>
5:13 pm - Friday April 18, 5986

“የቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ! (ቀለብ ስዩም - የህሊና እስረኛ)

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!

 
“የቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ!
ቀለብ ስዩም (የህሊና እስረኛ)
በእዚህ ርዕሰ-ጉዳይ ስለ ውዷ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያና ስለ አይበገሬዎቹ ፋኖዎች ታላቅ ገድል የበኩሌን ለማዋጣት የህሊና እስረኝነቴ አላገደኝም፡፡ በርእሰ-ጉዳዩ ዙሪያ ማውሳት የፈለግሁት ያለመነሻ ምክንያት አይደለም፡፡ አንዳንድ ቅን አስተሳሰብ ያላቸው ታዳሚዎቼ “ስለ አማራነት አግዝፋ ባሳየችበት የተባ ብዕርዋ ስለ ኢትዮጵያዊነትም ልትነግረን ይገባል!” የሚል አይነት አስተያየት አቀብለውናል፣ እኔም ታዳሚዎቼን የማክበር የሞራልና የሥነ ምግባር ግዴታ እንዳለብኝ ስለማምን እነሆ! የግል አመለካከቴን ጀባ ! እላለሁ፡፡
እኔና እናንተ የቅድመ-አያቶቻችን፣ የአያቶቻችንና የአባቶቻችን ልጆች ነን፡፡ እንደሚታወቀው አባቶቻችን፡- ድምፀ-አራዊት ግርማ ሌሊት ሳይበግራቸው፣ ዳዋ ጥሰው ጤዛ ልሰው፣ የቀን ሀሩር የሌሊት ቁር ሳያደግዳቸው፣ ከነደደ እሳት ከተሳለም ስለት ተፋልመው ነበር ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያን ከነሙሉ ክብርዋ ያቆዩልን፣ ያስረከቡንም፡፡
ኢትዮጵያ ፍጹም ልበ-ሙሉ የሆኑ የጦር ጀግኖች ያሉዋት ብትሆንም ጦርነቶች የፈጠሩዋት ሀገር ግን አይደለችም፣ ኢትዮጵያ አዳምና ሔዋን ያወረሱን የገነት ርስታችን ናት፡፡ መላው አለም ከኢትዮጵያ አብራክ ተገኘ እንጂ ኢትዮጵያ ከእዚህ አለማዊ ሥርአት አብራክ አልተገኘችም፡፡ ኢትዮጵያ ሀገረ-እግዚአብሔር ናት፤ እናም ኢትዮጵያ የሚለው ስያሜዋ በራሱ የቅድስና መጠሪያዋ ነው ቢባል ገለጻው የተጋነነ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ፍቅር ናት፤ የመተዛዘንና የመደጋገፍ እሴቶቻችንም ከእዚሁ የሚመዘዙ መሆናቸውንም በድፍረት መናገር እንችላለን፡፡ ኢትዮጵያ፡- እንደ ልጃገረድ ዳሌ የሚያማልሉ ወንዞች ክረምት ከበጋ፣ ቀን ከሌሊት ያለእረፍት የሚፈሱባት፣ አራዊት በየመስኩ በነፃነት የሚቦርቁባት… ለምለም ምድር ናት፡፡ ብታምኑም ባታምኑም ለእኔ ኢትዮጵያ በልቤ ሳሎን ውስጥ እንደ ጌጥ ያስቀመጥኳት ውብ አበባ ናት፡፡ ለእናንተም ልክ እንዲሁ ናት ብዬ አስባለሁ፤ አምናለሁም፡፡
ብዙዎች ይህን እውነት አይረዱትም፡፡ ኢትዮጵያን ለመረዳትም ሆነ ለማወቅ የልብ ቅድስና ያስፈልጋል፡፡ ጌታችንና መድሀኒታች እየሱስ ክርስቶስ በልጅነት ዘመኑ ወደ  ኢትዮጵያ የመጣው ለቅድስት ሀገራችን የገባውን ቃልኪዳን ለማፅናት ነበር፤ ሙሴ ወደ ሀገረ ኢትዮጵያ መጥቶ ለአርባ አመታት የኖረው ከአምላክ የተሰጣትን ታላቅ ተስፋ ስለተረዳ ነው፡፡ ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ በመቅደላ ራሱን የሰዋው፣ እምዬ ምኒልክ እንደ ብረት በጠነከረ ክንዱ የኢጣሊያን ወራሪና የትግራይን ባንዳ የደቋቆሰው፣ ሌሎች ኢትዮጵያዊያንም በታላቅ ጀግንነት በየዘመናቸው የተዋደቁት የኢትዮጵያን ሀገረ-እግዚአብሔርነት ጠንቅቀው በማወቃቸው ነበር፡፡ ዘርአይደረስ በሮም አደባባይ የጣሊያንን መንጋ በጉራዴ የረፈረፈው የኢትዮጵያ የነፃነት ምሳሌ የሆነውን ሰንደቅ አላማዋን ሲያንቋሽሹ በማየቱ ነበር፡፡ አብዲሳ አጋ በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት በጣሊያን ምድር የራሱን የጦር ሰራዊት አደራጅቶ ፋሽስት ሞሶሎኒን መግቢያና መውጫ ያሳጣው የኢትዮጵያ ክብርና ዝና ከፍ ማድረግ ተገቢና አስፈላጊ እንደሆነ በመገንዘቡ ነበር፡፡
ኢትዮጵያን ጠንቅቀው የሚያውቁት ውድ የኢትዮጵያ ልጆች ብቻ አይደሉም፡፡ የእዚህ አለም ገዥ (ሰይጣን ዲያቢሎስ) እና ታማኝ ልጆቹም (አሜሪካና አውሮፓውያን) ኢትዮጵያ በእግዚአብሔር መንግስት የሚኖራትን የክብርና የቅድስና ስፍራ በሚገባ ይረዳሉ፡፡ ኢትዮጵያ ሀይልዋም ብርታትዋም ፈጣሪ አምላክዋ ከመሆኑም በላይ የሀያልነትና የአይበገሬነት መንፈሳዊ መሳሪያዋ “ኢትዮጵያ” ከሚለው ስያሜዋ እንደሚነሳም ይገነዘባሉ፡፡ ስለዚህም ሰይጣናዊ ተልእኮአቸውን በመላው አለም ለማሰፈን የሚቻለው ኢትዮጵያ የምትባል አገር ስትጠፋ ነው ብለው ስለሚያምኑ ሁሉም የኢትዮጵያ ጠላት ሆነው ይቀጥላሉ፡፡
ይሁን እንጅ ህወሓትና ሸኔን የመሳሰሉ የእናት ጡት ነካሾች የኢትዮጵያን የሀያልነት ምስጢር አያውቁትም፡፡ የኢትዮጵያዊነት እሴቶችና የሰብአዊነት ፋይዳዎችም በውስጣቸው ስለሌለ አይገነዘቡትም፡፡ እነርሱ እንደ ጋማ ከብት ሆዳቸውን ለሞላ ሁሉ ለመጫን ያጎነብሳሉ፡፡ በመሆኑም የአሜሪካ የአውሮፓና የግብፅ ጌቶቻቸው እንዳሻቸው እየተንደረደሩ ይጋልቡአቸዋል፡፡ ምን መናገር እንዳለባቸው እንኳ በውል ስለማያውቁ፡- “… ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጎን ተሰልፈን እንዋጋለን.. እስከ ሲኦልም ቢሆን ወርደን ኢትዮጵያን እናፈርሳለን…” እስከ ማለት ደርሰዋል፡፡ “በአፍ ይጠፉ- በለፈለፉ!” እንዲል መጽሐፉ ከእነዚህ የጋማ ከብቶች (የትግራይ ወራሪዎች) አብዛኛዎቹ በተመኙት መሰረት ወደ ሲኦል ወርደዋል፣ ከፊሎቹም ወደ ግብአተ-መሬታቸው ሊወርዱ በፍጻሜ መጀመሪያ ላይ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያዊነት ሁሉም የድል አድራጊነት መንፈስ በመሆኑ ሽንፈት የሚባል ነገር አይታወቅም፡፡ የግብጽ ሴራና የህወሓት ፉከራ ለኢትዮጵያውያ ምናቸውም አይደለም፡፡ በጀግንነት የሚያህላቸው የለም፣ ጠላቶቻቸውንም እስከወዲያኛው ማስወገድን ያውቁበታል፣ ይችሉበታልም፡፡
ወደ ሌላኛው ርዕሰ ጉዳይ እንሸጋገር፡፡ ፋኖ ሲባል አማራ ብቻ የሚመስላቸው አንዳንዳንድ ወገኖች እንዳሉ እገምታለሁ፡፡ ይሁን እንጂ አእምሮአችንን እስፍተን ብንመለከት “ፋኖ” በጎሳና አካባቢ የተወሰነ አይደለም፡፡ በዘመነ ጣሊያን ወራሪ የነበረውን የፀረ- ጠላት ፍልሚያ ብንፈትሸው፡- በጎንደር፣ በጎጃም፣ በሸዋ፣ በባሌ፣ በሲዳሞ፣ በከፋ፣ በወላይታ፣ በወለጋ… ወዘተ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በዱር በገደሉ የሸፈቱ አያሌ ስመጥር ፋኖዎች ነበሩ፡፡ ፋኖነት፡- አንድ አካል በሌላው ላይ ግፍና በደል ሲፈጸም፣ ፍትህ ሲጣስና ሰብአዊነት ሲረገጥ በእምቢ ባይነት መፋለም ነው፡፡ ፋኖ፡- እንደ የመከላከያ ሰራዊትና እንደየክልሉ ልዩ ሐይ ደመወዝተኛ አይደለም፣ የሚያቋቁመውና የሚያሰማራው አካል የለም፡፡ ፋኖን ወደ ዱር ገደሉ እንዲወጣ የሚያደርገው በእርሱና በወገኖቹ ላይ የሚደርሰው ግፍና በደል ይሆናል፡፡ ፋኖነት በግል ተነሳሽነት የሚከናወን የነፃነት ትግል ነው ቢባል ተሳስታችሁዋል የሚለን የሚኖር አይመስለኝም፡፡
እንዳብነት በአማራ ክልል የሚገኙትን ፋኖዎች መመልከት ይቻላል፡፡ ከታሪክ የማይማረው ህወሓት የግብፃውያ ሮቦት ሆኖ የአማራን ህዝብ ረግጦ ለመግዛትና ሰብአዊ ክብራቸውንም ለመርገጥ ያልፈነቀለው ድንጋይ ያልማሰውም ጉድጓዋድ አልነበረም፡፡ ያኔ፡- እነ መሳፍንት ጥጋቡ፣ እነ ጎቤ መልኬ፣ እነ አረጋ፣ እነ ኩሎኔል ደመቀ ዘውዱ፣ እነ አጋየ አድማሱን፣ እነ አስቻለው ደሴ፣ እነ ቃቁ አወቀ፣  እነ መብራቱና ናቃቸው፣ እነ ሙላው የሞላ አጃው አባት፣ እነ ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ፣ እነ ዘመነ ካሴ፣ እነ ሄኖክ፣ እነ ደረጀ በላይ (አባናደው)፣ እነ ቶማስ ጀጃው፣ እነ ጌታቸው ሽፈራው፣ እነ ንግስት ይርጋና ጠቅሼ የማልጨርሳቸው. የመሳሰሉ የአማራ የቁርጥ ቀን ፋኖዎች እዚህም እዚያም ተፈጠሩ፡፡ ቤት ንብረታቸውን፣  እናት አባታቸውን፣ ሚስት ልጆቻቸውን ትተው በዱር በገደሉ ተሰማርተው ህወሓትን በሚገባው ቋንቋ ያናግሩት ጀመር፡፡ የእግር እሳት ሆነው መቆሚያ መቀመጫ ነሱት፡፡ ይህ የእምቢ ባይነትና አይበገሬነት መንፈስ አድጎ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ አደረጋቸው፡፡ ከትግራይ እስከ ጋሸና ላሊበላና ሌሎች ብዙ ቦታዎች የተገነቡትን የጠላት ምሽጎች ለመስበር ግምባር ቀደም ተፋላሚ እስከ መሆን ደረሱ፡፡
እናም የክፉ ቀን ደራሸ የሆኑ፣ በግል ተነሳስተው ለሀገራቸውና ለህዝባቸው ጥቅም መከበር ያለምንዳ የሚፋለሙ ፍኖዎቻችንን ማክበር፣ ማወደስና ማመስገን ይበልጥ ማጀገን ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ክቡር ለፋኖዎቻችን ይሁን! በእዚህ አጋጣሚ አንድ ነገረ ለማለት እፈልጋለሁ፤ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ፋኖ አጋየ አድማሱ ለፈጸመው ታላቅ የጀግነት ጀብዱ 5 ክፍሎች ያሉት የመኖሪያ ቤት ማበርከቱ ይበል የሚሰኝ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ይሁን እንጂ ሌሎችንም ፋኖዎች በእዚህ መልኩ ማገዝና ማበረታት ይገባል ባይ ነኝ፡፡
በመጨረሻም አንድ መልእክት አስላልፌ ከእዚህ ጽሑፍ ልውጣ፡፡ በእዚህ የህልውና ፍልሚያ ወቅት ከሕወሓት የተማረውን የፖለቲካ ሴራ መደጋገም የሚፈልግ ካለ ራሱን ቢፈትሽ መልካም ይመስለኛል፡፡ በያንዳንዱ ዝርዝር ጉዳይ ላይ በቂና አሳማኝ መረጃዎችን እየደረደርኩ መሞገት ብችልም አሁን ጊዜው እንዳልሆነ እረዳለሁ፡፡ የጦርነቱ ኬሚስትሪ ኢትዮጵያ ሀገራችን ከመፍረስ ማዳን በመሆኑ ዝርዝር ጉዳይ ውስጥ መግባት አልፈለግሁም፡፡ ከሀገር ህልውና በሁዋላ መወቃቀስና ማስተካከል ይቻላል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ ጦርነቱን በመፋለም ላይ የሚገኘውን የወገን ሃይል አንዱን ተጠቃሚ ሌላውን ተጎጂ የሚያደርግ የተጋድሎ ውጤት የመቀማት ስራ እንዳይመዘገብ ከወዲሁ መጠንቀቅ ብልህነት ነው፡፡
ዛሬን በአግባቡ ካልያዝነው ነገ ይበላሻል፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ፡- “የቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ!”  ይለናልና።
እግዚአብሔር ሆይ! ጥበቃህ፣ ምህረትና ቸርነትህ ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያውያን ጋር ይሁን!!!
አሜን፡፡
Filed in: Amharic