>

"ቤርቤረሰቦችዬ ሶስቱ እስረኛ ጋዜጠኞች የትና በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ? ጥቂት ላውጋችሁ...??? (ዘመድኩን በቀለ)

ቤርቤረሰቦችዬ ሶስቱ እስረኛ ጋዜጠኞች የትና በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ? ጥቂት ላውጋችሁ…???
ዘመድኩ በቀለ

“ዛሬ ደግሞ ስለእነዚህ ሦስት ጋዜጠኞች መረጃ እስጣችኋለሁ። እናንተ ደግሞ ተወያዩበት። በወንጀላቸውም ላይ አስተያየት ስጡበት። 
 
ታሳሪዎቹ…  ነገዳቸው መቼም ይሄን ቃል ስጠቀም ደምብዛታቸው የሚቀሰቀስባቸው አሉ። ሆኖም ግን ሕገመንግሥታዊ መብት መሆኑን ደግሞ አንዘንጋ። “ሕገ መንግሥታችን” እኛን በብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦችነት” እንጂ በአበባ፣ ከበደ ስለማያውቀን ይሄ ሕገ መንግሥት በሥራ ላይ እስካለ ድረስ በዚያው እንቀጥላለን
ታሳሪዎቹ… 
 
• አንደኛው ታሳሪ ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ ነው።
• ሁለተኛው ታሳሪ ትግሬ ኢትዮጵያዊ
• ሦስተኛዋ ታሳሪ ደግሞ ዐማራ ኢትዮጵያዊት ናት። የብሔር ተዋጽኦው እንኳ ሲያዩት ተመጻፃኝ ይመስላል አይደል? 
 
… አሳሪው ደግሞ ባለ ጊዘው የኦሮሙማው መንግሥት ነው። 
 
…ታሳሪዎቹ አሁን የት ናቸው።  ከታች የተለጠፈውን ጦማር ያንብቡ። 
• በመጀመሪያ ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ  ‼
ወሬ ፩/አንድ 
ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ ፈይሳ
“… ያለፈው ሳምንት አርብ ከጠዋቱ 4:30 ላይ ነበር የአዲስ አበባ ፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ ፖሊሶች ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ ፈይሳን ከመኖሪያ ቤቱ በቀጥታ ወደ ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ይዘውት የሄዱት። ደንብ ነውና ቤተሰብም እስረኛው ወደተወሰደበት ፖሊስ ጣቢያ ሄደ። እዚያ እንደደረሱም ለእስረኛው መድኃኒትና ቅያሬ ልብስ ለመስጠት እንደመጡም ተናገሩ። ፖሊሶቹ ግን እንዲህ የሚባል እስረኛ አናውቅም። ጥፉ ከዚህ አሏቸው።
…ቤተሰብም ይቆዩና በማግሥቱ ባለፈው ቅዳሜ ጉዳዩን የያዘው የኦሮሚያ ፖሊስ ነው መባሉን ይሰሙና የእስረኛው ቤተሰቦቹ 6 ኪሎ ወደሚገኘው የኦሮሚያ ፖሊስ መምሪያ ያቀናሉ። በዚያም የለም ይባላሉ። ምንአልባት ብለው ቀጥሎም ግሎባል አካባቢ ወደሚገኘው የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ቢሮም ይሄዳሉ። በዚያም የለም። እኛ ጋር አልመጣም ይባላሉ።
…ቤተሰብ ተስፋ አልቆረጠም። ይቀጥሉና መጀመሪያ እስቲ ወደ ቡራዩና ገላን ከተሞች ሄዳችሁ አጣሩ የሚል ምክር የሰሙት የታሳሪው ቤተሰቦች ወደዚያው በማቅናት በቡራዩ ከተማ በሚገኙ ሦስት ፖሊስ ጣቢያዎች ይጠይቃሉ። በዚያም የለም ይባላሉ። ከዚያም ደግሞ ገላን ኮንዶሚኒየም አካባቢ ወደ ሚገኘው የኦሮሚያ ፖሊስ ጣቢያ ያቀናሉ። በዚያም የለም ይባላሉ።
…የጋዜጠኛ ታምራት ነገራ ፈይሳ ቤተሰቦቹ እንደገና በትናንትናው ዕለት ተመልሰው ወደ ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ በማምራት ልጃችን የታሰረበት ይነገረን? የሚል ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን ጣቢያውም “ጉዳዩን የያዘው የኦሮሚያ ፖሊስ ነው” አድራሻውን ተሳስታችሁ ስለሚሆን እንደገና ገላን ሄዳችሁ አጣሩ የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ገልፀዋል። አሁን ጋዜጠኛ ታምራት የታሰረበትን ቦታ ባለማግኘታቸው ቤተሰቡ ለእስረኛው መድኃኒትና ምግብ እንኳን ማድረስ እንዳልቻሉና በዚህም የተነሣ ከፍተኛ የሆነ ጭንቀት ውስጥ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
“… ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ… በወያኔ ህወሓት፣ በሻአቢያ፣ በኦነግ፣ በጠሚኮ ዐቢይ አሕመድ፣ በሽመልስ አብዲሳ፣ በኦህዴድና በኢዜማ ጥርስ ውስጥ የገባ ጋዜጠኛ ነበር። ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የዐቢይ አሕመድና የታከለ ኡማ የግል እስረኛ እንደነበረው ሁሉ ጋዜጠኛ ታምራትም አሁን የብዙ ቂመኞች የሽመልስ አብዲሳ የግል እስረኛ መሆኑ ነው የሚነገረው።
… አዲስ አበቤ ጉድሽ ፈላ አለ አጎቴ ሌኒን። እያንዳንድሽ አዲስ አበባ ትያዢያለሽ ፊኒፊኔ ትታሰሪያለሽ በኦሮሚያ ትዳኚያለሽ። ከኑማ ጋ ዱቢን።
ወሬ ፪ /ሁለት 
ጋዜጠኛ ክብሮም ወርቁ አብርሃ 
…ይሄ ደግሞ የአሐዱ ሬዲዮ ዜና አርታኢ ነው። በሥራው ላይ ሳለ ስህተት ሠርተሃል ተብሎ ይጠረጠርና ወደዘብጥያ ይወርዳል። በዚያም የሃገሪቱ ሕግ በሚፈቅድለት መልኩ ጠበቃ ቀጥሮ ይከራከራል። ፍርድቤቱም በዋስትና ይፈታና በውጭ ሁኖ ይከራከር ብሎ ይወስናል። በውሳኔውም መሠረት የታሳሪው ወላጅ አባት ፍርድቤቱ ለዋስትና የጠየቀውን 15ሺ ብር ከፍለው፣ የመፈቻ ወረቀቱን ይዘው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ግቢ ቆመው የልጃቸውን መፈታት በጉጉት ይጠባበቃሉ። የልጃቸውን መፈታት መጓጓታታቸውን  ያየው የዐብይ አሕመድ የፖሊስ ተቋም ግን ታሳሪውን ከመፍታት ይልቅ” የምንአባቱንስና ፍርድቤት ውሳኔ ነው” በሚል መንፈስ እስረኛውን በሚኒባስ መኪና ጭኖ ወደ ሌላ ወዳልታወቀ ሥፍራ ይሰውረዋል።
… ቤተሰብ መልሶ የክስ ማመልከቻ ይዞ ፍርድ ቤት ይቀርባል። ተከሳሹ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንም ፍርድቤት ይቀርባል። ለተከበረው ፍርድ ቤትም እንዲህ ይላል። “የአሐዱ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ዜና አርታኢ የሆነው ክብሮም ወርቁን ከእስር ፈተነዋል። አሁን የት (የትአባቱ እንዳለ ቁጠሩት) እንዳለ አናውቅም። በማለት ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያስታውቃል። የጋዜጠኛው ቤተሰቦች በበኩላቸው ደግሞ ልጃቸው ጋዜጠኛ ክብሮም ከ26 ቀናት በፊት በፍርድ ቤት ከእስር እንዲለቀቀ ቢወሰንለትም እስካሁንም ያለበትን እንደማያውቁ ለፍርድ ቤቱ ይገልጻሉ።
…ጋዜጠኛው “ጭራሹኑ ከእስር አልተፈታም” የሚል እምነት ያላቸው የክብሮም ቤተሰቦች፤ ጉዳዩን ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የወሰዱት ባለፈው ህዳር ወር አጋማሽ ነበር። በክብሮም ጠበቃ አቶ ጥጋቡ ደሳለኝ አማካኝነት ለፍርድ ቤቱ የቀረበው አቤቱታ፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን “የፍርድ ቤት ውሳኔ ባለማክበር፣ ግለሰቡን በኃይል አስገድዶ በመያዝ ከእስር ቤት እንዳይፈታ ከልክሏል” የሚል ነው።
በዚህ መሰረት ጠበቃው “አካልን ነጻ የማውጣት “( habeas corpus) አቤቱታ በመመስረት ጋዜጠኛው ከእስር እንዲፈታ ለፍርድ ቤት አቤት ብለዋል። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንም ትናንት ታህሳስ 4፤ 2014 ዓም ለፍርድ ቤቱ በጽሑፍ ባቀረበው መልስ “[ተጠርጣሪው] በኮሚሽኑ በሚገኙ የተጠርጣሪ ማቆያም ሆነ በኮሚሽኑ እውቅና ስር የሌለ” መሆኑን ገልጿል። አከተመ።
…የዳግማዊ ደርግ፣ የዳግማዊ ወያኔ፣ ሥርዓት ሳታስፎግር ከች ያለች ይመስላል። የጋዜጠኞቹ የእስር አያያዝና የፍትህ ሥርዓቱም ወደ ቀደመ ማንነቱ ሳይመለስ እንዳልቀረ ማሳያ ነው ተብሏል። የኢንሳ አለቃ ሆነው ፖለቲከኞችን፣ ጋዜጠኞችን ወደ ዘብጥያ በማውረድ ይታወቁ የነበሩት ዐቢይ አሕመድ አሁን ጭራሽ የሃገሪቱ መሪ አዛዥ ናዛዥ ሆነዋል። እናም ተኩላው የበግ ለምድ ለብሶ መቆየት አልቻለም። ለምዱ ተገፈፈ የሚሉም አሉ። አሁን ይሄ ሁሉ ሆኖ ሳለ ግን የዐብይ አሕመድ መንግሥት የግሉ አድናቂዎች፣ ቅንድቡንና ቁመቱንም፣ ከንፈሩንም የሚያደንቁ በአብዛኛው ሴቶች ናቸው በእሥረኞቹ ላይ ሲያሾፉ እየታዩ ነው። “እሰይ ደግ፣ እንኳንም ታሰሩ” የሚሉ ቀፋፊ ድምጾችንም ሲያሰሙም ይደመጣሉ። ትናንት የመለስ ዜናዊን መንግሥት ጋዜጠኞችን አሰረ ብለው ካልታነቅን ብለው ለገላጋይ ያስቸግሩ የነበሩ “ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን” ዛሬ በተራቸው ጋዜጠኞቹ ይፈቱ ማለቱን የዐቢይ ውለታ ሼም አስይዟቸው “ይፈቱ” ባይሉ እንኳ። “እገሌ ይታሰር፣ እገሊት ትቀፍደድ፣ ብለው ራሳቸውን ባያዋርዱ መልካም ነው የሚሉም አሉ። የትኛውም ሥርዓት ይወድቃል። የማይወድቀው ሃገርና ህዝብ ነው። ሥርዓት ይለወጣል። ይሄዳል። ይመጣል። ይተካልም።
…በመጨረሻም ሰሞኑን የገሌው ቤተኛው ኢሳት” ጋዜጠኞች ለዘገባ ኦሮሚያ ክልል ይሄዳሉ አሉ። ለዚያውም እዚሁ ቅርብ ሰበታ ነው አሉ የሄዱት። እዚያ እንደደረሱ የኦሮሚያ ፖሊስ ሰብስቦ እስር ቤት ያጉራቸዋል። ቢባል ቢባል ማን ይስማ። እንዲያውም ፖሊሶቹ በማን ፈቃድ ወደዚህ ክልል መጣችሁ? ብለው ከመጠየቅ አልፈው “እስቲ ዐቢይ መጥቶ ሲያስፈታችሁ እናያለን? ” ወደሚል ኃይለቃል መግባታቸው ተነግሯል። በመጨረሻም ዛር ወጥቶ፣ ተንቀጥቅጦ በስንት አማላጅ ኢሳት ጋዜጠኞቹን ከሰበታ ፖሊስ ጣቢያ ማስፈታቱ ተነግሯል።
… ወዳጄ ይሄ ምልክት ነው። መጪው ጊዜ ከባድ ስለመሆኑ ምልክት ነው። በተለይ ኦሮሚያ ውስጥ ኦነግ እና ኦህዴድ በሥልጣን ሽሚያ ሲሉ ክልሉን ብቻ ሳይሆን ለሃገሪቷም ጠንቅ ሳይሆኑ እንደማይቀሩ የሚሰጉ አሉ። ሙስና፣ ዘረፋ በኦሮሚያ ፖሊስ ሕጋዊ እስኪመስል ድረስ ተስፋፍቷል። አዲስ አበባን ወደ ፊንፊኔነት ለመቀየር ሲባል አንዳን እርምጃዎች መውሰድም ይጀመራል። ከእነዚህ እርምጃዎች መካከከልም አሁን እንደሚደረገው አዲስ አበባ ትያዛለህ። ኦሮሚያ ታስረህ እዚያው ትዳኛለህ። ከዚያ ለቁቤ ማመልከቻ 2ሺ ብር ትከፍላለህ። እንቢ ካልክ ከመረረህ ወይ ወደ ደብረ ብርሃን አልያም ወደ ደብረ ማርቆስ ትሰደዳለህ። ወደ ጉራጌም እንዳትሄድ በዚያም ሽግር አለ።
• ምን ተሻለህ አዲስ አበቤ?
ወሬ፫/ሦስት
ጋዜጠኛ መዓዛ መሀመድ 
…ታህሳስ 2/2014 ዓም ሁለት የአዲስ አበባ ፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ ፖሊሶች ንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ጆሞ አካባቢ ጠዋት ላይ ጋዜጠኛ መዓዛ መሀመድን ለጥያቄ ትፈለጊያለሽ ለጊዜው ቤተሰብ ወዳላወቀው ስፍራ ትወሰዳለች። ቆይቶም በማግስቱ የጋዜጠኛዋ ባለቤት አቶ ሮቤል ገበየሁ መዓዛ የታሰረችው ሰሜን ማዘጋጀ አካባቢ በሚገኘው የቀድሞው 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ መሆኑን ያረጋግጣል።
…በማግሥቱም ታህሳስ 2 ቀን 2014 ዓም ከቀኑ 9 ሰዓት በኋላ መኖሪያ ቤቷም በፖሊስ መፈተሹንና ምንም ዓይነት የወንጀል ነገር አለመገኘቱን በምስክር መረጋገጡን ጭምር ባለቤቷ ለዜና ሰዎች መናገሩም ተዘግቧል።
… ባለቤቷ ሮቤል እንደተናገረው ከሆነ መአዛን በታሰረችበት ፖሊስ ጣቢያ በአካል አግኝቶ እንዳነጋገራትና መዓዛም በአካሏ ላይ ምንም አይነት የደረሰባት አካላዊ ጉዳት እንዳላየባት የገለጸ ሲሆን ይህን ለማረጋገጥና ለማየት የሚፈልግ ሰው በጣቢያው አሰራር መሰረት እሁድ እና ማክሰኞ ከጠዋቱ 2 ሰዓት እስከ ቀኑ 7 ሰዓት ድረስ ማንኛውም ሰው ሊጠይቃት እንደሚችልም ጠቁሟል።
“… ጋዜጠኛ መዓዛ መሀመድ በሁሉ ዘንድ የምትታወቀው በዐማራነታቸው ምክንያት ታግተው ደብዛቸው ስለጠፉት 17ቱ የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርስቲ የዐማራ ተማሪዎች ጉዳይ ላይ በምታደርገው የማያቋርጥ ጩኸትና ዜጎች በተለይ ዐማራው ጉዳት ደረሰበት በሚባልባቸው ሥፍራዎች ሁሉ በአካል በመገኘት ከፈረሱ አፍ መረጃ በማቀበል ነው። ጋዜጠኛና መምህርት መዓዛ መሀመድ ደፋር፣ አስሬ ለክታ አንዴ የምትቆርጥ፣ ሆዷ የማያሞኛት፣ ገሌ የማያስገባት ጋዜጠኛ ናት።
• ጋዜጠኛዋ ትታሠር ይሉ የነበሩ ሁሉ አሁን ሰላም እንዳገኘ ሰው ተንፋስ ብለዋል። ደግነቱ የወደፊቱ መከራና በተለይ ቀጥሎ ከወደ ኦሮሚያ የሚመጣው ችግር የሚመርጠውና የሚምረው፣ የሚያስተርፈውም ያለመኖሩ ነው። ዛሬ ጭራቸውን ቆልፈው ከብልፅግናው መንግሥት ጋር አንሶላ ካልተጋፈፍን ሞተን እንገኛለን የሚሉ በሙሉ ነገ ደም እምባ ያለቅሳሉ።
…የሚገርመው ነገር ዛሬ በመላው ዓለም #Nomorre እያሉ ከምር ለሃገራቸው ክብር የሚታገሉ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ይሄንን ይዘው፣ ተሸክመውና ለብሰው አደባባይ ይዘው የሚወጡትን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አንዳቸውም በኢትዮጵያ በአዲስ አበባ በተለይም በኦሮሚያ ይዘው መውጣት አይችሉም። የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ አይደለም ማውለብለብ… በግንባርና በእጅ ላይ ማሰር፣ በነጠላ ጫፍም ላይ በጥለት መልክ አሠርቶ መልበስ ዋጋ ያስከፍላል። ይህን የማያውቁ ያሳዝኑኛል። እያወቁ የሚያሽቋልጡ ደግሞ ያስቁኛልም ያሳቅቁኛልም።
… በሰላም ዋሉልኝ።
Filed in: Amharic