≪ ይሄን ካርታ ስታዩ በኢትዮጵያዊነታችሁ አትኮሩም?≫
ተመስገን ባዲሶ
☞…..▼ እ,ኤ,አ በ1884 የአውሮፓ ሀገራት በበርሊን ያደረጉት ኮንፈረንስ የራሳቸውን ጉዳይ ያዘለ አጀንዳ ለመነጋገር አልነበረም። ይልቅ እምቅ የሆነ የተፈጥሮ ሀብት ያላትና ጨለማዋ አህጉር ብለው የሚጠሯትን አፍረካ በወረራ ለመቀራመት እንጂ!!……እነዚህ የአውሮፓ ሀገራት ኃይላቸውን ተመርኩዘው የሰው ሀገር የሚወሩበት የበርሊኑ ኮንፈረንስ ቅኝ_ግዛት የሚል ሀገር የማቅናት ስያሜ ይስጡት እንጂ አላማው ሀገር ለመዝረፍ ነበር። በዚህ ታሪካዊ የአውሮፓዊያን ጉባዔ ወደፊት ሙሉ አፍሪካን እንደበሬ አርደው፣ እንደ_ቅርጫ ሊከፋፈሉ ቃል ተገባቡ። ባህር አቋርጠው አፍሪካን እንዳሰቡትም በመዳፋቸው አስገቧት። አፍሪካም ለዘመናት የስቃይ ፅዋን ስትጎነጭ ኖረች፣ ቁጥሩ የማይታወቅ ሀብት በጉልበተኞች ተዘረፈች፣ ዜጎቿ በተፈጠሩበት እና በተወለዱበት የእናት እና የአባታቸው የቅድመ አያቶቻቸው የውርስ መሬት ላይ ሁለተኛ ዜጋ ሆነው ኖሩ። ህይወት በአፍሪካ ትርጉም አጣ፣ ሰብዓዊነት ዘቀጠ፣ ሰው ከእንስሳ በታች ተቆጠረ። እያንዳንዱ ሀገር «ማነህ?» ቢባል ማን እንደሆነ የሚናገርበት አንደበት አጣ። የነበረው ሃይማኖት፣ ባሕል፣ ትውፊቱ፣ ቋንቋው ጭምር….. ከሀብቱ ጋር ተነጠቀ። ቆፍሮና አርሶ የወራሪ ነጭ ገባሪ እንጂ የመሬቱ ተጠቃሚ መሆን አልቻለም። እንኳን የጥቅም ተካፋይ ሊሆን ይቅርና በነጭ መንገድ እንዳይሄድ፣ ከደረሰበት እንዳይደርስ፣ እሱ በሚሄድበት መኪና እንዳይሳፈር፣ በአጠቃላይ በተፈጥሮ ማግኘት ያለበት መሰረታዊ ነገሮቹ ሁሉ አፍሪካዊው ተገፈፈ። «ነፃነት» የሚለው ቃል በዚህች አህጉር ከሚገኘው መዝገበ_ቃላት ላይ ተደለዘ። ወራሪዎቹ ሀብቱን ወደሀገራቸው እያገዙ፣ በተረፈው ደግሞ በራሱ በአፍሪካዊው መሬት ላይ የቅንጦት ህይወት እያጣጣሙ ስንት ግፍና መከራ ለአፍሪካ ሕዝብ አሸከሙት? አፍሪካዊያን ከስንት አመታት መረገጥ በኋላ የነፃነት ትግል አድርገው፣ አያሌዎች ሞተው ተራ በተራ ነፃ ቢወጡም የቅኝ ገዢዎቹ «የከፋፍለህ ግዛው!» ሴራ የቀበረው ፈንጂ በየጊዜው እየፈነዳ በእርስ በእርስ እልቂት ወንድም ወንድሙን ሲገድል ኖረ! በሩዋንዳ የደረሰው በታሪክ የማይረሳ የዘር ፍጅት የኮሊያኒሊስቶች ውጤት ነው።
☞▼ ይሄ ሁሉ በደልና ግፍ የፈፀሙት አውሮፓዊያን እ,ኤ,አ በ1884 ያደረጉት የበርሊን ኮንፈረንስ ነበር። ይሄን የሴራ ሸንጎ ካደረጉ 136 አመት ገደማ ተቆጠረ። በዚሁ ሁሉ አመታት አውሮፓውያኖዎቹ የጥፋት ተልዕኳቸውን በተግባር አከናውነው የሚፈልጉትን በሙሉ ፈፅመዋል። ይሄ ሁሉ በታሪክ ተፈፅሞ፣ ዛሬም አፍሪካዊያን በታሪክ ትምህርታቸው ትውልድን ያስተምሩበታል። የትኛው የአውሮፓ ሀገር የትኛውን የአፍሪካ ሀገር በቅኝ እንደገዛ በመመሪያ መፃፎቻቸው ላይ አስፍረው ለተማሪዎች ክዋኔውን ያስገነዝቡበታል።
☞…….▼ ይሄ የአፍሪካን ካርታ ያዘለው የመማሪያ መፅሃፍ፣ በአንዲት የአፍሪካ ሀገር የታሪክ መፅሓፍ ላይ ሰፍሮ ያገኘውት ነው። እስኪ የኢትዮጵያ ካርታ ላይ ያለውን ፅሁፍ አንብቡ። « ለመሆኑ FREE የሚባል ቅኝ ገዢ የአውሮፓ ሀገር አለ?» የበርሊኑ ኮንፈረንስ ያላሳካው ብቸኛው እቅድ ቢኖር ይሄው ያነበባችሁት ፊደል ነው። ነፃነቷ ያልተገፈፈ፣ መሬቷ ያልተደፈረ፣ ከነጭ ጫማ ወድቃ ያልኖረችው ኢትዮጵያን የጠበቋትና ያስከበሯት ደማቸውን ያፈሰሱና ውድ ህይወታቸውን የገበሩት አያቶቻችን ናቸው።
FREE የሚለው ቃል ዝም ብሎ የተፃፈ ተራ ፊደል አይደለም! በደም የተፃፈ ከባድ የውለታ ቃል ነው።
ዘላለማዊ ክብር ይሄን ውድ የታሪክ ማዕረግ ላጎናፀፉን ይሁን።