አንዱአለም ቦኪቶ. ገዳ
እሁድ ጠዋት ከምሸግ ወጣ ብላ የምትገኝ አንዲት ከተማ ከጥቂት ወንድሞች ጋር ሆነን ቡና እየጠጣን ሳለ የአንደኛው ፋኖ ወንድማችን ስልክ ጮኸ፡፡
“ኃሎ!.. ተጀመረ!?… እሺ… እሺ!”አለና ስልኩን ዘግቶ “በሉ ተነሱ! ጦርነቱ ተጀምሯል! “አለ፡፡
አጅሬዎቹ ወዲያው ጥድፊያ ውስጥ ገቡ፡፡
“..አንዲ ተነስ እንሂድ!” ሲሉኝ
“አዎ እውነታችሁን ነው እንሂድ ከዚህ!” ብዬ ተነሳሁ፡፡
በርግጥ መጀመሪያ “እንሂድ” ሲሉኝ (24 ሰአት የሚያጅቡኝ ጠባቂዎቼም ስለነበሩ) ጦርነቱም ቅርብ ርቀት ላይ ስለተጀመረ “አሁን ያለህበት ቦታ ጥሩ አይደለም !ወደ ደህና ቦታ እንሂድ” ያሉኝ ነበር የመሰለኝ፡፡
እንደዚህ በከፍተኛ ደስታ የተነሳሱት ወደ ጦርነቱ ስፍራ ለመሄድ እንደሆነ መኪና ውስጥ ገብተን የመኪናውን አቅጣጫ ሳይ ነበር የገባኝ፡፡
ለአይን በሚያስፈራ ገደል ላይ በተሰራች ቀጭን እና ጠመዝማዛ መንገድ በረረን…፡፡
በመሃል” ጥይት እየጨረስን ነው ጥይት ይዛችሁልን ኑ!” ተባልን፡፡
ሰፊ ወታደራዊ ካምፕ እንደመሆኑ ከሚመለከተው አካል ጥይት ጠይቀን ነጎድን፡፡
ፋኖዎቹ ፊት ላይ የሚታየውን ጉጉት ላስተዋለ እንደዛ እየበረረን ሄደን ቦታው ስንደርስ የሚጠብቀን ጥይት ሳይሆን ለሁላችንም የቤትና የቦታ ስጦታ ሊሰጠን ‘ቶሎ ድረሱ እንዳያመልጣችሁ!’ የተባሉ ነው የሚመስለው፡፡
“እውነትም አማራ ጦርነት ሰርጉ ነው” አልኩ በሆዴ፡፡
ዝም ብዬ መብሰክሰኬን ሲያይ ሾፈራችን ” አንዲ ዘፈን ልቀይርልህ?” አለኝ እና መልሴን ሳይጠብቅ “ኤፍሬም ይመችሃል ?”አለ፡፡
እኔ ለራሴ ውግያ ቦታው ስንደርስ ምን እንደሚፈጠር እያሰብኩ በሆዴ “ምን ቀን ነው ከእነኝህ ጉዶች ጋር የተዋወኩት!?” እያልኩ ስለልጆቼም እየተጨነኩ ነበር፡፡
“ኤፍሬም… አላውቀውም!” አልኩት በደንብ ሳላሳብበት፡፡
“ኤፍሬም ታምሩን አታውቀውም?!” አለኝና ሙዚቃውን ድብልቅ አድርጎ ከፈተው፡፡
“በተጧጧፈ ጦርነት ገብተን እንደ ገብስ ልንታጨድ የምንችልበት እድል ባለበት “እንደ ገብሱ ዛላ” የሚል ዘፈን ከፍቶ ያወያየኛል እንዴ?! ብዬ “ቀይረው!” አልኩት ፡፡
“ኢትዮጵያን የነካ አይኔን የነካ…. ግጠም አለኝ!” ….የሚለውን የመሃሪን ዘፈን ብልቅጥ አድርጎ ከፈተው፡፡
እውነት ነው!
አሁን ደካማ ጎኔ ኢትዮጵያ ስትነሳ ሞራላቸው በአንዴ ተጋባብኝ እና “አንደርስም እንዴ?!” ከሚሉት ወገን ሆኜ አረፍኩት!
ሄድን ሳይሆን በረርን!
ውግያው ከሚካሄድበት ኮረብታ ግርጌ ስንደርስ…ግን ፈተናዬ ጀመረ!
ሁሉም ወደ ጦርነቱ ስፍራ ለመድረስ ገና መኪናው እንደቆመ የጥይት ሳጥኖቹን ተሸክሞ አቀበቱን እንደሜዳ መሮጥ ጀመሩ…አንዲ የከተማ አይጥ በየት በኩል.. በምን አቅም ትከተል!?
….እንኳንስ የጥይት ሳጥን ልሸከም በያዝኳት መሳሪያ ውስጥ ያለውንም ጥይት የሚሸከምልኝ ባገኝ ደስ ይለኝ ነበር!
….ስፖርት አለመስራቴን የረገምኩበት ቀን ነበር……ልብና አካል አልተገናኝቶም!
ይበልጥ የሚጸጽተኝ ራሴ በሰኣቱ አለመድረሴ ሳይሆን ምርጥ ምርጥ የሚባሉትን እሳት ልጆች ከኔ ጋር አቆይቼ ሃይል ማጉደሌም ጭምር ነበር፡፡
የኮረብታው መሃል በመከራ ስንደርስ የመጀመሪያው ቁስለኛ ከላይ በሸክም ሲወርድ ተገናኘን…አመዴ ቡን አለ!…ከዛም ሁለተኛው ቁስለኛ…. ከዛም ሶስተኛው… …..
እንኳንስ እኔ ..አብረውኝ ያሉት በተደጋጋሚ በውግያ ያለፉት ልጆች ራሳቸው መጨነቅ ሲጀምሩ አየው….አፌን መረረኝ! …በቀደም ስማቸውን መዝግበን ጫማ፡ ኮዳ ወዘተ አሟልተን..ምሽግ ያስገባናቸው ልጆች ዛሬ እዚህ ግባ እንኳን በማይባል ቃሬዛ ደማቸው እየፈሰሰ እግሬ ስር ተኝተው ማየት ያማል…!
በዛ ላይ ጦርነትን እና ውጥንቅጡን በፊልም እንጂ በአካል አላውቀውም፡፡
አንዱ ቁስለኛ ልጅ “ውሃ አጠጣኝ ስለእግዚያብሄር!” አለኝ…እኔ ሙቀቱን ስለማልችለው ሁሌም አንድ የተጀመረ ሃይላንድ ከእጄ አይጠፋም…ከእግሬ ስር ቃሬዛ ላይ ተኝቶ አይኔን ወደ ላይ እያየ ሲለምነኝ በድንጋጤ “ኧረ ወንድሜን እንካ ጠጣ” ብዬ ልሰጠው ስል “ኧረ ውሃ አይሰጥም!” ብለው መነተፉኝ…
ከዚህኛው ቁስለኛ በኋላ የመጣ ቁስለኛ አልነበረም፡፡
ጦርነቱ ከሚካሄድበት ጫፍ ምንም አይነት መልእክት አይደርሰንም፡፡
እያሸነፍን ይሁን እየተሸነፍን ሳናውቅ እንዲሁ በጭንቀት አቀበቱን መውጣት ቀጠልን ….፡፡
ዝርዝሩ ለሌላ ጊዜ ይቆየንና በአጭሩ ህወሃት እኛ የነበርንበትን ምሽግ ለመደርመስ 80 ሰዎችን ለሙከራ በሚመስል መልኩ ልካ ነበር….ውግያው ሲጠናቀቅ ሁሉም አባላችን በቁጭት የሚያወራው ስለ አራት ስዎች ማምለጥ ብቻ ነበር፡፡ 76ቱ ወያኔዎች ወደ ቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትራቸው ተሸኝተዋል፡፡
ከመንገዴ 4 ቁስለኛ አይቼ ጨልሞብኝ የነበርኩት ሰው ጀግናዎቹ የሻለቃ ባዬ ፋኖዎች የሰሩትን ሳይ ከሚገባው በላይ ደስ አለኝ…!
.ሻለቃ ባዬ ቀናው ማለት የዘመናችን ዳግማዊ ቴድሮስ እንደማለት ነው… መሸነፍን አያውቃትም!
ድንገተኛ ጥቃት በተሰነዘረበት ወቅት በአካባቢው ደርሰው የማይተካ እርዳታ የሰጡት በሻ/ቃ ሀብቴ የሚመሩት ጀግና ፋኖዎች…በሻ/ቃ ሰፈር መለስ እንዲሁም በሻ/ቃ እሸቴ የሚመሩት ጀግኖች ፋኖዎች እንዲሁም በድንገት በተሰነዘረው ጥቃት ወዲያውኑ የከባድ መሳሪያ ሽፋን የሰጠው ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን ሁሉ ከፍተኛ ምስጋና ይገባቸዋል፡፡
እንግዲህ ከእሁድ ጀምሮ እዛው የነበርኩ በመሆኑ ወሬውን ላደርሳችሁ አልቻልኩም፡፡
ዛሬም እገዛችሁ ደርሶኛል፡፡
ከድንጋጤያችን (የደነገጥኩትስ እራሴ ብቻ ነኝ በርግጥ) ወጥተን ዛሬ ወደ ማደራጀቱ ተመልሰናል፡፡
በምስሉ የምትመለከቱትን ወሳኝ ቁሶች ገዝተን ወደ ምሽግ አድርሰናል፡፡
ያው ዛሬም እናንተን ማስቸገሬ ግን እንደቀጠለ ነው…
አሁን ላይ ብታግዙን ደስ የሚለንን የእርዳታ አይነት እዚህ ጋር መግለጽ ስለማልፈልግ አቅምና ፍላጎቱ ያላችሁ ሰዎች በውስጥ አናግሩኝ፡፡
ሌሎቻችሁም እርዳታችሁን ቀጥሉ
ኢትዮጵያ እንደ ልማዷ ታሸንፋለች!