>
5:29 pm - Sunday October 11, 5187

የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ አሳድሯል የተባለውን ጫና የሚያወግዝ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሄደ ----DW-

የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ አሳድሯል የተባለውን ጫና የሚያወግዝ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሄደ
DW

ቁጥራቸው የበዛ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያ  አሜሪካውያንና ኤርትራዊያን በጋራ የተሳተፉበት የተቃውሞ ሰልፍ  በዋሽንግተን ዲሲ በነጩ ቤተመንግሥት ደጃፍ ተካሄደ።
እሁድ ኅዳር 12/2014  ዓ.ም ከሰዓት በኋላ “ይበቃል !” በሚል መሪ ቃል  ከኋይት ሃውስ ፊት በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የተገኙ ሰልፈኞች፤ “ዩናይትድ ስቴትስ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ እያደረሰች ነው” ያሉትን ጫናና ጣልቃ ገብነት አውግዘዋል።
በተጨማሪም አሜሪካ የኢትዮጵያ መንግሥት በአሸባሪነት ለፈረጀው ህወሃት እያሳየች ነው ያሉትን ወገንተኝነት እንድታቆም ያሰሙት በነበረው መፈክር ጠይቀዋል። የሰልፉ አስተባባሪዎችና ተሳትፊዎችም ሰልፉ የተጠራበትን ዓላማ ማሳካቱን ተናግረዋል።
ተመሳሳይ ዓላማ ያለው  ሰላማዊ ሰልፍ ከዋሺንግተን ዲሲ በተጨማሪ በመላ ዓለም በሚገኙ ከ20 በሚበልጡ ከተሞች እንደተካሄደ አስተባባሪዎቹ ያሰራጯቸው የበይነ-መረብ መልዕክቶች ያሳያሉ ።
ዩናይትድ ስቴትስ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ውጥረት ከጠመንጃ ይልቅ ፖለቲካዊ መፍትሄ እንደሚያስፈልገው በተለያዩ  ጊዜያት ስትገልፅ ቆይታለች።
በቅርቡም በጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የተናገሩት አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ  “በኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ሰራዊት እና በኤርትራ  መከላከያ ሰራዊት የተፈጸሙ የኃይል እርምጃዎችን እናወግዛለን ።በህወኻት የተፈጸሙ የኃይል እርምጃዎችንም እናወግዛለን ።ህወኻት ከትግራይ ክልል ውጭ ያስፋፋውን ጦርነት እናወግዛለን ።ህወኻት ከአፋር እና አማራ ክልል ስፍራዎች ለቆ መውጣት አለበት። ህወኻትና የአሮሞ ነጻ አውጭ ግንባር ወደ አዲስ አበባ የሚያደርጉትን ግስጋሴ በአስቸኳይ እንዲያቆሙ ጥሪ እናቀርባለን ’’ ማለታቸው ይታወሳል።
Filed in: Amharic