>

ሁለቱ የአብን አመራሮች ወግ...!!! (ወንድወሰን ተክሉ)

ሁለቱ የአብን አመራሮች ወግ…!!!

ወንድወሰን ተክሉ

የአቶ ክርስቲያን ታደለ ወቅቱን ያገናዘበ እይታና የባልደረባው ጋሻው መርሻ ወለፈንዲ እይታ!!
«ስሙ መከላከያ ስለተባለ ጦርነትን በመከላከል ብቻ ያሸንፋል ማለት አይደለም። ዝምታው እስከመቼ ነው? ሕዝቤ ሆይ አጥቂህን ማጥቃት ብቻ ያድንሃል!»
 የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባልና የአብን ከፍተኛ አመራር Christian Tadele Tsegaye   በማለት ጦርነቱ ያጋጠመውን ተግዳሮት በሚገልጽ ደረጃ ተናግራል።
በአንጻሩ ደግሞ ሌላኛው የአብን አመራራ Gashaw Mersha   «እነሱ ወደ አዲስ አበባ እኛ ወደ መቀሌ ለመድረስ እንታገላለን።ማን ቀድሞ እንደሚደርስ የምናየው ይሆናል። መቀሌን ታርጌት አድርገን እየታገልን አማራና አፋር ክልል የገባውን ወራሪ እንደ አዋሽ እዚሁ ሰምጦ እንዲቀር እናደርገዋለን። ጽናት የአሽናፊነት መንገድ ናት። እንጽና » በማለት አዲስ አበባን በመቀሌ ለውጠን እናሸንፋለን እያለ ነው።
፠  የወንድም ክርስቲያን እይታ፦
የክርስቲያን ታደለ እይታ ከመርህ አንጻርና መሆን ከሚገባው ድርጊታዊ እርምጃ አኴያ ትክክለኛ እይታ ነው። ላለፉት አራት ወራት ያስተጋባነውን ድምጽ ነው ክሪስ እየደገመልን ያለው። ሆኖም ክሪስ ማቅረብና መግለጽ የሚገባው ይህንን ማጥቃት ብሎ የገለጸውን ለመፈጸም እራስህ አዛዥ ስትሆን እንጂ አሁን ባለው የዘመቻ አመራር ጦርነቱ አራት ኪሎ ካለው አቢይ ትእዛዝ እየተሰጠ በሚካሄድበት ሁኔታ የሚተገበር አይደለምና ይህንን ክፍል ለምን ዘለለው?? ወይንስ አላስተዋለውም ወይ ብዬ ልጠይቅ እወዳለሁ።
ጦርነቱ ሀምሌ 13ቀን እንደተጀመረና የአማራ ክልል ክተት አዋጀ እንዳወጀ የአማራ ክልል በፌዴራሉና በመከላከያው እዝ ስር ሳይገባ የተቃጣበትን የወረራ ጦርነት በአግባቡ መክቶ ለማሸነፍ የሚያስችለውን የራሱ የሆነ እዝ -ማለትም ከሁሉም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቌማት ወታዳራዊ ባለሙያዎች፣የኢኮኖሚ ባለሙያዎች፣የአለም አቀፍ ግንኙነትና የሚዲያ ባለሙያዎች፣የሁሉም ፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ሲቪልና ወታደራዊ ደህንነት ባለሙያዎችን እና መሰል አባላትን ያቀፈ አንድ  ወታደራዊ ካውንሲል/ግብረኋይል ተቌቁሞ የጦርነቱን ዘመቻ በፍጹማዊ ነጻነት ይምረው- ይህ ሳይሆን ከቀረና አብንም ሆነ መላው የአማራ ህዝብ በአንድ ብአዴን/ብልጽግናዊ አመራር ስር ታቅፎ ጦርነቱ ከአራት ኪሎ በሚተላለፍ ትእዛዝ ባህርዳር እየተቀበለች የምትመራ ከሆነ ከውጤት ይልቅ ውድቀትና ውርደት ይጠብቀናልና የአማራ ክልላዊ መንግስት ይህንን አይነቱን አደረጃጀት ይመስርት እናንተም ይህንን እውን በማድረግ ደረጃ እንደ ቅድመ ሁኔታ አቅርባችሁ ግፊት አድርጉ እንጂ በጭፍን አትቀላቀሉ በሚል ሀሳብ አቅርበን ውድቅ የተደረገው በብአዴን ብቻም ሳይሆን በእነዚሁ በእኛ ባልናቸውም ጭምር ነው ።
ክሪስ ዛሬም ቢሆን ማጥቃትን ካልፈጸምን ማሸነፍን አንችልም ብሎ ሲያምን እሱ ማጥቃት አለብን ብሎ እሚያምነው በመንግስት አዋጊነት ለምን ወደ ማጥቃቱ አንሸጋገርም እያለን ነው  ያለው እንጂ ህባችንን በራስህ ግዜ ተነስተህ ተዋጋ እያለን አይደለም። ይህ ማለት ደግሞ  ህዝባችንና ታጣቂዎቻችን ተዋጋ/ተዋጉ  የሚል ትእዛዝ የሚሰጠውን አካል ሳያገኝ በራስ ተነሳሽነት ብቻ ተነስቶ ይዋጋል ብሎ ማሰብ ትልቅ ስህተት ነውና በዚህም ላይ ክሪስ ስታል ማለት ይቻላል። ከዚያ ይልቅ ክሪስ  ማድረግ ያለበትና ሊያደርግም የሚቻለው ነገር …እንደ መሪነቱ ይህንን የመሪነት ኋላፊነትን  በመውሰድና ተነሻነትን በመጨበጥ ህዝቡን ተዋግቶ ሊያዋጋ  የሚችል (እንደ የአማራ ህዝባዊ ኋይል/ፋኖ) አማራዊ አዋጊ  የጦር መሪ ያለውን ኋይል የመፍጠሩና  ይህንንም ኋይል ሕዝባዊ ድጋፍና ደጀን ያለው በማድረግ ጉዳዩን ወደፊት ወደ ሕዝብ በማምጣቱ ጉዳይ ላይ በርትቶ ቢሰራና ቢናገር ይበልጥ ውጤታማ ይሆናል።
፠ የጋሻው መርሻ እይታ
አዲስ አበባን በመቀሌ ለውጦ  እንቁልልጬ እያለ  እናንተ አዲስ አበባ ስትገቡ እኛ መቀሌ ገብተናል ብሎ ለመጮህ ያሰበ ጨቅላ ሀሳብ ሆኖ ነው የሚታየኝ። ከእንጭጭ ሀሳብነቱ ባሻገር ጭልጥ ያለ የብአዴን ብልጽግና ተራ ህዝብን ማስታገሻ ፕሮፖጋንዳ ሆኖ ነው የማየው። በዚህ ላይ እሱ ስለጠቀሰው የአፋርና አማራ ክልል ውስጥ ስለገባው ወያኔን ውጦ የማስቀረት ተራ ፉከራ በዚሁ ጦርነቱ አሁን ለደረሰበት ደረጃ ላይ እንዲደረስ ባደረጉት አመራሮች እና የእዝ ሰንሰለት ተጠቅሞ እንደሚፈጸም አድርጎ የመግለጹ ጉዳይ የልጁን የእይታ መጠንን ከማሳየት በዘለለ የሚያሳየን አመላካች መፍትሄን አናይበትም። (በነገራችን ላይ ጋሻውና ጣሂር መሀመድ የአማራን ልዩ ኋይል የአማራን ሕዝባዊ ኋይል ፋኖና የአማራን ሚሊሺያ ተጋድሎና ጀብድ እየገለጹ ልጆቻችንን ከማበረታት ይልቅ ከተሞቻችንን እየለቀቀ በመፈርጠጥ ሰሜን ሸዋ የደረሰውን መከላከያ ተብዬውን በማወደስና በማጀገን ላይ መጠመዳቸውን ግርም እያለኝ ያየሁት ጉዳይ ነው)
፠ በሁለቱም ዘንድ ያልታየው የጦርነቱ ገጽታ፦
ጦርነቱ ዛሬ ላይ ያለው ውጤት ብዙ መዘርዘር ሳያስፈልገው የውጊያ ስልት እስትራቴጂ እቅድ ወዘተ በሙሉ አካቶ በያዘ ሁኔታ የጦርነቱ አሁናዊ ደረጃና ውጤት የአመራር ውጤት መሆኑ ነው። የችግሮቻችን አስኴል መሪና አመራር ነው ማለት ነው።
ይህ ማለት ይህንን የጦርነት ይዘት ለመለወጥ ወሳኙ እርምጃ “ሀ” ተብሎ የሚጀመረው በአመራር ላይ ለውጥ በማምጣት ብቻ ነው።
ይህንን ወሳኝ ነጥብ ማንም ሲገልጸው አናይም!!!
፠ ሁለቱም ማድረግ የሚገባቸው፦
አማራው እንዴት አድርጎ የራሱን ሰራዊት በራሱ መሪ እየመራ ውጊያውን ማካሄድ እንደሚችል እያሳቡ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ላይ ሰፊ ዘመቻ መክፈት። አይሆንምን ትተሽ ይሆናልንም አስቢ እንደሚባለው ወያኔ በለስ ቀንቶት አቢይ መራሹን ብልጽግናን ቢገረሥስ ወይም አቢይ አማራን ጭዳ አድርጎ ከወያኔ ጋር ቢታረቅ የእነሱና የአማራ ህዝብ እጣፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል አስበው ያውቁ ይሆን?? ይህንን ዛሬ በማሰብ ከወዲሁ ህዝባችንን በማዘጋጀቱ ላይ መረባረብ ቢጀምሩ ለራሳቸውም ይሆናሉ።
ሁለቱም ማወቅ ያለባቸው ብአዴንና ብልጽግና ነገ ወይ በጦርነት አሊያም በድርድር አማራውን ጭዳ እንደሚያደርጉና ከሕዝብ ጋር ተፋጠው የሚቀሩት እነሱ መሆናቸውን አውቀው ከወዲሁ ከህዝብ ጋር የወገን አሰላለፍን እንዲያስተካክሉ ይጠበቅባቸዋል።
በተለይ ጋሻው ከፕሮፖጋንዳ ስራ እራሱን ሊያርቅ ይገባል።ይህንን ያህል ጭልጥ ያለ የብአዴን ብልጽግና ካድሬያዊ ስራውን ቀነስ አድርጎ ነገን እያሰበ ቢሰራ ይመከራል።አቢይ ብልጽግና ብአዴን sooner or later either they  liked or not ይጠፋሉ። የአማራ ሕዝብና ሀገረ ኢትዮጱያ ግን ይቀራሉ።
Filed in: Amharic