>

የኃያላን ሀገራት ጣልቃገብነት አዝማሚያ! (አሳፍ ሀይሉ)

የኃያላን ሀገራት ጣልቃገብነት አዝማሚያ!
=አሳፍ ሀይሉ

እንደማስበው በአሁኑ ሰዓት የአይተ ኢሳያሷ ኤርትራ ጦሯን እንደ ከዚህ ቀደሙ ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት ብትሞክር፣ የአሜሪካና ኔቶ መቅሰፍታዊ በትር ሰለባ ትሆናለች የሚል ጠንካራ ግምት አለኝ!
በኢትዮጵያም ጉዳይ ቢሆን አሜሪካ ጠበቅ ያለ (ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትንም ጭምር ያካተተና ቀነገደብም ያለው) እርምጃ በአብይ መንግሥት ላይ ብትወስድ፣ ከዚያ በኋላ የሚነሳው አሜሪካ ትክክል ነች ወይስ አይደለችም? የሚለው ጥያቄ ምንም የሚፈይደው ነገር የለም።
የአብይን መንግሥት ለመርዳት የሚከጅሉ ሀገሮች ቢገኙ እንኳ በፍጥነት cost-benefit analysisሳቸውን በፍጥነት ለማስላት ይገደዳሉ።
ከዚያ የሁሉም በዓለም ላይ ያለ ሀገር ጥያቄ የሚሆነው  “እኔ ለአብይ አህመድ መንግሥት ስል ከአሜሪካ (እና ከኃያላን አጋሮቿ) ጋር ጦርነት ውስጥ መግባት እፈልጋለሁ ወይ?” የሚለው ነው።
እንኳን እንደኛ ሀገሯን የድሃ ድሃ ሀገር ብለው ከአሜሪካ ጋር ሊዋጉ፣ ብዙ የተለያየ የሀብት ምንጭ ሊሆኗቸው በሚችሉ እንደ ኢራቅና ዩጎዝላቪያ ወይ ሊቢያና አፍጋን በመሠሉ ሀገሮች ላይ እንኳ ደፍሮ ከአሜሪካኖችና አጋሮቻቸው ጋር አጉል የብረት ሰፋጣ መግጠም የሚፈልግ ማንም ሀገር የለም። አይኖርምም።
ዩጎዝላቪያ ላይ፣ እና ድጋሚ አፍጋኒስታን ላይ፣ ሁለት ጊዜ፣ አሜሪካ ከቤልግሬድና ከካቡል የውጭ ሀገር ዲፕሎማቶችና ዜጎች በሙሉ ለቀው እንዲወጡ መልዕክት አስተላለፈችላቸው።
ቻይናዎች አንወጣም አሉ። ቀነገደብ አስቀመጠች። አሁንም አንወጣም አሏት። በመጨረሻ ከከተማዎቹ ጋር አብራ የቻይናን ኤምባሲዎች በአውሮፕላን ሚሳይሎች አመድ አደረገቻቸው። በካቡልም በቤልግሬድም ቻይና ዲፕሎማቶች ሞተውባታል። ከድንፋታ በስተቀር ያመጣችውም፣ ልታመጣጠየምትችለውም ነገር የለም።
በሶርያ ላይ ሩሲያ አዘናግታና አመቺ ጊዜ ጠብቃ ያደረገችው ይሄንኑ ነበር። ሩሲያ በሶርያ መግባት እንደሌለባት ሁሉም አምነዋል። ግን ለሶርያውያን ብለው ከሩሲያ ጋር ጦርነት ይገጥማሉ? cost-benefitቱ እና ጣጣው፣ ያንን አያስመኝም። ስለዚህ የቻሉትን የጥጋብ ድርጊት እያደረጉ ግን ከሩሲያ ጋር ፀብ ላለመጫር ይጠነቀቃሉ።
በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ሩሲያ በሳዳቷ ግብፅ ጉዳይ በመጨረሻ ሰዓት ኒውክሊየሯን መዛለች። በኩባ ጉዳይ። እና በተለያዩ አስጊ ጉዳዮች። እና ጠቡን አስወግደው በሠላም ጨርሰዋል።
አሁን ያ የቀዝቃዛው ጦርነት ርዕዮተ ዓለማዊ መሳሳብና መገፋፋት ቀርቷል። አሁን የጥቅምና ጉዳት ስሌት ነው ሀገሮችን የሚመራቸው። ዩክሬን ላይ ሩሲያ ጦሯን ብታዘምት፣ አሜሪካ እዚያ ድረስ ሄዳ፣ አውሮፓዎች ደሞ ደጃፋቸው ላይ ከሩሲያ ጋር አጉል ጦርነት ውስጥ ለመግባት ይፈልጋሉ?
No! አያደርጉትም! ያስፈራራሉ! ይደነፋሉ! ግን ሩሲያ ገፍታ ብትወርራት ዩክሬንን ብሎ  ጠንቀኛ ጦርነት ውስጥ መግባት worth አያደርግምና ያፈገፍጋሉ!
በታይዋን ጉዳይ፣ በሌሎችም ሀገሮች የጣልቃገብነት ጉዳዮች ላይ የሀገሮች አቋም ተመሣሣይ ሎጂክ ነው የሚከተለው።
ዓለማቀፍ ህግ በበኩሉ ከለላ አይሆንም። ማንንም ለማዳን አይጠቅምም ማለት ይቻላል። በመርህ ከመጠቀስ ውጪ፣ እና ሲፈለግ ከመቀንቀን ውጪ የኃያላኑን ተሞክሮ መሠረት በማድረግ የሚፃፍ አስገራሚ ፍርደጉልቤ ሥርዓት ነው።
ስለዚህ በአሁኑ ወቅት ይህን ዓለማቀፍ እውነታ ተረድቶ፣ የአብይ መንግሥት ጠባይ መግዛት የግድ ይለዋል። ጠባይ ገዝቶም እስካሁን ከተነከረበት ደም መፋሰስ እጁን ታጥቦ ይወጣል ወይ? አጠራጣሪ ነው። አይመስለኝም።
ግጭታችንንና ጦርነታችንን እስካልፈለጉ ድረስ፣ እና በኢትዮጵያ ሠላምና አንድነት ላይ ወሳኝ interest አለን ብለው ካመኑ ግን፣ በቀናት ውስጥ የአብይን መንግሥት ደሰማምሰው የፈለጉትን አስተዳደር ለማስፈን ከተነሱ፣ ከእግዜሩ በቀር  ሊከለክላቸው የሚችል አንዳችምጠምድራዊ ሀይል የለም።
ይህን ስል በውስጤ ይህ fair ነው እያልኩ አይደለም። ብሽቀትም ሳይሰማኝ ቀርቶ አይደለም – በሀገሮች እኩል አለመሆን።
ነገር ግን እውነታውን የመቀበል ጉዳይ ነው። በበኩሌ እውነታውን 100% አውቄው እቀበለዋለሁ። እውነታን መቀየር የሚቻለው መቀየር የሚቻልበት ተጨባጭ መንገድ ካለ ብቻ ነው። ከሌለ መጋጋጥ ብቻ ነው ትርፉ። እና አወዳደቅን ማክፋት።
እንደማምነው በአሁኗ ቅፅበት ኃያላኑ በእኛ ጉዳይ ይህን ያህል አላመረሩም። cost-benefitታቸውን እያሰሉ ነው። ውጤታማውን መንገድ እያጠኑና እያደረጁ ነው። የጎረቤት ሀገራትንና የአፍሪካን ግብረሀይልም በትብብር ሊያሰማሩ ያስቡ ይሆናል።
እስከዚያ በራሳችን ሠላምን መፍጠርና ከጦስ መዳን እንችላለን። አለዚያ ግን ከሊቢያ በመቀጠል ቀጣዩ አፍሪካዊ ታሪክ በኢትዮጵያችን ላይ መደገሙ አይቀሬ ይሆናል።
እውነታው ይኸው ነው።
ፈጣሪ ሀገራችንን አብዝቶ ይባርክ።
Filed in: Amharic