>

"ዳግማዊ አቡነ ጴጥሮስን ማየት ካሻችኹ ወልድያ አሉላችሁ" (ኤፍሬም ሀብተ ማርያም)

ዳግማዊ አቡነ ጴጥሮስን ማየት ካሻችኹ ወልድያ አሉላችሁ”
ፍሬም ሀብተ ማርያም)
*…. የወልዲያው ወጣት ስለ አቡነ ኤርምያስ ከነገረኝ!

በቅርቡ ከወልድያ ወደ ባሕርዳር የመጣ ወጣት ስለ አቡነ ኤርምያስ ከነገረኝ በጥቂቱ።
” ወልዲያ ያለው መከራ ከመነገር በላይ ነው ግልጹን ስነገርህ በወልድያየሚኖር አንድ ሰው አግኝተህ ከረሃብ በሕይወት እንዴት ተረፍክ ፤ምን እየበላህስ እስከዚህ ደረስክ ? ካልከው መልሱ እንዲህ የሚል ነው:-
“አባቴ አባ ኤርምያስ እርሱ ተርቦ እያበላኝ፣እርሱ ተጠምቶ እያጠጣኝ ” ይልኻል።
የወልዲያ ሰው የዘመኑን ጴጥሮስ አግኝቷል።ይገርምኻል አባታችን በየባንክ ቤቱ የሚገኙ ጀነኔተሮችን ሰብስበው ወደ ወፍጮ ቤት በማስወሰድ፤ለክፉ ቀን ብለው ገንዘብ በቤታቸው ያስቀመጡ ባለሃብቶችን ” ይህ ቀን ሲያልፍ እኔ እከፍላለሁ፣እኔ ባልኖር ቤተክርስቲያን ትከፍላችሗለች አይኔ እያየ ልጆቼ በርሃብ አይሙቱብኝ እባካችሁ አበድሩኝ “እያሉ በተማጽኖ እየተበደሩ እህል ገዝተው እራሳቸው ብጹዕነታቸው ወፍጮ ቤት ቆመው እያስፈጩ ሕዝቡን እየመገቡ ነው። አቅም ኖሮት ሊያስፈጭ የሚመጣ ካለ እዛው ቆመው አንድ አንድ ኪሎ እያስቀነሱ በየቤቱ መንቀሳቀስ ለማይችሉ አረጋውያን ያደርሳሉ። ችግሩ ከተፈጠረ ጊዜ ጀምሮ ያለማቋረጥ ጸሎተ ምሕላ እራሳቸው በዕንባ ሆነው እያደረሱ ነው። በአካባቢው ያሉ የሽብርተኛው ሕወሓት መሪዎችን ያሉበት ካንብም ሆነ ሌላ ቦታ በመሄድ ፊት ለፊት በመጋፈጥ “ልጆቼን አትንኩ ህዝቤን አታስጨንቁ እግዚአብሔር ይፈርዳል” እያሉ የህዝቡን መከራ እያቀለሉ ነው።
 ይገርምሃል ስለ አቡነ ጴጥሮስ እየሰማሁ ያደኩትን ታሪክ በገሀድ ተገልጦ በእርሳቸው ላይ አየሁት። ሞት አይፈሩም(ስለክርስቶስ የሞተ እንዴት ሞትን ይፈራል)። በከተማው ባሉ አቢያተ ክርስቲያናት ይዘዋወራሉ ያስተምራሉ። እርግጠኛ ሆኜ የምንግርህ አቡነ ኤርምያስ ባይኖሩ ኖሮ የወልዲያ ህዝብ ይህንን የመከራ ዘመን ለመግፋት ይከብደው ነበር። በሕክምና እጦት፣በመድኃኒት ማጣት በየቀኑ ሰው ይሞታል። እናቶች በወሊድ ምክንያት ይሞታሉ። በፊት አካባቢ የዝናብ ውሃ ነበር የምንጠጣው።አሁን በእግር ተጉዘን ከወንዝና ከኩሬ ውሃ ቀድተን ነው የምንጠጣው። ይኼም በስንት መከራ። ተነግሮ አያልቅም ጊዜው ሲደርስ ሁሉም እውነት ስለ አባታችን ይሰማል ህያው ስራቸውም ለዘለዓለም በልባችን ጽላት ተመዝግቦ ይኖራል።
“አንድ ነገር ላስቸግርህ ለወዳጆችህ እንዲህ በልልኝ አቡነ ጴጥሮስን በአካል ማየት ከፈለጋችሁ ወልዲያ አለላችሁ በልልኝ “
♦እኔም እላለሁ አምላኬ ሆይ የመከራው ዘመን አልፎ አቡነ ጴጥሮስን (ኤርምያስ ) በአካል አግኝቼ ከእግራቸው ላይ ተደፍቼ በረከትን አገኝ ዘንድ አድለኝ።
Filed in: Amharic