>

" የሀብታሙ አያሌው የትግል ጉዞ ከትናንት እስከ ዛሬ....!!!"   ( ሸንቁጥ አየለ)

” የሀብታሙ አያሌው የትግል ጉዞ ከትናንት እስከ ዛሬ….!!!”  
ሸንቁጥ አየለ

ሀብታሙ አያለዉ ከኢህአዴግ የወጣት ሊግ መሪነት ወጥቶ ወደ ተቃዋሚነት ተቀላቀለ ሲባል ነገሩን በማሾፍ ነበር የሰማሁት:: አሁን ኢህአዴግ ቤት የነበረ ሰዉ ተቃዋሚ ቢሆን እዉን ተቃዋሚ ይሆናል ብዬ ካጣጣሉት ሰዎች አንዱ ነኝ::ከጋዜጠኛ ተመስገን ጋር በዚህ ነገር ስንነጋገር በወቅቱ ያካፈለኝን ሀሳብ ግን ሁል ጊዜም በአክብሮት አስታወሰዋለሁ::
ተሜ ሲናገር ፈገግ ይላል::የተሜ ትህትናዉ ለጉድ ነዉ::ልበ ሙሉነቱም ያስገርማል::ሀሳቡን ደግሞ በልዩነት ሲያካፍል የሰዉ ስሜት እንዳይጎዳ በጣም ተጠንቅቆ ነዉ::ጨቋኞችን እና እብሪተኞችን የማይፈራዉ ተሜ ለግለሰቦች ስሜት ግን በጣም ይጠነቀቃል::
—-
እናም ስለ ሀብታሙ አያሌዉ እንዲህ አለኝ “የለም ሸንቁጥ ሀብታሙ አንተ እንደምታስበዉ ተራ የኢህአዴግ ሰዉ አይደለም::በጣም ጎበዝ ጭንቅላት ያለዉ ሰዉ ነዉ::በጣም ጥሩ አቋም አለዉ” ሲል መለሰልኝ:: እኔ ደግሞ ጥሎብኝ ኢህአዴግ አባል/አመራር የነበረ  ተቃዋሚ ሆነ ሲባል እዉነትም አይመስለኝም:: ይሄ እይታዬ ጥቂት ከረር ያለ ቢሆንም ደግነቱ የሰዎችን ባህሪና ሀሳብ በሂደት እየገመገምኩ ትክክለኛ አቋም ካላቸዉ ማክበርና የሚገባቸዉንም ቦታ መስጠትንም ጠንቅቄ አዉቃለሁ::
—-
እናም ተሜ በወቅቱ ስለ ሀብታሙ የሰጠዉን ሀሳብ አልተስማማሁበትም ነበር::”ከኢህአዴግ ዉስጥ አሁን ተቃዋሚ ሰዉ ይወጣል?” ብዬ አለፍኩት::በተለይ ግን አንድ ሰዉ አማራ:ኦርቶዶክስ እና በኢትዮጵያዊነት ፖለቲካ አምናለሁ እያለ ከኢህአዴግ ጋር ከሰራ በብዙ ምክንያት ያን ሰዉ ተቃዋሚ ይሆናል ብዬ ለማመን የምቸገርበት ሁኔታ አለ::ግን ይሄን አቋሜን ሀብታሙ አያሌዉ በደንብ የፈተነበት ወቅት ወዲያዉ መጣ::
——-
በወቅቱ ተቃዋሚ ነኝ ብሎ እንዘጥ እንተፍ ይል የነበረዉ የአንድነት ፓርቲ ዉስጥ ስዬ እና ነጋሶ የሚባሉ ሁለት የጸረ ኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ አራማጅ የኢህአዴግ ጉራጆች ገብተዉ ነበር::እነዚህ ሁለት ጸረ ኢትዮጵያዊነት ግለሰቦች ታዲያ ልክ ፓርቲዉ ዉስጥ እንደገቡ ያደረጉት የፓርቲዉ የፖለቲካ ፕሮግራም እንደ ነፍጠኞች አስተሳሰብ አሃዳዊነትን ያራምዳል ብለዉ ፈረጁ::ከዚያም  የፓርቲዉን የፖለቲካ ፕሮግራም ወዲያዉ ሽረዉ በኢሃዴግ የፓርቲ ፕሮግራም ተኩት:: እናም ዘግይቶ ሀብታሙም የተቀላቀለዉ ፓርቲ ይሄን ፓርቲ ነበር::
—–
ሀብታሙ ጥርት ያለ የኢትዮጵያዊነት አስተሳእብ እንዳለዉ ያወቅሁት ታዲያ ወዲያዉ ነበር::  ልክ የአንድነት ፓርቲን እንደተቀላቀለ መጀመሪያ ሙግት የገጠመዉ ስለ አንድነት ፓርቲ የፖለቲካ ፕሮግራም ነበረ::
ቃል በቃል በኢንተርቪዉ ላይ የሰጠዉን መልስ እስካሁን አስታዉሰዋለሁ:”አንድነት  ፓርቲ የኢትዮጵያ አንድነት ፓርቲ ነኝ ብሎ ሲያበቃ የፖለቲካ ፕሮግራሙ ግን ኢትዮጵያን የሚያፈርሰዉ የጎሳ ፖለቲካ ፕሮግራም ነዉ::ይሄም የተቀዳዉ ከራሱ ከኢህአደግ ፕሮግራም ነዉ::ይሄ መለወጥ  አለበት::”
ይሄን ከፍተኛ ክርክር አድርጎ የፖለቲካ ፕሮግራሙ እንዲለወጥ ያቀረበዉን ሀሳብ እስካሁን አስታዉሳለሁ:: ይሄ ሰዉ ጥርት ያለ ሀሳብ አለዉ ስልም ወዲያዉ አድናቆቴን በልቤ ቸሬዉ ነበር::
እያንዳንዱ ያቀርበዉ የነበረዉ የፖለቲካ ፕሮግራም ጥርት ያለ ኢትዮጵያዊነት በልቡ ያለ ሰዉ ብቻ ከአዕምሮዉ የሚያፈልቀዉ ነበረ::ነጥብ አንድ ብላችሁ ያዙልኝ::
——
የሀብታሙን የሀሳብ ጥራት በደንብ ያሳዬኝ ግን አሁን በአማራ ህዝብ ላይ የተከሰተዉ የመከራ ወቅት ነዉ::ዛሬ የአማራ ብሄረተኛ ነን ባዮች የአማራን ህዝብ እልቂት እና መከራ በአካባቢ እየሸነሸኑ  አንድም በስልጣን ወይም ደግሞ ከኦህዴድ ጋር ተቀናጅቶ ወያኔን መምታት የሚቻለዉ ኦህዴድን የሚያስቀይም ነገር ባለማንሳት ነዉ ብለዉ ለጊዜአዊ ጥቅማቸዉ እንወክለዋለን የሚሉትን ህዝብ ክደዉታል::ዛሬ የአማራ አክቲቪስት እና ሚዲያ ነን ብለዉ ሲፏንኑ የነበሩ ሰዎች በመቶ ሽህ አማራ ወለጋ ላይ ሲፈናቀል እና ሲያልቅ በብዙ መቶ ሽህ አማሮች በወሎ እና በሸዋ ሲያልቁ ይሄ በደል ከተነገረ መንግስታችንን ያስቀይማል ብለዉ ዝምታን መርጠዋል:: አንዳንዶቹም አንዱን አካባቢ ለማግኘት ሌላዉን አካባቢ ለኦህዴድ ፈርመዉ በመስጠት እነሱ የአማራ አባወራ ሆነዉ ስለ አማራ የሚናገረዉን ሁሉ ቀንድ ቀንዱን እየመቱት ነዉ::(በነገራችን ላይ በዚህ ሰዓት እንደ አባይ ዘዉዱ በአማራ ክልልም ሆነ በቀሪዉ ኢትዮጵያ የሚከናወነዉን የአማራ ህዝብ ስቃይ ለመዘገብ የደፈረ ጋዜጠኛ በሀገር ቤት እጅግ በጣም ጥቂት ነዉ::የአባይ ዘዉዱ አርያነት ለጊዜዉ ይቆዬን እና ወደ ሀብታሙ አያሌዉ እናተኩር::)
—-
የብአዴኖች ይታወቃል::ግን አዳዲሱ የአማራ ብሄረተኛ ነኝ ባይ ከብአዴናዉያን በከፋ ሁኔታ የኦህዴዳዊ ወዶ ገብ ባሪያ መሆንን መርጧል:: አንድ ምሳሌ ላንሳ::ሰሞኑን በስልሳ ሽህ የሚቆጠሩ አማሮች ከወለጋ እንዲሁም በአስር ሽህ የሚቆጠሩ  አማሮች እየተፈናቀሉ እና ብዙዎች ጭፍጨፋ እየተደረገባቸዉ ነዉ::
ይሄን መረጃ በፔጄ ላይ አካፈልኩት::አንድ ትልቅ የአማራ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ነኝ የሚል ሰዉ ግን በዉስጥ መስመር መጥቶ ብዙ እጅግ ብዙ ሰደበኝ::ግን ምን ሆነህ ነዉ? አልኩት:: “አንተ ዝም በል::በዚህ ሰዓት እዚያ ወለጋ ስለሚያልቀዉ የአማራ ህዝብ አያገባንም::ግንኙነታችንን እያበላሸህ ነዉ” ብሎ ደነፋ:: ለምን ? የሚል ጥያቄ አነሳሁለት::ኦህዴድን ላለማስቀዬም እንደሆነ የሚያሳብቅበት ብዙ ምክንያት ደረደረ::
—-
ይሄን ያነሳሁት በምክንያት ነዉ::አማራ መከራ ዉስጥ ገብቷል::ይሄ መከራ ዉስጥ መግባቱ አይደለም አስቸጋሪዉ ነገር::መካዱ ነዉ አስቸጋሪዉ ነገር::ለብዙ አመታት በኢትዮጵያ አንድነት ስም የተደራጁ ሀይሎች አማራ ሲያልቅ አማራ ተገደለ አትበሉ ብለዉ ብዙ ሰዉ ያስጨንቁ ነበር::አሁን ደግሞ በአማራ የተደራጁ ሀይሎች ስለ አማራ ሰቆቃ አትናገሩ ብለዉ ሰዉን አስጨንቀዉ ይዘዉታል:: ለዚህ አባባል ማሳመኛ ሀሳብ ካላቸዉ አደባባይ ወጥትዉ አይከራከሩም::ወይም በጽሁፍ አያስረዱም::ግን እንዲሁ በሽፍንፍኑ ዝም በሉ የሚል ዘምቻ ይዘዋል::ኢትዮጵያ ስትድን ብቻ ሁሉም ነገድ እንደሚድን ይታወቃል::ግን ሁሉም ነገድ እንዲድን እና በኢትዮጵያዊነት የደራጀ እርምጃ ለመዉሰድ እያንዳንዱ እዉነት እንደ ወረደ መነገር አለበት::ሰዉ አማራ ተብሎ ከተፈናቀለ እና ከተጨፈጨፈ ይሄዉ እዉነት መዘገብ አለበት::የአማራ ፖለቲከኞች ግን እዉነትን ሽሽት ላይ ናቸዉ::
——
ሰዉ ዝም ካላለ በወያኔነት ይከሱታል::በርካታ የብልጽግና ካድሬ ተሰብስቦ ይሰፍርበታል::በተለይም ሚዲያ ላይ ሰርተዉ የሚተዳደሩ ሰዎች ላይ ሚዲያዉን ሳይቀር ህዝብ እንዲጠላዉ ያለ ምንም ይሉኝታ ይዘምቱባቸዋል::
እናም ሀብታሙ በዚህ ወቅት የአማራ ህዝብን ብሶት ጥርት ባለ የሀሳብ ፍሰት ያስረዳል::ይተነትናል::ኢትዮጵያዊነትን በሚያከብር እና በአሳለጠ መልክ እዉነቱን ቁጭ አድርጎ ያሳያል::
—–
ከሃብታሙ በጣም የወደድኩት ነገርም አለ:: እንደ እንዳንድ ጥራዝ ነጠቅ የአማራ ተከራካሪ ነን ባዮችም ስለ ኢትዮጵያ አያገባኝም አይልም::የኢትዮጵያን ችግር በደንብ በአክብሮት ይተነትናል::
ኢትዮጵያ ስትድን የአማራ ህዝብ እንደሚድንም ጠንቅቆ ስለተረዳ በኢትዮጵያ መዳን ላይ አትኩሮት ያደርጋል::
—–
ይሄ ሁሉ ሆኖ ሀብታሙ በትንታኔዉ ዉስጥ የሚያሰማዉ አንድ ቅሬታ እና እሮሮር ጮክ ብሎ ይሰማኛል::ይሄዉም የብልጽግና ካድሬዎች የመንጋ ትችት እና ስድብ ልቡን እንዳቆሰለዉ ግልጽ ነዉ::
—–
 እናም ለሃብታሙ አያሌዉ Habtamu Ayalew Teshome  የምትከተለዋን ምክር ማስተላለፍ ፈለግሁ:-
——-
ወዳጄ ሀብታሙ የምትሰጠዉን ትንታኔ ጊዜ ሳገኝ ለመከታተል እሞክራለሁ::
ለኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት የሚበጅ ለአማራዉም ህዝብ ከፍታ የሚሆን ትንታኔ ነዉ የምታቀርበዉ::
ብዙ የመድረክ ሰዎች እና የሚዲያ ሰዎች የሀሳብ እጥበት ከደረሰበት አጨብጫቢ መንጋ ስሜት ጋር ለመመሳሰል ሲሞክሩ አንተ እና ጓደኞችህ እዉነት ላይ ቆማችሁ የራሱ ልጆች ለከዱት የአማራ ህዝብ እንዲሁም ለመላዉ የኢትዮጵያ ህዝብ በዚህ ሰዓት ድምጽ ስለሆናችሁ ልትመሰገኑ እንጂ ልትወቀሱ አይገባም::
የሰዉ ትችት ግን ዉስጥህን ያደማዉ ይመስላል::አደባባይ የወጣ ሀሳብ ለትችት መቅረቡ ዋናዉ ባህሪዉ ነዉ::ስለዚህ አትጨነቅ::ሀሳብህን ማካፈልህን ቀጥል::እዉነት ዋጋዋ ዉድ ነዉ::መንጋ አይረዳትም::እዉነትን በሰዓቱ የሚረዷትም ጥቂቶች ናቸዉ::
ህዝባችን የሚያስቡ አዕምሮዎች ያስፈልጉታል::የሚያስቡ ብቻ ሳይሆን የሚናገሩ አንደበቶች ያስፈልጉታል::ታላቁን ህዝባችንን አንዱ የገደለዉ አንሰላስሎ አለመናገር እና የሀሳብ ፍጭት ለማድረግ መጥላት ነዉ::
ስለዚህ ዝም ብለህ የምታስበዉን እና አንሰላስለህ መፍትሄ ነዉ የምትለዉን አካፍል::እዉነትን ማጋለጥህንም ቀጥል::ሀሳብ ያለዉ ይሞግትህ::ህዝብ የሚድነዉ በተሻለ የሀሳብ ሙግት  ላይ በሚቆም መፍትሄ ነዉ::
Filed in: Amharic