>

ሸኔ  ወደ ስልጣን ከመጣ በቀሉ የሚከፋው  በኦሮሞ ህዝብ ላይ ነው.....!!!! (የኦነግ መስራች ዲማ ነገዎ(ዶ/ር)) 

ሸኔ  ወደ ስልጣን ከመጣ በቀሉ የሚከፋው  በኦሮሞ ህዝብ ላይ ነው…..!!!!

የኦነግ መስራች ዲማ ነገዎ(ዶ/ር) 

አዲስ አበባ፡- የኦሮሞን ህዝብ ለማደናገር ሸኔ በሚል የተደራጀው አሸባሪ ቡድን እድል ተሰጥቶት ወደ ስልጣን ከመጣ በቀሉ የሚከፋው በዋናነት በኦሮሞ ህዝብ ላይ ነው። የሕወሓትና የሸኔ ጥምረትም የስም ልዩነት ካልሆነ በስተቀር ሁለቱም አንድ ናቸው ሲሉ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ጉዳይና ደህንነት ቋሚ ኮሚቴ አባል እና የኦነግ መስራች የሆኑት ዲማ ነገዎ(ዶ/ር) አስታወቁ።ዶ/ር ዲማ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጡት አስተያየት፣ አሸባሪው ሕወሓትና ሸኔ የስም ልዩነት ካልሆነ በስተቀር በተግባርም በዓላማም የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች በመሆናቸው ሁለቱን የተለያዩ አካላት አድርጎ ማየት አይገባም።

አሸባሪው ሕወሓት ዛሬ ህዝቡን ለማደናገር የኦሮሞ ህዝብ ወገንተኛ ለመምሰል ከፍተኛ መፍጨርጨር እያደረገ መሆኑን ያነሱት ዶ/ር ዲማ፣ ዳሩ ግን በታሪክም ሆነ በተግባር ወደኋላ መለስ ተብሎ ከተቃኘ ቡድኑ በማስተር ፕላን ምክንያት በርካታ የኦሮሞ ወጣቶች በጠራራ ፀሐይ ያለምንም ርህራሄ በጥይት የፈጀ፣ ይሄ ሳያንስ የእሬቻ በዓል ለማክበር የወጡ የኦሮሞ ንጹሃንን በመጨፍጨፍ ጥቁር ጠባሳና ዘግናኝ ድርጊቶችን ጥሎ ያለፈ ቡድን መሆኑን አስታውሰዋል ።

የሽብር ቡድኑ ፍላጎት ትናንትም ዛሬም ኦሮሞን በመስበር የኦሮሞን ሀብት መውረስ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ዲማ፣ ለዚህ ዓላማ ማሳኪያም እውነተኛ የኦነግ ታጋዮችን በመግደል እንዲሁም በማሰር በሕይወት የተረፉትን ከአገር በማባረር ከአሥር ዓመታት ወዲህ ደግሞ ተላላኪውን በማደራጀትና በኦሮሞ ስም አምሳያውን ቡድን በማቋቋም ኦሮሞን የማደናገር ሥራ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

ቡድኑ ኦሮሞን ለማደናገር በኦሮሞ ስም ሸኔ በሚል ስም ተደራጅቶ መምጣቱ ምናልባት ለማያውቁት ለአንዳንዶቹ ማደናገሪያ ቢሆንም እውነታው ግን የሕወሓት ትልቁ ዓላማ እንደ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ በተለየ መልኩ ደግሞ የስልጣኑን እድሜ ያሳጠረውን ኦሮሞን ህዝብ ክፉኛ ለመበቀል መሆኑ መታወቅ አለበት ያሉት ዶ/ር ዲማ፣በቡድኑ አምባገነናዊ አገዛዝ በግፍ ያልተገደለ፣ያልተሰቃየና አገር ጥሎ ያልጠፋ ብሔር ባለመኖሩ የቡድኑ ዳግም ወደ ስልጣን የመመለስ ቅዠት ከንቱ ለማድረግ በጋራ መቆም ጊዜው አሁን ነው ብለዋል።

አሸባሪው ሕወሓት ትንሽ ቀዳዳ አገኝቶ ወደ ስልጣን የመመለስ እድል ካገኘ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አንገቱን ደፍቶ የሚኖርባት የሰቆቃ ምድር እንደምትሆን የተናገሩት ዶክተር ዲማ ህዝቡ አገሩን ከምስቅልቅል፤ ራሱንም ከስቃይ ለመታደግ ብቸኛው አማራጭ በጋራ መታገል መሆኑንም አስምረውበታል።

በመጨረሻም የሽብር ቡድኑ በሸረበው ሴራ የህይወት መስዋዕትነት በመክፈልና በመፈናቀል እንዲሁም በውጭ ኃይሎች ጫና ሳይንበረከክ የጋራ ጠላቶቹን በአንድነት በጽናት እየተፋለመ ላለ ለኢትዮጵያ ህዝብም ምስጋና አቅርበዋል።

ዋቅሹም ፍቃዱ

Filed in: Amharic