>

የዲፕሎማቶቹ ፅዋ ማህበር...!!! (ግዛው ለገሰ)

የዲፕሎማቶቹ ፅዋ ማህበር…!!!

ግዛው ለገሰ

ፕሮፌሰሩ የሰበሰቧቸው ተሳታፊዎች በጠቅላላ ባይባል እንኳ አብዛኞቹ መንግሥት፣ በተለይም ደግሞ አብይ አህመድ እንዲወገድ የሚፈልጉ ናቸው። ይህ ፍላጎታቸው የአምባሳደር ብርሃነን አንዳንድ ቅጥ ያጣ ቅጥፈት እንደወረድ እንዲያምኑና በጥያቄ እንዳይፈትኑት ጋርዷቸው ይታያል።
እሌን ግን የዚህ ማህበር ቋሚ አባል እንዳልሆነች ያስታውቃል። በሰሞኑ ክስተት፣ ቤቷ በመበርበሩ የተጋበዘች ይመስላል፤ “የተገፋውን ሁሉ ወዳጅ አድርጎ እንደመሣሪያ የመጠቀም” ስልት የራሱ የህወሓት ክህሎት ነው። ፕሮፌሰሩ ገና ስትገባ “ኦ . . . ሰሞኑን ቤቷ የተበረበረው እሌኒ ገብታለች” እያሉ ሲያሽቃብጡ፣ በኋላም ብርሃነ በወሬው መሃል ስሟን አነሳ መሰለኝ፣ ፕሮፌሰሩ “ያው ስምሽ ስለተነሳ የምትይው ነገር የለም?” እያሉ በድጋሚ ሲያሽቋልጡ ነው እሌኒ ከጦርነቱ በኋላ ስለሚሆነው ያሳሰባትን ስለ “ማርሻል ፕላን” የጠየቀችው።
ይህን ስል አብይ ላይ ወይም መንግሥት ላይ ተቃውሞ ሊኖራት አይችልም እያልኩ አይደለም፣ ለውጥ ያስፈልጋል ብላም ታምን ይሆናል። ግን እየተደፈደፈባት ያለው ኃጥያት ባስ ያለ ይመስለኛል። [ምናልባት ሰሞኑን የደረሰባት ነገር ባይደረግ ኖሮ እዚህ ቦታ ትገኝ ነበር? እንዲሁ ለማባያ እንዲሆን ነው።]
ይህ የዲፕሎማቶች ማህበር ተራ ማህበር አይደለም። ከዚህ ማህበር የሚፈልቀው ሀሳብ በተለይ የኃያላኑ ምዕራባዊ ሀገራት መሪዎች የትኛውም ፖለቲካዊ ውሳኔ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳድራል። በሌላ በኩል የፕሮፌሰሩ የሰላም ኮሚቴ አለ። በቪዲዮ ላይ እንዳየነው ብዙ እውቅ ሰዎችን፣ ለሰላም የሚተጉ ግለሰቦችን የያዘ ኮሚቴ ይመስላል (ሰዓሊ ገብሬም ይገኙበታል)። ፕሮፌሰሩ በዚህ ቪዲዮ ላይ በስብሰባው የተሳተፉ የሰላም ኮሚቴው አባላት መናገር እንደማይችሉና የዓለማቀፍ ዲፕሎማቶቹን እና ተጋባዦቹን ሀሳብ መስማት ብቻ እንዳለባቸው አጥብቀው አስገንዝበዋል – የኮሚቴው አባላት ገና ብዙ ሥራ እንደሚጠብቃቸውም ገልፀዋል። የዚህ የሰላም ኮሚቴ መጨረሻ ምን ይሆን?
በነገራችን ላይ ይህ ቪዲዮ እያንዳንዱን ተሳታፊ በወንጀል የማስከሰስ አቅም ያለው ይመስለኛል። ሆኖም የሚያሳስበኝ ፕሮፌሰሩ ተመሳሳይ ዲፕሎማቶችን ሰብስበው አብይን ወይም ሌላ ተወካይ ባለስልጣንን ጋብዘው አነጋግረው ቢሆንስ? ቪዲዮውን ማን አወጣው? አብይ የዘመተው ይህን ቪዲዮ ካየ በኋላ ይሆን እንዴ? ወይስ ስብሰባው ከዘመተ በኋላ ነው?
ይህ ቪዲዮ ይፋ ሲወጣ ከውጤቶቹ መካከል አንዱ የፕሮፌሰሩ እና የሰላም ኮሚቴያቸው ክሬደቢሊቲ ዱቄት መሆን ነው። ይህ እንዲሆንስ የሚፈልገው ማነው? [ሆ! ቢበቃኝስ!]
[በሌላ ነገራችን ላይ፣ ጥቁሩን ተሳታፊ/ዲፕሎማት አላወኩትም፤ እስኪ ጠቁሙኝ! (“ጥቁር” ማለቴ በሌላ እንዳይተረጎምብኝ – አደራ!!)]
Filed in: Amharic