>

"ሰሜኑ ጦርነት ሁለገብ ድጋፍ.....!!!" ከባልደራስ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

ሰሜኑ ጦርነት ሁለገብ ድጋፍ…..!!!”

ከባልደራስ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ሥራ አሰፈጻሚ ህዳር 17/2014 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ በህዳር የመጀመሪያ ሳምንት ይፋ ባደረገው የአቋም መግለጫ የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ በተለይም ደግሞ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል እየተካሄደ ያለውን ጦርነት በስፋት መርምሯል፡፡ ባልደራስ የጦርነቱን ስትራቴጅካዊ ግቦች እና አመራር በተመለከተ በህዳር 08/2014 ዓ.ም. ካወጣው መግለጫ በኋላ በመንግሥት በኩል የጦርነቱን አቅጣጫ ሊለውጡ የሚችሉ አግባብነት ያላቸዉ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ተመልክቷል፡፡ በዚህም በጠላት በኩል ይደረግ የነበረው ከፍተኛ ግስጋሴ ሊገታ መቻሉን ከሚወጡ ታማኝ የመረጃ ምንጮች ለመረዳት ችለናል፡፡
በሌላ በኩል ግን በሀገራችን በተፈጠረው ጦርነት ውስጥ ኃያላን አገራት በተለያዩ ደረጃዎች እጆቻቸውን በስፋት እያስገቡ መሄዳቸው ምናልባትም በቀጣይ በኢትዮጵያ ህልውና እና መረጋጋት ላይ ሊያሳድረው የሚችለው አሉታዊ ተጽዕኖ ከባድ ሊሆን እንደሚችል ተገንዝበናል፡፡ ጦርነቱ ዓለማቀፋዊ መልኩ እየጎላ መምጣቱ በአንድ መልኩ ለኢትዮጵያዊው ኃይል የሚሰጠው ዕድል እንደተጠበቀ ሆኖ በመንግሥት በኩል እየተወስዱ ያሉ እርምጃዎች የኢትዮጵያ ጠላት በሆነው የህውሃት ወራሪ ኃይል ላይ በሃገራዊ አንድነት መንፈስ ምላተ ህዝቡን ከማስተባበር አንጻር እንጅ የፖለቲካ ትርፍን ከግምት ውስጥ ያስገባ ሊሆን አይገባም፡፡ በዚህ ረገድ አሁንም ሊታረሙ የሚገባችው ክፍተቶች አሉ።
 የኢትዮጵያን ህልውና ለማስከበር ውድ የህይዎት ዋጋ በመክፈል ላይ ለሚገኙት ለአማራ እና ለአፋር ልዩ ኃይሎች፣ለፋኖ እና ለሚሊሺያ ተገቢውን ስንቅና ትጥቅ ማቅረብ ይገባል። በተለይ በአማራ ክልል ያለዉን ህዝባዊ ኃይል በጥርጣሬ የማየቱ ሁኔታ ስላልተወገደ አቅርቦቱ እየተጓተተ ሰለመሆኑ ቅሬታዎች እንዳሉ ይሰማል። ለዚህ ኢትዮጵያ በታሪኳ አይታው ለማታውቀው የሃገር ህልውና ትግል፣ የሚካሄደው መነሳሳት እና የሚደረገው ድጋፍ ለሃገረ-ኢትዮጵያ እንጅ ለፓርቲ አለመሆኑን ተገንዝቦ በሆደ ሰፊነት ሁሉንም ሀገር ወዳድ ኃይሎች ማስተባበር ያስፈልጋል።
በታሪክ ኢትዮጵያ ባጋጠሟት ወሳኝ ጦርነቶች መሪዎቻችን ወደ ዘመቻ ሲሄዱ የበደሉት ካለ ይቅርታ ጠይቀው፣ አለአግባብ ያሠሩትም ካለ ፈትተው፣ ሁሉን መርቀው ወደ ጦር ግንባር የሚሸኙበት አኩሪ ትውፊት ያለን መሆኑ ይታወቃል፡፡ ድላችንን በአጭር ጊዜ እና በአነስተኛ መስዋዕትነት እንድንጎናፀፍ፣ ፈጣሪም ለቂም በቀል ያልተነሳን መሆኑን ተገንዝቦ ለድል እንዲያበቃን መንግሥት ቂም በመያዝ ያሠረውን የሕዝብ ልጅ እስክንድር ነጋን እና ሌሎች የባልደራስ ፓርቲ አመራር አባላትን ጊዜ ሳይወስድ በመፍታት ለአገራቸው ሰላም አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ሊያደርግ ይገባል። የፓርቲያችን የባልደራስ የደነደነ ጸረ ሕዉህት አቋም በብልጽግና መንገስት የታወቀ ስለሆነ ይህንን የፓርቲያንን መሪዎች የመፍታት ጥይቄ ከወቅቱ ሃገራዊ መንፈስ አንጻር አይቶ ሊመለሰዉ ይገባል።
 ከዚሀም በተጨማሪ በእስር ላይ ያሉ የባልደራስ ፓርቲ መሪያችዎችን ሰሞኑን ለመጠየቅ የሄዱ የፓርቲያችን አባሎች ጠይቀዉ እንደወጡ በፖሊስ ታሥረዋል፡፡ እስረኞችን ለመጠየቅ የሄዱ ሰዎችን ማሰር በመደበኛም ሆነ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊሳበብ የሚችል አይደለም። ይህን መሰሉ ህገ ወጥነት ህዝብን በመከፋፍል ከጦርነት ባላነሰ መልኩ ሀገርን የሚጎዳ መሆኑ ግልጽ ነው። ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ እስረኞች ለመጠየቅ ሄደው የታሠሩ አባሎቹም ባስቸኳይ እንዲፈቱ ይጠይቃል፡፡
ባልደራስ ከብልጽግና መራሹ መንግሥት ጋር ያለውን የፖለቲካ ልዩነት ለጊዜው የአገር ደህንነት ከተረጋገጠ በኋላ በዲሞክራሴያዊ መንገድ በሰላማዊ ሁኔታ በሚካሄድ ትግል ይቀጥላል ብሎ ያምናል። በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያዉያን ለሀገር ህልዉና እና ሉአላዊነት የሚያረጉት ጦርነት ከፓሪቲ ድጋፍ እና ወገናዊነት በላይ መሆኑን መገንዘብ የድሉን ጊዜ ያሳጥረዋል። ለኢትዮጵያችን ህልውና ውድ ህይወታቸውን እየከፈሉ ያሉ ኃይሎችን በማናቸውም ደረጃ መደገፍ ኢትዮጵያችን ከእኛ እና እንደ እኛ ሃገራዊ ራዕይ ካላቸው ዜጎች ሁሉ የምትጠይቀው ሓላፊነት እና ግዴታ መሆኑን በመገንዘብ ፓርቲያችን የተጣለበትን አደራ ለመወጣት በበኩሉ ውሳኔ ላይ ደርሷል፡፡
ስለሆነም ባልደራስ ጦርነቱን አስመልክቶ በህዳር 08/2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ያስቀመጣቸው ስትራቴጅካዊ ግቦች እስኪሳኩ ድረስ በአገር ውስጥ እና በውጭ ያሉ አባሎቻችንን እና ደጋፊዎቻችንን በማስተባበር ኢትዮጵያችን የምትጠይቀንን ግዴታ፣ድርጅታዊ ነፃነታችንን በጠበቀ መልኩ ለመወጣት ተነስተናል፡፡ ይህንን ዓላማ ተግባራዊ ለማድረግም ከፍተኛ አስተባባሪ ኮሚቴ አቋቁመናል፡፡በውጊያው የቆሰሉ የመከላከያ አባላትን ጨምሮ ለሌሎች የህዝባዊ ተዋጊ ኃይሎች የደም ልገሳ ድጋፍ ከማድረግ ጀምሮ የተለያዩ የድጋፍ ዓይነቶችን እና አቅርቦቶችን ለማከናወን አስተባባሪ ኮሚቴው መርሃ ግብር አውጥቶ ዝግጅት ጀምሯል፡፡ ዝርዘር የድጋፍ ዓይነቶችን በተመለከተ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፓርቲያችን ይፋ ያደርጋል፡፡
የትግላችን መሠረት የሆንከው የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብም ሃገራዊ ህልውናን ለማስቀጠል እያደረከው ላለው ዘርፈ ብዙ መስዋዕትነት ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ከፍተኛ ከበሬታ አለው፡፡ አሁንም በምትችለው መንገድ የአገርህን እና የከተማህን ህልውና ለማስጠበቅ ፓርቲያችን በሚያወጣው መርሀ ግብር መሠረት ድጋፍህን እንድታበረክት በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን፡፡
የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ
ህዳር 20/2014 ዓ.ም.
አዲስአበባ- ኢትዮጵያ
Filed in: Amharic