>

መማርስ ውኃ ዋና!  (ክርስቲያን ታደለ)

መማርስ ውኃ ዋና! 

ክርስቲያን ታደለ

ይህን ሳልናገር ብቀር ታሪክም ይወቅሰኛል። እናም ለአገሬ ወጣቶች በተለይም ለአማራ ወጣቶች የምነግራችሁ ለእውነት የቀረበ ግምት ቢኖር ካሳለፍነው እና አሁን ካለንበት በእጅጉ የበረታ ወጀብ ከፊታችን እንደሚጠብቀን ነው። የማናስቀረው፥ የግድ ተፈትነንበት የምናልፈው ወጀብ…ሊያውም እጅጉን የበረታ ወጀብ ከፊታችን ይጠብቀናል። ወጀቡን የምንሻገረው እንዲሁ በእድል አይደለም። ይልቁንም ተፈትነን ነው። ፈተናውን እጅ ለእጅ ተያይዘን እንደአመጣጡ በመመለስ ብቻ የምናልፈው ነው። እንዳመጣጡ ለመመለስ ደግሞ መከላከያ ሰራዊቱን መቀላቀል የግድ የሚለን አማራጭ የሌለው ምርጫ ነው።
ፈተናው በአስኳላ ትምህርት ባለ የባለዲግሪ፣ ማሰተርስ፣ ዶክትሬትና የፕሮፌሰርነት ማዕረግ የሚታለፍ አይደለም። ፈተናው ወታደራዊ አቅምን በመገንባት ብቻ የሚታለፍ ነው። አልያ «ድጓ መና…ቅኔ መና…መማርስ   ውኃ ዋና» ያሉት መርጌታ እጣፈንታ ነው የሚገጥመን። ( ያለንበት ዘመን የመጨረሻው መጨረሻ ነው። የመጨረሻውን መጨረሻ መሻገር የሚችለው ወታደራዊ አቅምን በመገንባት ብቻ ነው። ከዚህ በላይ ብዙ…እጅግ ብዙ ባልኳችሁ በወደድሁ ነበር። ዳሩ በአደባባይ ለማውጋት የማይመች ሆኖ ነውና…ወጣቶች እባካችሁ…የመከላከያ ሰራዊቱን ተቀላቀሉና ለአገራችሁና ለምትወዱት ሕዝባችሁ ድረሱለት።
ዛሬ ኢትዮጵያን ለማፍረስና ሂሳብ እናወራርዳለን ብለው ወገኖቻችንን በገፍና በግፍ የሚጨፈጭፉ ድኩማኖች ይህን ያህል ፈተና የሆኑብን በታሪክ አጋጣሚ በአገር መከላከያ ሰራዊት የነበራቸውን ተሳትፎ አንፃራዊ ብልጫ በመጠቀም ነው። ነገ ተመሳሳይ ጥያቄ እያነሳን ሙሾ ልናወርድ ነወይ?
የግርጌ ማስታዎሻ፦
1) የቅኔ መና…ድጓ መና ሥርወ ታሪክ፦ መርጌታው መጽሐፈ ብሉያትን ከሀዲሳት ያካለሉ፣ አቡሻኸሩን የዘለቁ፣ ድጓውን የጠነቀቁና በቅኔው የመጠቁ ነበሩ አሉ። ከእለታት አንድ ቀን ወደ አማቶቻቸው ተጠርተው ሲሄዱ ወንዝ ይሞላባቸውና እርሳቸውንም ሆነ ባለቤታቸውን ማሻገር ያቅታቸዋል። ይህን የተመለከተ ኮበሌ «ላሻግራችሁ» የሚል ፍላጎቱን ያሳያል። ጥሪ የሚሄዱ ሙሽሮችን ለማሻገር ቃል የገባው ኮበሌ ሙሽሪትን ካሻገር በኋላ ታዲያ ቃሉን አክብሮ መርጌታውንም በማሻገር ፋንታ በሙሽሪት ላይ አባወራው መርጌታ አሻግረው እየተመለከቱ በአደባባይ  ነውር ይፈጽማል። መርጌታውም  በከፍተኛ የመጠቃት ቁጭት ስሜት ውስጥ ሆነው «ቅኔ መና…ድጓ መና…መማርስ ውኃ ዋና» አሉ ይባላል።
2) ይህን መልእክት ለወንድሞችና እህቶች መስከረም ላይ ነበር የተናገርነው። ዛሬ ላይ የትናንት ግምታችን ለእውነታው የበለጠ ቅርብ መሆኑን ነፍስ ያወቀ ሁሉ የተረዳው ነው። መልእክቱም ከትናንት ይልቅ ዛሬን በተሻለ የሚገልጽ እና ለአሁን እጅግ አስፈላጊ ሆኖ ስላገኘነው ነው በድጋሚ ያጋራነው።
የአገር መከላከያ ሰራዊትን ተቀላቀሉ!
Filed in: Amharic