(ዳዊት ከበደ ወየሳ)
በአገራችን ያለው… የወታደራዊ እና ህዝባዊ ደህንነት “በተወሰነ ደረጃ የመረጃ ማሰባሰብ ድክመት አለበት” የሚሉ ትችቶች በተደጋጋሚ ይሰነዘራሉ። ይህ ትችት ውሃ የሚያነሳ ቢሆንም፤ እኛ ደግሞ መረጃ ስናገኝ ዝም ካልን፤ ተጨማሪ ስህተት ልንሆን ነው። በመሆኑም ይህን መረጃ የምናካፍላቹህ… የመረጃ ትንሽ ስለሌለው መሆኑን በመረዳት፤ ላልደረሰው አዳርሱ።
ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ከአዲስ አበባ ተነስተው ወደ ጅጅጋ የሚበሩ አውሮፕላኖች በህወሃት ደጋፊዎች የተሞሉ ነበሩ። እስከዛሬዋ እለት ድረስ በሺዎች የሚቆጠሩ የህወሃት ደጋፊ የሆኑ ሰዎች ከአዲስ አበባ ጂጂጋ ገብተዋል። ከጅጅጋደግሞ ወደ ኢትዮጵያ እና የሱማሊያ ፑንትላንድ እየተሻገሩ ነው። በዚህም መሰረት… ከጅጅጋ – ቶጎ ውጫሌ – ከቶጎውጫሌ ወደ ቦሳሶ ፑንት ላንድ ብዙ ሺህ ህወሃቶች ገብተዋል።
ይህ ጉዞ “በደህንነቱ በኩል ይደረስበታል፤ ወይም ይገታል” ተብሎ ቢታሰብም፤ ይባስ ብሎ በየቀኑ የሚመጣው ህዝብ ቁጥር በጣም እየበዛ መሆኑ የጅጅጋ ነዋሪዎችን ስጋት ላይ ጥሏቸዋል። በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ሱማሌ የተረጋጋች ብትመስልም፤ ውስጥ ውስጡን ግን፤ የአብዲሌ ደጋፊዎች ጊዜ እና ሁኔታ እየጠበቁ መሆኑን ለማወቅ ችለናል። ለዚህም ጥሩ አመላካች የሚሆነው፤ ባለፈው ደሴ እና ኮምቦልቻ በህወሃት ሲያዝ፤ የአብዲ ኢሌ ደጋፊዎች “ወያኔ ሊመለስልን ነው። አብዲሌም ይፈታል” በማለት በደስታ ሲጨፍሩ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
በአሁኑ ወቅት በሱማሌ ኢትዮጵያ የሚገኙት የአብዲሌ ወይም የወያኔ ደጋፊዎች፤ ከአዲስ አበባ እና ከሌሎች ከተሞች ወደ ጅጅጋ የሚገቡትን የህወሃት ደጋፊች፤ ወደ ቶጎ ውጫሌ ያለምንም ችግር እያሻገሯቸው ይገኛሉ። በሌላ በኩል ደግሞ “አሜሪካ አንድ ሺህ ያህል ወታደሮቿን ወደ ምስራቅ አፍሪቃ አስጠግታለች” ሲባል፤ ነጠብጣቡን ገጥመን ስዕሉን ማንበብ ካቃተን ከሰነፍ ተማሪ የማንሻል ቂሎች ነን… ማለት ነው። በጣም የሚያናድድ የዋህነታችንን ትተን፤ ከአዲስ አበባ እስከ ጅጅጋ፤ ከዚያም እስከ ቶጎ ውጫሌ እና ፑንት ላንድ ድረስ የሆነውን ስንመለከት፤ በዚያ ላይ ደግሞ የአሜሪካ ወታደር በፑንትላንድ አድርጎ ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ማሰቡን ስንሰማ፤ አንዳች ተንኮል ሊሸተን ይገባል። በኛ በኩል ይህን ያህል ካልን ይበቃል። ቀሪውን ለኢትዮጵያ ሱማሊያ ክልል ባለስልጣኖች እና ለፌዴራል መንግስት ደህንነት እንተወው።
በነገርዎ ላይ ከሱማሊያ በርበራ ወደብ ወደ ጅጅጋ የሚወስደው መንገድ 241 ኪሎ ሜትር ነው። ከወደቡ ወደ ኢትዮጵያ እቃዎችን ለማመላለስ፤ የኢትዮጵያ መንግስት በ4.5 ሚሊዮን ዶላር ወጪ… ከቶጎ ውጫሌ እስከ ጅጅጋ ትልቅ መንገድ አሰርቷል። አሁን ይህ መንገድ አላማውን ስቶ በቅርቡ የጦርነት ቀጣና እንዳይሆን ነው የብዙዎች ስጋት የሆነው። በዚያ ላይ በአካባቢው የአሸባሪዎች እንቅስቃሴ መኖሩ በተደጋጋሚ ይነገራል። ሌላው ቀርቶ… ከቅርብ አመታት በፊት፤ የህወሃት ሰዎች በዚህ በቶጎ ውጫሌ መሽገው ከቆዩ በኋላ በድንገተኛ ብርበራ፤ 7 ኪሎ ግራም ወርቅ እና 60 ሚሊዮን የልዩ ልዩ አገራት ገንዘብ መያዙ የሚታወስ ነው።
አሜሪካ… በኢትዮጵያ እና በህወሃት መካከል የተከሰተውን ልዩነት ከማባባስ በቀር፤ ለማቀዝቀዝ ያደረገችው አንዳችም ጥረት እንደሌለ የኢትዮጵያ መንግስት ምንጮች ያመለክታሉ። አሁን ደግሞ አንድ ሺህ ወታደራዊ ጦር ወደ በርበራ ወደብ መላኳ፤ በሁሉም የኢትዮጵያ ከተሞች የሚገኙ የህወሃት ደጋፊዎች ደግሞ ወደዚህች ቶጎ ውጫሌ ከተማ ማምራታቸው ድንገተኛ አጋጣሚ ሊሆን አይችልም። ይህ ስፍራ… በበርካታ የኢትዮጵያ ወታደራዊ እዞች ስር ሲጠበቅ የነበረ መሆኑ ይታወሳል። ሌላው ቀርቶ አለም አቀፉ ጀግና ኮ/ል አብዲሳ አጋ ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ የመጨረሻውን ወታደራዊ ግዳጃቸውን የተወጡበት፤ በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመን ሰርጎ የገባውን የሱማሊያ ሰራዊት የቀጡበት ታሪካዊ ቦታ ነው። እነጄነራል አማን አምዶም ሚካኤል ኢትዮጵያዊነትን ያስመሰከሩበት ስፍራ ነው።
እናም የወታደራዊ እና ህዝባዊ ደህንነት ሆይ! በዚህ በኢትዮጵያዊያን ደም እና አጥንት በቆየ ታሪካዊ ስፍራ ላይ፤ አሜሪካ እና ወዳጆቿ… ህወሃቶች እና የአብዲ ኢሌ ደጋፊዎች በቀጠሮ እየተጠባበቁ ነው የሚመስለው። “ምን እያደረጋቹህ ነው?” ብለን አንጠይቅም። ነገር ግን መረጃችን ደርሷችኋል፤ እናንተም ሰምታችኋል ብለን እናስባለን።