>
5:28 pm - Friday October 10, 0645

አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ!  የፕሮፖጋንዳ ጥይት የማይበሳው ስብእና...!!!   (ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ)

አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ!  የፕሮፖጋንዳ ጥይት የማይበሳው ስብእና…!!!
  ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ

ምእራባውያን የብዙሀን መገናኛዎች የአትሌት ሀይሌ ገብረስላሴን፣ ‹‹እዘምታለሁ!›› ማለት አምነው መቀበል ከብዷቸዋል፤  አሸብሯቸዋልም፡፡ ለምን?
ምእራባውያኑ ጠ/ሚንስትሩን ከአሜሪካው የህዳሴ ግድብ ደርድር ማቋረጥ ጀምሮ በጎን፣ ከትህነግ ጋር ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ደግሞ በግልጽ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ አጠልሽተዋቸዋል፡፡ በሀሰት ዜና እየሰሩ፣ ያልተደረገ ተደረገ እያሉ፣ የዘር አጥፊ፣ ጨፍጫፊ  አድርገው ለአለም ህዝብ አቅርበዋቸዋል፡፡ ስለሆነም የእሳቸው ‹‹እዘምታለሁ!›› ማለት፣ ለእኛ እንጂ ልእልናው፣ለእነሱ ተጨማሪ የፕሮፖጋንዳ መሳለቂያ ግብአት ነው፡፡
ሀይሌ ገብረስላሴን ግን ያውቁታል! የትኛውም ፕሮፖጋንዳ ሊንደው አይደለም ሊሸነቁረው አይችልም፡፡ ከልጅነት እስከ እውቀቱ አለም ያውቀዋል፤ ትልልቆቹ ጣቢያዎች ዘጋቢ ፊልም ሲሰሩለት፣ ጋዜጠኞቹ ለቃለመጠይቅ ሲጋፉለትና ሲጠላለፉለት ኖረዋል፡፡ ሀይሌን በኦሎምፒክ አደባባይ ባንዲራው ላይ ከተተከሉ አይኖቹ እንባ ጉንጮቹን አቋርጦ ሲንጠባጠብ አለም ተመልክቷል፡፡ ሀይሌ ላለፉት  ሶስት አስርታት የኢትዮጵያን ቀለም ለብሶ የአትሌቲክስ ደማቅ ምልክት ሆኖ አለም አይቷል፡፡ ሀይሌን አለም የሚያውቀው ከሀይሌነቱ በላይ በኢትዮጵያዊነቱ፣ ከተፈጥሯዊው ጥቁርነቱ በላይ በአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ብሄራዊ ቀለሙ ነው፡፡  እና ያውቃሉ! ይህ ስም ምንም የፕሮፓጋንዳ ጥይት እንደማይበሳው፤ ይህን የሶስት ቀለም ጥምረት ምንም የፕሮፓጋንዳ በረኪና እንደማያስለቅቀው ያውቃሉ፡፡ . . . . ሀይሌ ብቻውን የምእራባውያኑን ሚዲያ፣ አፍቃሪ ትህነግ መንግስታት፣ በገንዘብ የተገዙ የፖለቲካ ደላሎች፣  . . . በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ለማቃጠል ዘይት ጥደው ሲያንተከትኩ የነበሩት ላይ ሁሉ፣ ምድጃቸው ላይ በረዶ ከልሶበታል፡፡
በተለይ ደግሞ፣ ከቀበሌና ወረዳ ስልጣን የተነሱ፣ ወይም ለውጡ ባስከተለው ነውጥ ጥቂት ጥቅም የቀረባቸው፣ ‹‹ኢትዮጵያ ትበተን!›› እያሉ በሚያላዝኑበት በዚህ ወቅት፣  ሀይሌ ባለፉት ሶስት አመታት የወደመበትንና ያጣውን የምናውቅ ኢትዮጵያውያን፣ የሀይሌን ‹‹ለኢትዮጵያ እዘምታለሁ፣ እሞታለሁ!›› ስንሰማ፣ የስብእናው ልእልና በግላዊ ጥቅም ማጣት እርሾ መነሾ የማይጎብጥ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡  . . . . . . እናም እናከብርሀለን ሀይሌ!
Filed in: Amharic