>

ለኢትዮጵያ ሀትሪክ የሠሩ በራሪ ነብር....!!! ደቻሳ አንጋቻ ታደሰ

ለኢትዮጵያ ሀትሪክ የሠሩ በራሪ ነብር….!!!
ደቻሳ አንጋቻ ታደሰ

 ብ/ጀ ተስፋዬ ሀ/ማርያም !
 
1ኛ- ከቀኃሥ እስከ ደርግ ዘመን 
2ኛ- በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ዘመን 
3ኛ- አሁን በህልውና ዘመቻ ዘመን 
ትውልዳቸው በቀድሞው ሸዋ ክ/ሀገር ጨቦና ጉራጌ አውራጃ ነው ። የቀለም ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ዝነኛውን የቀዳማዊ አፄ ሀይለስላሤ ሐረር ጦር አካዳሚ 6ኛ ኮርስ ምሩቅ በመሆን በምክትል መቶ አለቃ ተመረቁ ። በውትድርና ሙያቸው ሲያገለግሉ ከቆዩ በኃላ በኮ/ል ካሣ ገ/ማርያም በሚመራው የበረራ ደህንነት ተቋም የስፔሻል ፎርስ ስልጠና ወስደው የአየር መንገዳችንን ደህንነት በማስጠበቅ አገለገሉ ።
ለከፍተኛ ትምህርት ወደ አሜሪካ በማቅናት የስፔሻል ፎርስ ስልጠናቸውን በስኬት አጠናቀው ተመለሱ ። በአብዮቱ ዘመን ፈርሶ የነበረውን የአየር ወለድ (በራሪ ነብር ) ጦር በድጋሜ በማደራጀትና በመምራት አገልግለዋል ። በ1969 ዓ.ም ለ6 ወራት ናቅፋ ተከቦ የነበረው በኮ/ል ማሞ ተምትሜ ይመራ የነበረው 15 ሻለቃን ከሌሎች ጓዶቻቸው ጋር በአለም የዝላይ ታሪክ ተሞክሮ ከማያቅ ከፍታ በዣንጥላ በመዝለልና ከሻለቃው ጓዶች ጋር በመሆን የ6 ወራት የሻዕቢያን ከበባ በፍፁም ጀግንነት ሰብረው ወጥተዋል ። ሻዕቢያ ለዚህ ጀግንነታቸው አድናቆት በመቸር ሰብረው የወጡበትን ጠባብ መተላለፊያ Tesfaye pass / ተስፋዬ በር ብሎ ሰይሞላቸዋል ።
በመቀጠል የዚያድባሬን ወረራ ለመመከት ወደ ምስራቅ በማቅናት ሀረር ከተማን በመከላከል የነበረውን ውጊያ ተሳትፈዋል ። በውጊያውም በመድፍ ፍንጣሬ ጭንቅላታቸው ክፋኛ ቆስለው ከሞት ለትንሽ አምልጠዋል ። ከቁስላቸው ካገገሙ በኃላ ወደ ሰሜን ኤርትራ ግንባር በማቅናት የ1970 ግብረ ኃይሎች ዘመቻን ተሳትፈዋል ። አሥመራ ዙሪያ የነበረውን የሻዕቢያ ከበባ በመሥበር እስከ ኢላበርዕድ /ከረን ያለውን ቀጠና ከጠላት ነፃ በማውጣት ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክተዋል ። ለፈፀሙት አኩሪ ጀግንነትም የወቅቱ የኢትዮጵያ ትልቁን ሽልማት የህብረተሰባዊት ኢትዮጵያ የጀግና ሜዳይ ሽልማት ተቀብለዋል ። በነገራችን ላይ ይህን የወቅቱ ደረጃ አንድ ሽልማት የወሰዱት ሰዎች ሶስት ናቸው ።እነሱም
1/ ኮ/ል መንግስቱ ኃ/ማርያም
2/ ብ/ጀ ለገሠ ተፈራ
3/ ብ/ጀ ተስፋዬ ሀ/ማርያም  ናቸው ።
ወደ ቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት በማቅናት የከፍተኛ አዛዥነት  ትምህርታቸውን ተከታትለዋል ። ከዛ በመመለስ የብላቴ ማሰልጠኛ ዋና አዛዥ በመሆን አገልግለዋል ። 1983 ዓ.ም ሰራዊቱ በግፍ ከተበተነ በኃላ ወደ እስር ተጋዙ ። ከተፈቱ በኃላ የዶሮ እርባታ በመሥራት ሂወታቸውን መግፋት ጀመሩ ። 1990 የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ሲጀመር መደበኛ ጦርነት የከበደው ወያኔ በግፍ የበተናቸውን የቀድሞ ሰራዊት የድረሱልኝ ጥሪ ሲያደርግ የበደለኝ ወያኔ እንጂ ኢትዮጵያ አይደለችም በማለት ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ግንባር ዘመቱ ። ወያኔ ያበላሸውን ጦርነት ከሌሎች የቀድሞ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን መልክ በማስያዝ ለሀገራቸው ድሉን አስገኙ ። የጦር ሜዳ ውሎቸውን የሚዳስስ “የጦር ሜዳ ውሎ” የሚል አውቶባዮግራፊ መፅሀፍ ፅፈዋል ።
አሁን ደግሞ በአረጋዊ የእድሜ ዘመናቸው መንግስት ያቀረበውን የህልውና ዘመቻ ጥሪ በመቀበል ለኢትዮጵያ ብለው ለ3ኛ ጊዜ ግንባር ከተዋል ።
የህብረተሰባዊት ኢትዮጵያ የጀግና ሜዳይ ተሸላሚ ብ/ጀ ተስፋዬ ሀብተማርያም ለሀገራችን ኢትዮጵያ ስለከፈሉትና እየከፈሉት ስላሉት ክቡር መሥዋእትነት ኢትዮጵያ ታመሠግኖታለች ።
ይህ የብ/ጀ ተስፋዬ ሀ/ማርያም ታሪክ ኢትዮጵያ ስትጠራቸው ጨርቄን ማቄን ሳይሉ ፤ ስርአት በድሎኛል ሳይሉ የሀገራቸውን ጥሪ ሁሌም በደስታ ስለሚቀበሉት የቀድሞ የኢትዮጵያ የጦር ሰራዊት አባላት ወካይ ታሪክ ነው።
ክብር ለሠራዊታችን !
ኢትዮጵያ ታሸንፋለች!
Filed in: Amharic