጆፌ አሞራ ዝለሽ መውደቅሽን ሲጠብቁ የኖሩ የውጭ ጠላቶችሽ ዛሬ መዝለፍለፍሽን አይተው ከሀሰት ፕሮፖጋንዳ አንስተው በሸር በተሞላው ፖለቲካቸው ስምሽን በቀን አሥሬ እየጠሩ የመፈራረስ እና የእልቂት ሟርት እያዘነቡብሽ ነው። ከአገር ውስጥ አገር በማዋለድ ጥበብ የተካኑት ሃያላንም ምጥሽን ለማቀላጠፍ ወደ ኦፕሬሽን ጣቢያቸው ሊወስዱሽ መጣደፍ ከጀመሩ ውለው አድረዋል።
ወያኔም ከዚህ በሁዋላ ኢትዮጵያን ማስተዳደር እንደማትችል ስላወቀች በትልቋ ኢትዮጵያ ውድቀት የምትመሰረት ትንሽ አገር – ትግራይን ለመፍጠር የሞት ሽረት ትንቅንቅ ላይ ነች። አገር እያወደመች፣ ንጹሐንን እየረሸነች፣ ሴቶችን እያስደፈረች  ኢትዮጵያን ሲኦል ለማድረግ ሸዋ ደርሳለች። የወያኔ እና የምዕራቡ ተንኮል ያልገባቸው ወይም ገብቷቸውም ግድ ያልሰጣቸው የከሸፉ ፖለቲከኞች ይህን አገር የማፍረስ እኩይ ተልዕኮ ለማሳካት – የፌዴራሊስቶች ግንባር በሚል ለሚወለደው አገር የአይን አባት ሊሆኑ አሰፍስፈዋል። ከወዲህ ማዶም የቆሙት ፖለቲከኞችም አደጋውን ማስቆም ቢያቅታቸው ‘እራሳችሁ ያዘጋጃችሁትን ሕገ-መንግስት ተጠቅማችሁ ትግራይን ይዛችሁ ጥርግ ማለት ትችላላችሁ፤ ብቻ እኛን አትንኩን’ የሚመስል ጥሪ በይፋ ለወያኔ ሲያቀርቡ እየሰማን ነው።
እንግዲህ ኢትዮጵያን መታደግ የሀገር ወዳድ ልጆቿ ሁሉ  እዳ ነው። ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተሰማራበት መስክ እና በቆመበት መሬት ሁሉ ከንፈር መጠጣውን አቁሞ አገሩን ለማዳን የአቅሙን እና የችሎታውን ሊረባረብ የግድ ይላል። አገራችን ከውስጥ በመጥፎ ልጆቿ፤ ከውጭ በታሪካዊ ጠላቶቿ ኩፉኛ ተቀስፋ ተይዛለች።
ኢትዮጵያ ሰው እየፈለገች ነው። ቢዘገይም ሀገር የማዳን እርብርብ ከሁሉም ኢትዮጵያዊ ይጠበቃል። አገር ወዳድ ምሁራን እና ልሂቃን ዝምታችሁን ስበሩ። ግራና ቀኝ ቆመን ጠአት ከመጠነቋቆል ይልቅ ይህን አደጋ ለመቀልበስ ይረዳል የምንለውን የመፍትሄ ሃሳብ በድፍረት ወደ አደባባይ በማምጣት ቢያንስ ጉዳቱን ለመቀልበስ ብንረባረብ ይበጃል። የሰላም በሮች ሙሉ በሙሉ ሳይጠረቀሙ በፊት ያሉትን እድሎች እንጠቀም። ኢትዮጵያ የከፋ አደጋ ውስጥ ነች።
እግዚያብሔር ኢትዮጵያን ይታደጋታ!
Filed in: Amharic