>

ከስህተቱ የማይማር ሰው የለም! - ከመሠረታችን እንጀምር! - ከታጠርንበት እንውጣ!  የሆድ-የሆዳችንን እናውጋ.. !!! አሳፍ ሀይሉ

ከስህተቱ የማይማር ሰው የለም! – ከመሠረታችን እንጀምር! – ከታጠርንበት እንውጣ!  የሆድ-የሆዳችንን እናውጋ.. !!!
አሳፍ ሀይሉ

በጭራሽ ከስህተቱ የማይማር ሰው የለም! ብዬ ሞራሌን አሰባስቤ መጣሁ። ማንሳት ስለፈለግኩት ቁምነገር እንጂ፣ ከምን እንደምጀምር አላውቅም። የመጨረሻ እውነት ብለን ከያዝናቸው ነገሮች ልጀምር።
ለምሣሌ በአሁኑ ወቅት “ክልል” ብለን እየጠራናቸው (እና ዓለምምም እየጠራቸው) ስላሉት የአስተዳደር መዋቅሮች የተወሰኑ እውነቶችን በማየት ብንጀምርስ? በጣም ጥሩ!
እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ ታሪክ ታይተው ተሰምተው የማይታወቁትን ሁለት ግዙፍ ክልሎች (ማለትም “አማራ ክልል”ን እና “ኦሮሚያ ክልል”ን) ቆርጦ፣ ቀጥሎ፣ ጠፍጥፎ፣ ከዚህም ከዚያም በዘርና በቋንቋ ፊሽካ አጠራርቶ የፈጠራቸው ወያኔ ነው።
በእርግጠኝነት የማስበው ወያኔ ኦሮሚያ እና አማራ የሚባሉ ግዙፍ ክልሎችን በመፍጠሩ በሠራው ስህተት ደግሞ ደጋግሞ ተፀፅቷል ብዬ ነው።
ዳግመኛ የአድራጊ ፈጣሪነት ሥልጣን ቢያገኝ፣ ከስህተቱ ተምሮ፣ እራሱ በዘር ማንዘር ከዚህና ከዚያ አጠራርቶ የሰፋውንና የፈጠረውን “ክልል” ወደየነበረበት ታሪካዊ ቁመና መልሶ እንደሚበታትነው አምናለሁ።
መለስ ዜናዊ በ1985 ላይ “አማራ አማራ” ብሎ ወትውቶ አልወጣለት ሲልና.. ሸዋን ከጎንደር፣ ወሎን ከጎጃም፣ ያንኖ ከዚያ እያጠራራ የአማራን ክልል ፈጥሮ ሁሉንም በአንድ ጎተራ ሊከትት መከራውን ሲበላ፣ ፕሮፌሰር መስፍን እውነታውን አፍርጠው ነግረውት ነበር፦ “አማራን አሁን አንተ አማራ አማራ ስትለው ፈጠርከው!” ብለው።
እንደማስበው እርሳቸው አማራን አሉት እንጂ፣ የአባባላቸው አመክንዮ ግን ለሁሉም የሚሠራ ነበር፦
“ወለጋውን ከአርሲ፣ ሐረርጌውን ከጉጂ፣ ሸዋውን ከባሌ፣ ከፋውን ከቦረና በቋንቋና በዘር ማንዘር ፊሽካ አጠራርተህ ኦሮሞ ኦሮሞ ስትለው አሁን አንተ ፈጠርከው!”
ማለታቸውም ነበር። ይህን ስናገር “A word is like a magic” ብለው የቃላትን ታላቅ ኃይል አምነው ቃላትን እያመለኩ የሚኖሩትን የሜክሲኮ ጥንታዊ የቶልቴክ ነገዶች አስታወስኩ።
በብዙ እምነቶችም ቃላት ለብቻቸው ተለይተው እንደ እግዜር አይመለኩ እንጂ ሁሉም እምነቶች ለቃላት ከፍ ያለ ሥፍራ እንዳላቸው እናውቃለን። የክርስትያኖች ቅዱስ መፅሐፍ እንኳ እግዜሩን ሲገልፅ “በመጀመሪያ ቃል ነበረ” በማለት ነው።
The word, the logos, the spiritual infinite power in an utterance that makes and unmakes existence! የፈጣሪ ቃል ሲነገረን “ይሁን አለ፣ እንደ ቃሉም ሆነ” እየተባለ ነው። ቃል ተዓምራዊ ኃይል አለው። ለበጎውም፣ ለክፋቱም የሚሠራ።
“ተው ክፉ አትናገር፣ የአፍህን እንዳይዝብህ!” ይላሉ አባቶች። “የሰይጣን ጆሮ ይደፈን!” ይላሉ ከአፍ የወጣችውን ቃል ሠይጣን ሰምቷት በእውን እንዳይከስታት! የወያኔም፣ የመለስም ነገር እንደዚያ ይመስለኛል!
በወያኔ “አማራ ክልል” ተብሎ የተፈጠረው ክልል በታሪክ “አማራ ነኝ፣ እና አንድ ላይ አማራ ተብዬ መተዳደር አለብኝ” ብሎ የማያውቀውንና፣ ከጎንደሬነቱ፣ ከመንዝነቱ፣ ከመርሃቤቴነቱ፣ ከይፋትነቱ፣ ከጎንደሬነቱ፣ ከጎጃሜነቱ፣ ከዚያም አልፎ ከየጁነቱ፣ ከወረሼህነቱ፣ ወዘተ ውጭ ሌላ ጋራና ሸንተረር ተሻግሮ አማራ ዘርማንዘርና ቋንቋን አሰናስሎ እንደ ክልልም ሆነ ግዛት አሊያም አንድ ክፍለ ሀገር ተዳድሮም ሆነ ፈልጎም የማያውቀውን በየራሱ መስክ የተሰበጣጠረ ሕዝብ ነበር።
መለስ ዜናዊ መጥቶ ገና ለገና ለፈጠረው የጨቋኝ – ተጨቋኝ እና የብሔር ብሔረሰብ ትርክት እንዲስማማለት ሲል፣ ጧትና ማታ አማራ አማራ አማራ እያለ ሲለፍፍ፣ ቃሉ ይዞበት ወይም ይዞለት፣ ፕሮፌሰሩ እንዳሉት፣ ያልነበረውን “አማራ ክልልን” ብቻ ሳይሆን “አማራነትን”ም ፈጠረው። ኦሮሚያነትንም፣ ኦሮሞነትንም፣ ኦሮሞ ክልልነትንም አብሮ ፈጠረው። እና እንደ ሜሪ ሼሊ Frankenstein ራሱ በፈጠረው ጭራቅ ተበላ!! እውነታው ይኸው ነው።
እና በመነሻዬ እንዳልኩት ከሥረ መሠረቱ የተለየ እድገት መሠረት እንደሌለው ቤት ነው። አያድግም። በላዩ ላይ ግዙፍ ነገር አታንፅበትም። ረጋ ሠራሽ ነው። ሩቅ አያሻገርም። የፀና፣ በዘመን ሂደት የተፈተነና ነጥሮ የወጣ እውነተኛ መሠረት የለውምና። ከበቀለበት አፈር፣ ከውሃው፣ ከሥሩ የተነቀለ ተክል፣ የፈለገ ውሃ ብታጠጣው ግንድ ሆኖ እንደማይበቅለው ማለት ነው።
በኢትዮጵያችን የግማሽ ክፍለዘመን የለውጥ ሂደቶች በስፋትና ተደጋግሞ የታየው ችግርም፣ ይኸው የፖለቲካና አስተዳደራዊ ለውጦች ለራሱ ለሕዝባችን ታሪካዊና ነባራዊ ሁኔታዎች ባዕድ ሆነው በመገኘታቸው ምክንያት የተከሰተ ነው።
የጥንት አባቶቻችን በተረት ሲናገሩ፦ “ሁልህም ወደየዘርህ ሲባል፣ አክንባሎ ወደ በረት፣ መሶብ ወደ ሠርዶ፣ ሸክላም ወደ አፈር ገባ” ይላሉ። አክንባሎው እበት ስለሚለቀለቅ መሰለኝ ወደ በረት የተመለሰው። አጥንቱን ቢቆጥር ምናልባት ከሸምበቆ (መቃ) የተሠራ ስለሆነ ነው ዘሩን ቆጥሮ ኩሽናውን ጥሎ፣ እንደ መሶቡ፣ ወደ ሰርዶ መግባት የሚቀርለት አይመስለኝም።
ምጣዱም ሸክላ ነውና ዘሩን ቆጥሮ ተነቅሎ ወደ አፈር ገባ። የሸክላ ድስቱም ወደ አፈር መግባቱ አይቀርም። አባቶችህ በነገሩህ ላይ አመክንዮአቸውን ተከትለህ ስትጨምርበት፣ ሠፌዱም ዘሩ ሰንበሌጥ ነውና ተበትኖ ወደበቀለበት ጨፌ መግባቱ የሚቀርለት አይመስለኝም።
ጉልቻውም ወደ ተፈነቀለበት ተራራ ወይም ወንዝ ሊገባ ነው። ኧረ ጉድ ነው? ይሄ ነገር ማለቂያም የለውም! ቤቱም ጭቃው ወደ አፈር፣ አሸዋ ግርፉም ረግፎ ወደ ባህር ዳርቻ፣ ጭዱም ወደ ማሳ፣ የጎጆውም ክዳን፣ ምድጃውም፣ ማጀቱም፣ ቤቱም፣ ሁሉም ነገር እንዳልነበር ሆኖ ሊቀር ነው። እንጀራም አይጋገርም፣ ወጥም አይሠራም፣ ቤትም የለም፣ ውድመት፣ እርዛትና ችጋር ነው ውጤቱ – ሁልህም ወደየዘርህ ግባ የሚል ጨዋታ መጨረሻው!
አስበኸዋል? የጥንት አባቶቻችንን በዘመን የተፈተነ ወርቃማ ጥበብ? አስተውለኸዋል? እንዴት በቀላሉ ተረት  አስመስለው እንዴት ከፍ ያለ ግዙፍ ጥበብን በቃል እንደሚያወርሱን?! እጅግ ይደንቀኛል!
“ምከረው፣ ምከረው፣ መከራ ይምከረው” ነው የሚሉት አባቶቻችን። የተኖረና በዘመናት በትውልዶች ተፈትሾ የተረጋገጠን ከራስህ ምድርና ሕዝብ የበቀለን የጥበብ ቃል አልቀበልም ብለህ ስትደርቅ፣ መከራ ይመክርሃል። መቼም ሰው ሆኖ የማይመከር የለምና።
ለማንኛውም ወያኔውም ሆነ የወየነው ሁሉ፣ …
“አማራነት” የሚል “ነት” የሚል ቅጥያ የለጠፈ አዲስ በልኩ የተሰፋለትን የተውሶ ማንነት ለመፍጠር መከራውን የሚበላውም ሁሉ፣ ….
በባሌና በቦሌ ከዚህና ከዚያ ያሉ ሕዝቦችን በቋንቋና ዘር ፊሽካ አጠራርቶ በተበጀለት ትረካ ወርድና ቁመና ልክ ሁሉንም በጨፌ ዙሪያ አደራጅቶ ኦሮሚያ የሚል የ”ያ” ቅጥያ ያለው ያልተኖረ የተውሶ ማንነትን ለመከሰት መከራውን የሚበላውም ሁሉ፣ …
እና ሌላውም፣ ሁሉም በቃል አልመከር ብሎ በመከራ እየተመከረ ያለው የሀገራችን የዘር አነብናቢ “ልሂቅ”፣ እስካሁን ከደረሰብን አጠቃላይ መከራ ካልተማረ፣ ከእንግዲህ ወዲያ በእኛ ዘመን ይማራል የሚል ተስፋም አይኖረንም።
በተለይ በተለይ “ትግራዋይነት” የሚባል “ዋ” እና “ነት” የሚሉ ባዕድ ቅጥዮችን ለጥፎ አዲስ የቅጥፈትና ለቅስፈት የሚዳርግ ማንነት ለመፍጠር መከራውን እየበላ ያለው የወያኔ የልሂቃን ቡድን፣ ካሳለፈውና በገዛ እጅ ሥራው ከደረሰበት ታላቅ መከራ ተምሮ ካልወጣ፣ ወደፊትም የመማር ተስፋው አጠያያቂ ነው።
በእኔ እምነት ወያኔ ሕገመንግሥቱ ሕገመንግሥቱ እያለ የሚደርቀው፣ ሕጋዊ መሠረትና ቅቡልነቱን ላለማጣት ነበር። ወይም ነው። የብሔር ብሔረሰብ ምናምን የሚለው ቀረርቶና እንቶ ፈንቶውም አጋሮችን ለማግኘት የሚለፍፈው እወጃ ነው።
ውስጡን ዘልቆ ከውጫዊው እውነታ ጋር በሚታረቅ መልኩ ለመረመረው ግን፣ በእኔ አመለካከት፣ ህወኀትም፣ እንደተቀረው ኢትዮጵያዊ ሁሉ፣ ካለውና ተሞክሮ ከከሸፈው፣ ሰውና ወገን ሆነን ሳለ እንደ ጭራቅ ካበላላን ያለፈው (የ60ዎቹ ሶሻሊዝም ተፅዕኖም ካባባሰው) የብሔር ብሔረሰቦች ጡሩንባው ወጥቶ፣ የተሻለና ለሁሉም፣ ለሁላችንም የሚበጀንን ሥርዓት ለመገንባት ዓይኑን የሚያሽ አይመስለኝም።
ይህን የምለው ወያኔ የቱንም ያህል በአስተሳሰቡ ቢደርቅ፣ ያደናቀፈው ድንጋይ ደጋግሞ እስኪያደናቅፈው ድረስ፣ ጨርሶ ይበድናል የሚል እምነት ስለሌለኝ። በነገራችን ላይ፣ አጠቃላይ ሥርዓቱ የተመሠረተበት የዘርማንዘር መሠረት የተበላሸ ሆኖ ነው እንጂ፣ ወያኔ በ40 ዓመት ታሪኩ ራሱን የለዋወጠውን (እነሱ ተሃድሶ የሚሉትን) ያህል፣ ራሱን የለወጠ አካል ያለ አይመስለኝም።
ይህንን practical necessityውን አገናዝቦ ራስን የመለወጥ አቅም፣ በሌላ ከዘርማንዘር በተላቀቀና በሚሠራ system of governance ላይ መመሥረት ከቻለ፣ እና ሁላችንም ከቻልን፣ then የተሻለ ነገን የማናይበት ምክንያት አይታየኝም።
በአጠቃላይ የያዝነውን ነገርና አቋም በቅርቡ የተፈጠረና ያልሠራ ተሞክሮ መሆኑን ዘንግተን፣ እና እንደ ዘለዓለማዊ ቆጥረን፣ ጎራ ከፍለን ከመተላለቅና ለቀጣይ ሌላ ዙር የትውልድ እልቂት መዘጋጀት አይጠቅመንም። ለማንኛችንም አይጠቅምም ይህ።
ይልቁንም፣ በመከራ ተደጋግመን በመመታት ከምንመከር ይልቅ፣ ከጥበብ ቃል ቆንጥረን፣ በጥበብ ቃል መክረን፣ የነገውን አስበን ሁላችንም ከገባንበት የጥፋት አዙሪት መውጣት ብንችል፣ ራሳችንንም፣ ሀገራችንንም፣ ትውልዳችንንም፣ በዓይነት በዓይነቱ ከፊታችን ተሰድረው ከሚጠብቁን ቀጣይ የመከራ መዓቶች እናድናለን። የሚል ተስፈኝነት ያልተለየው ፅኑ አመለካከት አለኝ።
“ሰው የሚማረው ከሁለት ነገር ነው፣
አንድም ከፊደል ሆሄ
አሊያም ከመከራ ኤሎሄ።
አንድ ቃል ከፊደል ገበታ “ሀ” ብሎ፣
አሊያም ከመከራ መዝገብ “ዋ” ብሎ፣
አንድም ከህይወት ሣር “ሀ” ብሎ፣
አሊያም ከፍዳ አሣር “ዋ” ብሎ።”
– ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን
  (ከማስታውሰው)
የፈጣሪ ፀጋ ከሁላችን ጋር ይሁን።
አበቃሁ።
_______________________
ማስታወሻ፦
ከላይ ባቀረብኩት ፅሑፍ ውስጥ አላግባብ በተጠቀምኳቸው ቃላት ወይም ኃይለቃላት የተነሳ ቅር የሚለው ሰው ቢኖር ከልቤ ይቅርታ እጠይቃለሁ። ሀሳቦችን በቀጥታ ወይም አስረግጬ ለመግለፅ በመሞከር የተፈጠረ ነው። እንጂ ሆነ ብዬ ያደረግኩት አይደለም። አይሆንምም። በመጨረሻም ጊዜ ሰጥታችሁ ሀሳቤን በፅሞና ለምታነቡ (እና አስተያየት ለምትሰጡ) ሁሉ ምሥጋናዬ ይድረሳችሁ።
Filed in: Amharic