>
5:13 pm - Monday April 19, 6917

"መንግሥት በተለያዩ ግንባሮች ድል መቀዳጀቱን ዐስታወቀ!!!!" (DW)

“መንግሥት በተለያዩ ግንባሮች ድል መቀዳጀቱን ዐስታወቀ!!!!”
DW

*…. የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፤ የአማራ ልዩ ኃይል፤ ፋኖ እና የአማራ ሚሊሺያዎች በጥምረት ባደረጉት የተቀናጀ ጥቃት በርካታ ከተሞችን መቆጣጠራቸው ተገለጠ። 
በሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ቁጥጥር ስር የነበሩት፦ እጅግ ስልታዊዋ የጋሸና ከተማን ጨምሮ በርካታ ይዞታዎች በመንግሥት ቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኢትዮጵያ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ዐስታውቀዋል። ሚንሥትሩ «ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት» በሚል ርእስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ድሉን፦ «ለሕዝባችን ሐሴትን የሚፈጥር፤ በአንጻሩ ደግሞ ለጠላት የማይጠገን ስብራት» ብለውታል።
በጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ እየተመራ በሁሉም ግንባሮች «በከፍተኛ  የማጥቃት እንቅስቃሴ» መገባቱንም «አስደናቂ ድሎች» መመዝገባቸውንም አክለው ተናግረዋል። ድሎቹ የተገኙባቸውን ሥፍራዎች ሲዘረዝሩም፦ «በጋሸና ግንባር ጀግኖቹ የመከላከያ ሠራዊት፤ የአማራ ልዩ ኃይል፤ ሚሊሻ እና ፋኖ በጥምረት ባደረጉት ተጋድሎ በጋሸና ግንባር የአርቢትን፣ የአቀትን፣ የዳቦ እና የጋሸና ጠቅላያ ዞን  የአካባቢውን  ሲቪል ማኅበረሰብ  በማስገደድ» በሕወሓት የተገነባው «ባለ ብዙ እርከን የኮንክሪት ምሽግ» መሰበሩን ይፋ አድርገዋል። ምሽጉ የተሰበረውም፦ «በተቀናጀ ዕቅድ፤ የአመራር ጥበብ እና ቴክኖሎጂ በመታገዝ በአነስተኛ ሰብአዊ እና ቁሳዊ መስዋዕትነት» መሆኑንም ገልጠዋል። በዚሁ ግንባርም በርካታ የነፍስ ወከፍ፤ የቡድን እና ከባድ ጦር መሣሪያዎችን የመንግሥት ኃይሎች መማረካቸውንም ጠቅሰዋል።
በጋሸና የተገኘው ድል፦ «ጠላት በላሊበላ እና በሰቆጣ፤ በወልዲያ እና ደሴ የተቆጣጠራቸውን አካባቢዎች በአጭር ጊዜያት ውስጥ ለማጽዳት መንገዱን የተመቻቸ ያደርገዋል» ሲሉም አክለዋል። «የወገን ጦር ጋሸናን እና  አካባቢውን ከመቆጣጠር አልፎ በላሊበላ፤ ወልድያ እና ወገልጤና  አቅጣጫ ወደፊት በአሁኑ ሰአት እየገሰገሰ  ይገኛል» ሲሉም በሰሜን ኢትዮጵያ ስላለው የጦርነት ውሎ እና ድል ተናግረዋል።
ከጋሸና ግንባር ባሻገር በወረኢሉ እና በሸዋ ግንባሮችም የመንግሥት ኃይሎች ድል መቀዳጀታቸውን የኢትዮጵያ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ይፋ አድርገዋል። በዚህም መሠረት፦ በወረኢሉ ግንባር የጃማ ደጎሎ፣ ወረኢሉ፤ ገነቴ፣ ፊንጮፍቱ እና አቀስታ ከተሞች በመንግሥት ኃይላት ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ዐስታውቀዋል። በሸዋ ግንባር ደግሞ  በመዘዞ፣  ሞላሌ እና ሸዋሮቢትም ድል መገኘቱ ተዘግቧል።
ቀደም ሲል በምስራቅ ግንባር በመከላከያ፤ በአፋር ልዩ ኃይል እና ሚሊሺያ ጥምረት  ነፃ የወጡት፦ የአሳጊታ፣ ቡርቃ፣ ዋኢማ፣ ጪፍቱ፣ ድሬሮቃ፣ ጭፍራ እና አለሌ ሱሉላ ከተሞች ሙሉ ለሙሉ ከጠላት ፀድቶ የአካባቢው አስተዳደር ወደ ቦታው በመመለስ አካባቢዎቹን መልሶ የማደራጀት ተግባር እያከናወነ ይገኛል»ም ብለዋል።
ፎቶ፦ (ከኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት)
Filed in: Amharic