ወንድወሰን ተክሉ*
ብልጽግና መራሹ መንግስት በሀገራዊ ህልውና ጦርነት ላይ ባለችው ሀገር ሀገራዊ አንድነትን ከመገንባት አንድነትን በሚያፈራርስ ተግባር የተጠመደ ስርዓት ሆኗል-!!!
፠የሀሳብ ልዩነትን ማክበርና መቀበል ማለት ሀገራዊ አንድነትን ማጠናከር ማለት ነው!!!
ሀገር በህልውና ጦርነት ላይ ናት ተብሎ የሀገሪቱ ርእሰ ብሄር ግንባር ዘልቆ ጦርነቱን ለመምራት እስከመገደድ በደረስንበት በአሁኑ ሰዓት መንግስት የታሰሩትን የህሊና እስረኞችን በመፍታት ከተቃዋሚዎቹ ጋር ያለውን ልዩነትን አቻችሎና ተቀብሎ የተቃዋሚውን ጎራ የተለየን ድምጽ እውቅና ሰጥቶ ሀገራዊ አንድነትን በማጠናከር በጦርነቱ ላይ ሀገራዊ ድጋፍ ከማስተባበር ይልቅ ይህንን ሀቅ በተቃረነ መልኩ ሰሞኑን በባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ደጋፊዎችና የአባይ ሚዲያ ተንታኝ በሆነው ጋዜጠኛ ላይ የእስር ተግባር ሲፈጽም ለማየት ተችሏል።
ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ላይ በእለት አርብ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ መስራችና ፕሬዚዳንት እስክንድር ነጋን እና ባለደረቦቹን ለመጎብኘት ወደ ቅሊንጦ የተጓዙ ስምንት የባልደራስ ደጋፊዎችን አፍኖ በማሰር መንግስት የተለመደውን ጸረ ሕዝብነቱን ባህሪይ እያሳየ ነው።
ስምንቱ የባልደራስ ደጋፊዎችና እስክንድር ነጋን ለመጠየቅ ሄደው ታፍነው የታሰሩት ፋሲል ውሃበ፣ምትኩ ካሳሁን፣ዮርዳኖስ እንዳለ፣ብሩክ ጫኔና ሰላም የተባሉ ወጣቶች ሲሆኑ ለመታፈን ያበቃቸውም ወንጀል የህልኒውን እስረኛ እስክንድርና የትግል አጋሮቹን መጎብኘታቸው ብቻ እና ብቻ ነው።
የብልጽግና መራሹ መንግስት በሀሰት ክስ በሀሰት ምስክር አስሮ በማሰቃየት ላይ ያለውን እስክንድር ነጋንና ባልደረቦቹን በዚህን ሰዓት መፍታት ሲገባው ስርዓቱ ግን ከማረሚያ ቤት አጅቦ ወደ ፍርድ ቤት የሚያመጣ አጃቢ የለንም በሚል መሰረት የለሽ ተልካሽ ምክንያት እነ እስክንድርን ወደ ፍርድ ቤት እንዳይቀርቡ ማገድና ብሎም እነ እስክንድርን ለመጎብኘት የተጔዙትን አፍኖ በማሰር የግፍ ማን አለብኝነቱን በይፋ እያሳየ ያለ ኋላፊነት የማይሰማውና ኋላፊነት የጎደለው ስብስብ ሆኗል።
በርካታ ኢትዮጲያዊያን ሀገራዊ አንድነት ይፈጠር ሀገራዊ አንድነታችን ይጠንክር የተለያየ የፖለቲካ አመለካከታችንን አቻችለን በሀገር ጉዳይ ላይ በአንድ ግንባር እንሰለፍ እያሉ በያሉበት ከፍተኛ ጥረት እያደሩጉ ባሉበት በዚህ ሰዓት ትልቁን ሃላፊነት ከያዘው መንግስት የበለጠ ድርሻና ሚናን ማየት ሲገባን ይህንን በተቃረነ መልኩ የተራ ዜጋውን ያህል እንኴን ስለሀገራዊ አንድነት የማያስብና የማይሰራ ግድየለሽ ስብስብ መሆኑን እያሳየን ይገኛል።