>

«ሕወሓት ሰዎችን በጅምላ ገድሏል....!!!» (ሒዩማን ራይትስዎች)

«ሕወሓት ሰዎችን በጅምላ ገድሏል….!!!»

 ሒዩማን ራይትስዎች

የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ታጣቂዎች ተቆጣጥረዋቸዉ በነበሩና በሚቆጣጠሯቸዉ የአማራ ክልል ከተሞች በርካታ ሰላማዊ ሰዎችን በጅምላ መግደላቸዉን  ሒዩማን ራይትስ ዋች አስታወቀ።ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት ዛሬ ባሰራጨዉ ዘገባ እንዳለዉ የሕወሓት ታጣቂዎች ከነሐሴ 25 እስከ ጳጉሜ 4 ፣2013  በአማራ ክልል ጨና መንደርና በቆቦ ከተማ ወደ ሐምሳ የሚጠጉ ሰዎችን በጅምላ ረሽነዋል።
በዘገባዉ መሠረት የሕወሓት ተዋጊዎች ነሐሴ 25 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ጨና ከገቡ በኋላ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትና ከአማራ ሚሊሽያዎች ጋር ከባድ ውጊያ ገጥመዉ ነበር።መንደሪቱን በተቆጣጠሩበት አምስት ቀናት ዉስጥ በ15 የተለያዩ ቦታዎች 26 ሰላማዊ ሰዎችን በጅምላ መግደላቸውን የዓይን ምስክሮች እንደነገሩት የመብት ተሟጋቹ ድርጅት ጽፏል። በቆቦ ከተማም ጳጉሜ 4 ቀን፣ 2013 ዓ.ም 23 ሰዎችን በአራት የተለያዩ ቦታዎች ገድለዋል።ግድያው ወደ አካባቢዎቹ በመገስገስ ላይ በነበሩት የትግራይ ኃይሎች ላይ በገበሬዎች ተፈጸመ ያለውን ጥቃት ለመበቀል እንደሆነም በዘገባው ሰፍሯል። በሂዩመን ራይትስ ዋች የቀውስና ግጭት ጉዳይ ክፍል ኃላፊ ላማ ፋኪህ የሕወሓት ኃይሎች ሰዎችን በጅምላ የመግደላቸዉ ጭካኔ የሰው ልጅ ሕይወትንና የጦርነት ሕግጋትን አለማክበራቸውን አሳይተዋል ብለዋል።
እነዚህና ሌሎች በግጭቱ ውስጥ በተካፈሉ ኃይሎች በትግራይና በአማራ ክልሎች ተፈጽመዋል በተባሉ የጦር ወንጀሎች ላይም ገለልተኛ ዓለም አቀፍ ምርመራ ማካሄድ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ሂዩመን ራይትስ ዋች፣ በጨና ተክለሃይማኖት መንደርና አካባቢ እንዲሁም በቆቦ ከተማ ስለተካሄደው ውጊያና ስለደረሰው  የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በመስከረምና በጥቅምት ወር፣ 36 የዓይን ምስክሮችን፣ የሰለባዎች ቤተሰቦችና ጎረቤቶችን የሃይማኖት አባቶችን እና ሐኪሞችን ከርቀት ማነጋገሩን በዘገባው ጠቅሷል።ከሟቾቹ የአርባ አራቱን ስም ዝርዝር ማግኘቱንም ድርጅቱ አስታዉቋል።
ይሁንና የሕወሓት ባለስልጣናትን አስተያየት ቢጠይቅም መልስ አለማግኘቱን ዐስታውቋል። ዶይቸ ቬለም በሂውማን ራይትስ ዎች ዘገባ እና በአማራ ክልል የርዳታ እህል ዝርፊያ ጉዳይ ከሕወሓት በኩል መረጃ ለማግኘት ከትናንት ጀምሮ ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም። ሂዩመን ራይትስ ዋች ወደ አማራና አፋር ክልሎች በተስፋፋው ጦርነት የደረሱ በደሎችን የሚያጣራ ገለልተኛ ዓለም አቀፍ አካል እንዲቋቋም ጠይቋል። የተመድ የፀጥታው ምክር ቤትም በተፋላሚ ኃይላት ላይ ማዕቀቦችን እንዲጥል ጠይቋልም።
Filed in: Amharic