>

"በድል የታጀበው የመጀመሪያው ምእራፍ” (ጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት)

“በድል የታጀበው የመጀመሪያው ምእራፍ”
ጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት

ውድ የሀገሬ ልጆች፣
የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ወዳጆች፣

ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ትከበራለች፤ ትታፈራለች። ኢትዮጵያን መገዳደር ይሞከር ይሆናል። ተገዳድሮ ማሸነፍ ግን ትናንትም አልተቻለም፤ ዛሬም አይሆንም፤ ነገም አይቻልም። ኢትዮጵያ የሚለው ስም ሁሌም ከአሸናፊነት ጋር የተያያዘ ነው። ከጥቂት ጊዜያት በፊት ኢትዮጵያን ሊወጋ የተነሳውን ጠላት በጋራ ሆነን እንድንመክት ጦር ግንባር ላይ የያዝነው ቀጠሮ ጠላትን አንገት ሲያስደፋ ኢትዮጵያን ቀና አድርጓታል። ሀገራችን ታፍራና ተከብራ እንድትኖር ለማድረግ በጦር ግንባር እየተከፈለ ያለው መስዕዋትነት የኢትዮጵያን የአሸናፊነት ስም የሚመልስ መሆኑን እያበሰርኩ፣ ያቀረብኩትን ጥሪ ተቀብላችሁ ሕይወታችሁን፣ ጉልበታችሁን፣ ሀብታችሁን፣ ዕውቀታችሁን፣ ጊዜያችሁንና ሞያችሁን ለሠጣችሁ ሁሉ በኢትዮጵያ ስም ላመሰግናችሁ እወዳለሁ። በዚሁ አጋጣሚ፣ የመጀመሪያውን ምእራፍ አጠናቅቄ ለተወሰኑ ጊዜያት ወደ ቢሮ መመለሴን እየገለጽኩ፣ ዛሬም ሆነ ወደፊት ጠላቶቻችን ጉልበታቸው ዝሎ፣ የጥላቻና የጠበኝነትን መንገድ ጥለው፣ የፍቅርና የሰላምን መንገድ እስኪመርጡ ትግላችን ይቀጥላል።
የእኛ ፍላጎት ሁሌም ሰላምና ፍቅር ነው። ኢትዮጵያ ሕብረ ብሔራዊ አንድነቷ ተጠብቆ የብልጽግና ጉዞዋ የተቃና እንዲሆን ያለንን ፍላጎት ከጅምሩ አሳውቀን ለተግባራዊነቱ ስንተጋ ቆይተናል። ነገር ግን በተደጋጋሚ ያቀረብነውን የሰላም አማራጭ ባለመቀበል፤ አሳታፊና አካታች የሆነውን አዲሱን የፖለቲካ ባህላችንን ረግጦ በመውጣት፤ ጥፋትንና እልቂትን ለማስቀረት ሲባል የተደረገውን ትዕግሥት ከቁብ ባለመቁጠር፤ የአንዳንድ የውጭ ጠላቶችን አፍና ድጋፍ በመተማመን፤ አሸባሪው ሕወሓት ከግብር አምሳሎቹ ጋር ሆኖ በሀገራችን ላይ አደጋ ደቅኖ ነበር። ነገሮች ያለቁና የተጠናቀቁ እስኪመስሉ ድረስ ኢትዮጵያን የማያውቁ ሁሉ በሥጋትና በፍርሐት ተውጠው ነበር። ሠግተው ሊያሠጉን፤ ፈርተው ሊያስፈራሩን የሞከሩ የውስጥና የውጭ አካላትም ነበሩ። ልጣችን የተራሰ፣ ጉድጓዳችን የተማሰ መስሎ የተሰማቸው ነበሩ። የኢትዮጵያን የአሸናፊነት ምሥጢር የሚያውቁት ብቻ በጽናት እስከ መጨረሻው የቆሙበት አጋጣሚም ተፈጥሮ ነበር።
ወደ ትግል የገባነው ሐቅን ይዘን ነውና የኢትዮጵያ አምላክ እንደ ወትሮው ከእኛ ጋር ነበር። ድካማችንን አበርትቷል። ሕዝባችንን ከዳር እስከ ዳር አነቃንቋል። የሠራዊታችንን ቁጥርና ዐቅም ጨምሮልናል። ልባችንን አጀግኖ የኢትዮጵያን አሸናፊነት በዓይናችን አሳይቶናል። ውድቀታችንን ሲመኙ የነበሩትን ሁሉ አሳፍሮ ዳግም የኢትዮጵያን ስም በወርቅ ቀለም እንድንጽፍ አስችሎናል። የዚህ ታሪክ አካል ለመሆን ፈጣሪ ዕድሉን የሰጣችሁ ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ። የኢትዮጵያን ስም ከማድመቅ የበለጠ ዕድል የለምና!!
በዕቅዳችን መሠረት የመጀመሪያውን ምዕራፍ፣ “ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነትን” በሁለት ሣምንት ውስጥ አሳክተናል። የመከላከያ ሠራዊት፣ የየክልሎቹ ልዩ ኃይሎች፣ የፌዴራል ፖሊስ አባላት እና የየአካባቢዎቹ ሚሊሻዎችና ታጣቂዎች በከፈላችሁት መሥዋዕትነት ለልጆቻችን የምንነግረው ድንቅ ታሪክ ሠርታችኋል። በሁሉም መስክ በደጀንነት የተሰለፋችሁ ሁሉ የኢትዮጵያ ውድ ሀብቶች መሆናችሁን በዓይናችሁ አይታችኋል።
ትግሉ ገና አልተጠናቀቀም። ነጻ ያልወጡ አካባቢዎች አሉን። አሁን የፈተነን ኃይል ዳግመኛ የኢትዮጵያ ፈተና ሆኖ እንዳይመጣ የሚያስችል ዘላቂ መፍትሔ ልንሰጠው ይገባል። ለዚህኛው ችግር በምንሰጠው መፍትሔ ወደፊት ለክፉ ያሰቡን ሁሉ እጃቸውን እንዲሰበስቡ ማድረግ አለብን። ላለፈው የምናመሰግንበት እንጂ ጨርሰናል ብለን እፎይ የምንልበት ወቅት ላይ አይደለንም። የተበተነው ጠላት እንዲማረክ ማድረግ አለብን። አካባቢያችንን ከበፊቱ በበለጠ ነቅተን የመጠበቂያ ጊዜው አሁን ነው። ፍተሻና አሰሳዎችን አጠንክረን መቀጠል ይገባናል።
ጠላት ያፈረሰውን መልሰን መገንባት፣ የተፈናቀሉትን መመለስ፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎቻችንንም ከበፊቱ በበለጠና በፈጠነ መንገድ ማሳለጥ ይጠበቅብናል።
ለሠራዊታችን የምንሰጠውን ሁለንተናዊ ድጋፍ በዓይነትም በብዛትም አጠናክረን የምንቀጥልበት ወቅት ነው። ያልዘመቱ ወገኖች ግማሽ ያህል ጊዜና ጉልበታቸውን ለዘማች ቤተሰቦች መስጠት ይጠበቅባቸዋል፤ እነሱ ለእኛ ሕይወታቸውን ሲገብሩ እኛ ለእነሱ ገንዘብና ጉልበታችንን መስጠታችን ቢያንስ እንጂ አይበዛም። እናም በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የዘማች ቤተሰቦችን መደገፍና ማበርታት አለብን።
ትግሉ በጦር ግንባር ብቻ አይደለም፤ በሁሉም መስክ መፋለም ይገባናል። የገበሬውን እህል አንዲት ፍሬ እንዳትባክን አድገን ወገባችን አሥረን መሰብሰብ አለብን። በዲፕሎማሲውና በፖለቲካው ዘርፍ የምንሠራቸውን ሥራዎች በአዳዲስ መንገዶች እያከናወንን መቀጠል ይገባል። ወጭ ቆጥበን፣ ጊዜና ጉልበት ጨምረን፣ ለሀገራችን ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ መሥራት ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል።
በተለይ በተለይ በህልውና ዘመቻው ወቅት ያየነውን የኢትዮጵያውያንን አንድነት እስከ ዓለም ፍጻሜ ሀብታችን አድርገነው መቀጠል አለብን። በገጠርና በከተማ፣ በሀገር ቤትና በውጭ፣ በግንባርና በደጀን፣ ያለን ሁላችን ለአንድ ዓላማ ተሰልፈን አንድ ግብ እያሳካን ነው። ማንም ተነስቶ ኢትዮጵያን ማውረድ ከማይችልበት ማማ ላይ እየሰቀልናት ነው። ይህ አንድነታችን እንዲዘልቅ ከፋፋይ ሐሳቦችን እንመክት። የድል አጥቢያ አርበኞችን እንቃወም። በተጋድሏችን ያገኘነውን ነገር ለማቅለል የሚፈልጉትን ፊት እንንሣቸው። በጋራ ታግለን በጋራ ያስገኘነውን ድል፣ እንደ ቅርጫ ሥጋ ሊመድቡ የሚነሡትን አቃራጮች እናነውራቸው። ያሸነፈችው ኢትዮጵያ ናት። ከዚህ የወረደ ነገር አንቀበልም።
የገጠመን ፈተና ብዙ መከራና ችግር ያስከተለብን ቢሆንም በምንም መንገድ የማናገኛቸውን ዕድሎችም ይዞልን መጥቷል። ከገጠመን ፈተና ይልቅ በዕድሎቻችን ላይ አተኩረን ከሠራን ኢትዮጵያን ኃያልና ራሷን በሁሉም መስክ የቻለች ሀገር እናደርጋታለን። ከፈጣሪ ቀጥሎ በፈተናችን ጊዜ አብረውን ለቆሙ እና በዓለም አደባባይ ለተማገቱልን ሁሉ ኢትዮጵያ ከፍ ያለ ምስጋና ታቀርባለች። የጀመርነው ህልውናችንን የማስከበርና ኢትዮጵያን በጽኑ መሠረት ላይ የመትከል ተጋድሏችንን በፍጥነት አጠናቅቀን ወደ ብልጽግና አጀንዳችን በሙሉ ጉልበት በቅርቡ እንደምንመለስ እምነቴ ነው።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ሕዳር 29፣ 2014 ዓ.ም
Filed in: Amharic