ጎዳና ያእቆብ
*…. ጥሩ ማለት ግን ምንድነው? የሚለካውስ በምንድነው? እኔ እስገሚገባኝ ጥሩነት የሚለካው በአካሄድ (means) እና በውጤቱ (end, goal) ነው።
ኢትዮጵያን የመፍረስ አደጋ ውስጥ የከተታት መዋቅራዊና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ሆኖ ስላ አንድ የብሔር ክልል አዋልደናልና እንኳን ደስ አላችሁ (አለን) የሚለው አብይ አህመድ ዘምቻለሁ አለና አመስግኑ ስሉኝ ይገርመኛል።
የአብይ አህመድ ዘመቻ የብሔር ፌደራሊዝምን ያግዳል ወይ? የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት ይጠብቃል ወይ? አንቀፅ 39ኝን ያግዳል ወይ? ዜጎችን እንደ ዜጋ በሁሉም የኢትዮጵያ ግዛት ያከብራል|ያስከብራል ወይ? ከአቃፊና ታቃፊነት ያወጣል ወይ?
ከዚህ ያነሰ መብለጭለጭ ለኔ የድጋፍም ይሁን የተቃውሞ ምንጭ ሊሆንልኝ አይችልም።
በፓሊሲ የተደገፈ ሂደት እና ውጤት እንጂ የመግለጫ ጋጋታ እኔን ወደግራም ወደ ቀኝም ዝንፍ አያደርገኝም።
አብይ አህመድ የፖሊሲ ለውጥ አድርጎ ይህንን ከፋፋይ ህገ መንግስት ወይ አርቆ (አሻሽሎ) ካልሆነም ሙሉ ለሙሉ አግዶ ኢትዮጵያን ከጥፋትና ከመፍረስ አደጋ ቢያድናትም እንኳን በማንነታቸው ምክንያት፣ በአማራነታቸው ምክንያት ለታረዱ ህፃናት፣ ሆዳቸው ለተቀደደ ነብሰ ጡሮች፣ እቤት ውስጥ ታጉረው ከነ ህይወታቸው ለተቃጠሉ አዛውንትና ባልቴቶች፣ ለትምህርት ወጥተው ለቀሩ ወጣቶች ህይወት እና እንግልት የወንጀል ተጠያቂነት ሲመጣ እንደ ወንጀል ማቅለያ ይያዝለት እላለሁ እንጂ ከተጠያቂነት አይድንም።
አሁን ላይ ለአብይ አህመድ እና በዙሪያው ላሉ ካድሬዎች የቀረችኝ አድንቆት የምትመስል ነገር ብትኖር ከዚህ በኃላ ምን መልካም ነገር ሰርተው እንደ ወንጀል ማቅለያ እንውሰድላቸው የምትለው ብቻ ናት።
መልካም ስራ የምለው ስር ነቀል እና መወቅራዊ የሆነ ህገ መንግስቱን እንደማገድ ያለ ቆራጥ ስራ እንጂ የወታደር ልብስ ለብሰው ወጧ እንዳማረላት ወይዘሮ መወዝወዝ አይደለም።
መልካም ሲሰራ የሚባለው ህይወት ያለው፣ ዘመን ተሻጋሪና ኢትዮጵያን ከመፍረስ ህዝቧንም ከስቃይ የሚታደግ ከሆነ ነው እንጂ ለሰልፊ ልብስና ቦታ መቀያየርን አያካትትም። መሆንን እንጂ መምሰልን አይጨምርም።
ሀገር ሲኖር ነው ያም ቢሆን መደረግ የሚችለው ለሚል ሙግት መልሴ ሀገር እኳ ነበረን።
ሀገር አልባ የመሆን አደጋ ውስጥ የከተተን ስርዓቱ ነው።
ተሰርታ ያደረችን ሀገር አሁን ያለችበት የመፍረስ አደጋ ውስጥ የከተታይ ህገ መንግስታዊ መዋቅሩ ነው።
ተጨማሪ የብሔር ክልል የሚያዋልደውና የብሔር የፌደራሊዝሙን ወኪልነቴን እዩልኝ ብሎ ዛሬ በፌስቡክ ገፁ ላይ የፃፈው አብይ አህመድ ስርዓቱን ቀይሮ ከዚህ አፍራሽ እብደት ያወጣናል ብዬ ለማሰብ ወይ የአብይ አህመድ ጭፍን ምዕመናን መሆን ካልሆነም ሆዳም ካድሬ መሆን ይጠይቃል።
በህገ መንግስቱና በጎሳ ፌደራሊዝም ላይ በህዋሃትና በአብይ አህመድ መካከል የነጥብ ልዩነት የለም።
ወደ ለየለይ ጦርነት ያደረሳቸው አለመግባባት የስልጣን እንጂ የመትህ ተቃርኖ አይደለም ስንል በምክንያት ነው።