>

ዐብይ አሕመድና ጌታቸው ረዳ (መስፍን አረጋ)

ዐብይ አሕመድና ጌታቸው ረዳ 

 መስፍን አረጋ


በኢትዮጵያ ውስጥ የቋንቋ እንጅ የዘር ልዩነት የለም፡፡  የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ ሰርገኛ ጤፍ ቅይጥ፣ ውጥንቅጥ ስለሆነ፣ በዘር ወንፊት ቢነፋ ንጹሕ ትግሬ፣ ንጹሕ አማራ፣ ንጹሕ ኦሮሞ ተብሎ ተንጓሎ የሚቀር ማንም – እደግመዋለሁ – ማንም የለም፡፡  ለምሳሌ ያህል የወርቅ ዘር ነኝ እያለ አጉል ይታበይ የነበረው መለስ ዜናዊ፣ ካንድ የከምባታ ሰው ጎን ቢቀመጥ በመልኩ ብቻ ማንም ሊለየው አይችልም፡፡  የኦሮሞ ብሔርተኛውን ለማ መገርሳን ደግሞ ቦረኔ ነው ከማለት ይልቅ ብቸኔ ነው ማለት ይበልጥ ያሳምናል፡፡  

ውጥንቅጥነትን በተመለከተ ደግሞ ከሁሉም ኢትዮጵያውያን በላይ ውጥንቅጥ የሆኑት ትግሬወችና ኦሮሞወች ናቸው፡፡  ትግሬ ክፍለ ሀገር የጦርነት ቀጠና እየሆነች አያሌ ወታደሮችን ስላስተናገደች ትግረኛ ተናጋሪወች ዝንቅ፣ ዝንቅንቅ ናቸው፡፡  አሮሞ ከሚባለው ውስጥ ደግሞ ከዘጠና በመቶው በላይ በደሙ ኦሮሞ ያልሆነ፣ ከጭፍጨፋ መልስ ማንነቱን ሳይወድ በግዱ የተነጠቀ፣ የሞጋሳና የጉዲፈቻ ሰለባ ነው፡፡   ስለዚህም እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ዘረኝነትን ከማንም በላይ መታገል የነበረባቸው ትግሬወችና ኦሮሞወች ነበሩ፡፡  

በተቃራኒው ግን የትግረኛና የኦሮምኛ ተናጋሪወችን እንወክላለን የሚሉት ወያኔወችና ኦነጎች ጉጠኝነትን ሙጭጭ ብለው፣ ኢትዮጵያን ሲያምሱና ሲያተራምሱ ግማሽ ምዕተ ዓመት አሳለፈዋል፡፡  ጎጠኝነትን ሙጭጭ ያሉት ደግሞ ምንም እውቀት የማይጠይቅ ቀላል የመንጋ መንጃ ስለሆነ ነው፡፡  በዚህ ረገድ ደግሞ ጴንጤነትና ጎጠኝነት መመሳሰል ብቻ ሳይሆን ይመጋገባሉ፡፡  ወያኔወች ተዋሕዶን ነክሰው የያዙት፣ ኦነጎች ደግሞ የጴንጤ ፓትርያርኮች የሆኑት በዚሁ ምክኒያት ነው፡፡          

በጎጠኞቹ በወያኔወችና በኦነጎች ዘንድ የመጨረሻው መለኪያ ዘር እንጅ ተግባር አይደለም፡፡  ሙሉ ትግሬ የሚባል ያለ ይመስል፣ ሙሉ ትግሬ አይደለም የሚባል ግለሰብ በወያኔወች ዘንድ ሙሉ ተቀባይነት የለውም፡፡  ሙሉ ትግሬ ባለመሆኑ ብቻ በሙሉ ልብ አይታመንም፡፡  ስለዚህም እንደዚህ ያለ ሰው ሙሉ ትግሬ ከሚባሉት በላይ ወያኔ ቢሆንም፣ የመጨረሻ እጣው ግን ባንድም በሌላም ሰበብ በፀረ ትግሬነት ተፈርጆ፣ ወጉዝ ከመ አርዮስ መባል ነው፡፡  ግለሰቡ አማራነት ካለበት ደግሞ እድለኛ ከሆነ ባዶ ስድስት ውስጥ ጨለማ ቤት ይታጎራል፣ ካልሆነ ደግሞ ከነነፍሱ ይቀበራል፡፡  

በተመሳሳይ መንገድ ሙሉ ኦሮሞ የሚባል ያለ ይመስል፣ ሙሉ አሮሞ አይደለም የሚባል ግለሰብ፣ በኦነጋውያን ዘንድ ሙሉ ተቀባይነት የለውም፡፡  ሙሉ ኦሮሞ ባለመሆኑ  ብቻ በሙሉ ልብ አይታመንም፡፡  ስለዚህም፣ እንደዚህ ያለ ሰው ሙሉ ኦሮሞ ከሚባሉት በላይ ኦነጋዊ ቢሆንም፣ ትንሽ ስሕተት ቢፈጽም ግን ተሳስቶ ሳይሆን አውቆ ነው ይባልና ባባገዳወች ተረግሞ አር የነካው እንጨት ይደረጋል፡፡   ግለሰቡ አማራነት ካለበት ደግሞ እድለኛ ከሆነ ተዘቅዝቆ ይሰቀላል፣ ካልሆነ ደግሞ ከነነፍሱ ቆዳው ይገፈፋል፡፡  ለዚህ ደግሞ አያሌ ምሳሌወችን መጥቀስ ቢቻልም፣ ዋና ዋናወቹን ብቻ እናወሳለን፡፡  እነሱም በረከት ስምዖንጌታቸው ረዳ እና ዐብይ አሕመድ ናቸው፡፡  

የወያኔን ፀራማራ አጀንዳ በማራመድ ረገድ ከራሱ ከመለስ ዜናዊ በላይ ትልቁን ሚና የተጫወተው በረከት ስምዖን ነው፡፡  እነ አዲሱ ለገሰን፣ ተፈራ ዋልዋን፣ አለምነው መኮንንን፣ ከበደ ጫኔን፣ ተመስገን ጥሩነህንደመቀ መኮንንን፣ … የመሳሰሉትን አማራ ነኝ ባይ ፀራማሮች፣ በብአዴን ቁልፍ፣ ቁልፍ ቦታወች ላይ አስቀምጦ፣  በአማራ ሕዝብ ላይ መርገምት ያወረደው፣ ይህ ጎንደር ውስጥ ተወልዶ ያደገ፣ የበላበትን ወጭት ሰባሪ እኩይ ግለሰብ ነው፡፡  በረከት ስምዖን ግን ተጋሩ ሳይሆን ኤርትራዊ ስለሆነ፣ ወያኔወች ያዩት የነበረው እስከጣፈጠ ድረስ ተላምጦ እንደሚተፋ አገዳ ነበር፡፡  በዚህ ምክኒያት ነው በረከት ሲታሰር ምንም ያላሉትና፣ ከታሰረም በኋላ እንዲፈታ ውስጥም ውጭም ያሉት ትግሬወች አንድም ቀን ጠይቀው የማያውቁት፡፡  በተቃራኒው ግን ክንፈ ዳኘው ተራ ሌባ ቢሆንም ትግሬ በመሆኑ ብቻ፣ የሱ መታሰር ወያኔወችን እንደ እግረ እሳት አንገብግቦ እንደ ግሪሳ አንጫጭቷቸዋል፡፡ 

  አሁን ላይ ደግሞ በበረከት ቦታ ተተክቶ ወያኔን ቀጥ አድርጎ የያዘው አፉ ያልተገራ ቢሆንም፣ አንደበተ ርቱዕ የሆነው ጌታቸው ረዳ ነው፡፡  ጌታቸው ረዳ ግን ሙሉ ትግሬ ስላልሆነ፣ ይባስ ብሎ ደግሞ አማራነት ስላለበት፣ ወቅቱ ሲደርስ ጉሮሮውን ተይዞ የሚታረድበት ቢላዋ ተስላ ተቀምጣለች፡፡  መታረዱ አይቀሬ እንደሆነ ደግሞ ካሁኑ ምልክቶች መታየት ጀምረዋል፡፡ ወያኔ በጦር ሜዳ በለስ የቀናው ሲመስል የወያኔ ጀነራሎች ይሞገሳሉ፣ በፋኖወች ሲወቀጥ ደግሞ ጌታቸው ረዳ ይወቀሳል፡፡   

የበረከት ስምዖን ምልምሎች የሆኑት ፀራማራ ብአዴኖች፣ ከዐብይ አሕመድ ጋር በመመሳጠር ሻጥር ካልሠሩበት በስተቀር፣ የአማራ ሕዝብ ወያኔን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚቀብረው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡  ያን ጊዜ ደግሞ ወያኔወች ሽንፈቶቻቸውን ሁሉ በጌታቸው ረዳና በመሰሎቹ ላይ ያላክኩና፣ በአማራ ሕዝብ ከመቀበራቸው በፊት፣ ጌታቸው ረዳን የአማራ ባንዳ ብለው ይቀብሩታል፡፡  

ወያኔ በለስ ቀንቶት ቢያሸንፍ እንኳን የአማራነት ደም ባለው ሰው ተመርቶ አሸነፈ እንዳይባል ስለሚፈራ ብቻ፣ ጌታቸው ረዳን ወይ ይበውዘዋል አለያም ይገንዘዋል፡፡  ለምሳሌ ያህል፣ወያኔ በ1991 አዲሳባን እንዲቆጣጠር ያንበሳውን ሚና የተጫወቱ የአማራ አዋጊወቹ ነበሩ፡፡  ወያኔ ግን አዲስ አበባን እንደሚቆጣጠር እርግጠኛ እየሆነ ሲመጣ፣ በአማራ አዋጊወች እየተመራ አዲስ አበባን ተቆጣጠረ እንዳይባል፣ የአማራ አዋጊወችን ስም እያፈነ እዚህ ግባ ይባል ያልነበረውን የሃየሎም አርአያን ስም ማግነን ጀመረ፡፡  ስለዚህም፣ ወያኔ በለስ ቀንቶት ቢያሸንፍ፣ የትግሬ ወጣቶችን ፈንጅ እያስረገጠ የሚያሰጨፈጭፈው፣ በቁሙ የተኮነነው ጻድቃን ገብረተንሳይ ትግሬ በመሆኑ ብቻ ዳግማዊ ሃየሎቸም ተብሎ አለመጥን ይገንና፣ ጌታቸው ረዳ ግን አሮጌ ቁና ተብሎ ተሸንቀንጥሮ ይጣላል፡፡  

ጌታቸው ረዳ፣ በየቀኑ እየወጣ ከአማራ ጋር ሒሳብ እናወራረዳለን፣ ሲኦል እንወርዳለን እያለ የሚቅለበለበው ወዶ ሳይሆን፣ በወያኔወች ዘንድ እንደሚጠረጠር ስለሚያውቅ ጥርጣሬውን ለማስወገድ ነው፡፡  ወያኔወች የሚጠረጥሩት ግን በተግባሩ ሳይሆን በዘሩ ስለሆነ፣ የፈለገውን ያህል አማራን ቢዘልፍና በአማራ ላይ ቢዝት እንዳይጠረጥሩት ማድረግ አይችልም፡፡  ባጨሩ ለመናገር፣ ጌታቸው ረዳ ማለት ካራጁ ጋር የሚውል በሬ ማለት ነው፡፡

ቀጥለን ደግሞ ወደ ኦነግ እንዙርና ስለ ኦነጋዊው ዐብይ አሕመድ ጥቂት እናውሳ፡፡  ዐብይ አሕመድ ኦነጋውያን በመቶ ዓመታት እንፈጽመዋልን ብለው ሊያስቡት ቀርቶ ሊያልሙት የማይችሉትን፣ በረቀቀ የሽንገላ ክሂሎቱ በሦስት ዓመታት ብቻ በመፈጸም፣ ከሞላ ጎደል ሁሉንም የጦቢያ ነገር የኬኛ፣ በኬኛ ለኬኛ ያደረገ ታላቅ ኦነጋዊ ነው፡፡  ባጭሩ ለመናገር  ዐብይ አሕመድ ማለት የሦስት ሺ ዓመት አገር በሦስት ዓመት ያፈራረሰ የሉባወች ሉባ ነው፡፡     

ዐብይ አሕመድ ግን የአማራ ደም አለበት ይባላል፡፡  ይባስ ብሎ ደግሞ ከአማራ ጋር ተጋብቷል፡፡   በዚህም ምክኒያት ጎጠኞቹ ኦነጋውያን ዐብይ አሕመድን መቸም ቢሆን በሙሉ ልብ አያምኑትም፡፡  ግማሽ ኦሮሞ ነው የሚሉት ዐብይ አሕመደ የሚሠራላቸውን ፀራማራ ሥራ፣ ሙሉ አሮሞ  ነው የሚሉት ለማ መገርሳ መሥራት ቢችል ኖሮ፣ ከጥርጣሬያቸው ለመገላገል ሲሉ ዐብይ አሕመድን ባስቸኳይ ቢያስወግዱት ደስታውን አይችሉትም፡፡  ቸግሩ ግን ለማ መገርሳ የዐብይ አሕመድን ያህል አጭበርባሪ ስላልሆነ፣  አማራን የማታለልና የመሸንገል (confuse and convince) ችሎታው እስከዚህም መሆኑ ነው፡፡  ስለዚህም አማራን እያታለለና እየሸነገለ ሙሉ በሙሉ እስኪያዳክምላቸው ድረስ፣ ኦነጋውያን ዐብይ አሕመድን ሰማይ ይሰቅሉታል፡፡  አማራ ያለቀለት ሲመስላቸው ግን፣ የዐብይ አሕመድ ሥራ ስለሚያልቅ፣ ሰማይ የሰቀሉትን ዐብይ አሕመድን መሬት አውርደው ይፈጠፍጡታል፡፡  

  ራሱ ዐብይ አሕመድም እስከጣፈጠ ድረስ ተላምጦ፣ ጥፍጥናው ሲያልቅ ተነቅሮ የሚተፋ የኦነጋውያን ሸንኮራ አገዳ መሆኑን በደንብ ያውቃል፡፡  እናቴ አማረኛ የማታውቅ ኦሮሞ ናት፣ ኦሮሙማነቴን ማንም ሊሰጠኝ አይችልም፣ ምንትሴ፣ ቅብጥርሴ እያለ ሳይጠይቁት የሚቅለበለበው፣ ኦነጋውያን እንደማያምኑት ስለሚያውቅ ነው፡፡     

ዐብይ አሕመድ በአማራ ጥላቸው ወደር የሌለው ኦነጋዊ አውሬ ቢሆንም፣  ሙሉ ኦሮሞ ስላልሆነ ብቻ በኦነጋዊነቱ ሁልጊዜም እንደሚጠረጠርና ባይነ ቁራኛ እንደሚጠበቅ፣  እያንዳንዷ ድርጊቱ በዘር መነጽር እንደምትመረመር፣ ትንሽ ቢሳሳት ግዙፍ ውለታው መና ቀርቶ ከሃዲ ተብሎ ተዘቅዝቆ እንደሚሰቀል ወይም ደግሞ ከነነፍሱ ቆዳው እንደሚገፈፍ ነጋሪ አያስፈልገውም፡፡  ስለዚህም ኦነጋውያን ትናንት ከሚያምኑት የበለጠ ዛሬ እንዲያምኑት ከፈለገ ትናንት ካደረገው የከፋ ዛሬ ማድረግ አለበት፡፡  ይህ ማለት ደግሞ ዐብይ አሕመድ በአማራ ሕዝብ ላይ የበለጠ እና የበለጠ ጭራቅ እየሆነ ይሄዳል ማለት ነው፡፡  

በሌላ አነጋገር ዐብይ አሕመድ በማንነቱ ምክኒያት እኩይ አዟሪት (vicious circle) ውስጥ የገባ ኦነጋዊ ሳጥናኤል ነው፡፡  ካዟሪቱ ነጻ የሚያወጣው ደግሞ ሞቱ ብቻ ነው፡፡  ስለዚህም ዐብይ አሕመድ ከእኩይ አዟሪቱ ወጥቶ፣ ኦነጋዊነቱን ትቶ፣ ኢትዮጵያዊነትን በንግግር ብቻ ሳይሆን በተግባር ያራምዳል ብላችሁ የምትመኙ የዋህ አማሮች፣ ከእባብ እንቁላል እርግብ እየጠበቃችሁ መሆናችውን ተረድታችሁ፣ ቁርጣችሁን አውቃችሁ፣ አርማችሁን አውጡ፡፡  አንዴ ቢያጭበረብራችሁ ወራዳነቱ የሱ የራሱ ነው፣ ሁለቴ ቢደግም ግን ጥፋተኞቹ እናንተው ራሳችሁ ናችሁ፡፡  

 

ዐብይ አሕመድ ዐሊ የኦነጉ ኦቦ

አፉና ምግባሩ ሐራምባና ቆቦ፡፡

በቅቤ ምላሱ እያሙለጨለጨ

ድፍን ያማራን ሕዝብ በደረቁ ላጨ፡፡

እንዴ ቢያጭበረብር የሱ ነው ኀፍረቱ

ሁለቴ ቢደግም የኛ ነው ጥፋቱ፡፡ 

ዐብይ አሕመድ በብዙ ረገዶች የመለስ ዜናዊ ካርቦን ቅጅ ነው፡፡  ትልቁ ልዩነታቸው መለስ ዜናዊ ስሜቱን መደበቅ የማይቸል ግልፍተኛ፣ በዚያ ላይ ደግሞ ላፉ ለከት የሌለው ስድ መሆኑ ነው፡፡  መለስ ዜናዊ አዋቂ ሳይሆን የሚያቃትን ትንሿን ነገር አሰማምሮ በማቅረብ ሰወችን (በተለይም ደግሞ ፈረንጆችን) አስማምቶ የሚሸጥ አራዳ ወይም ጮሌ (street smart) ነበር፡፡  ዐብይ አሕመድ ደግሞ ከዚህም ከዚያም የለቃቀማትን ጥራዝ ነጠቅ እውቀቱን በቅቤ አፉ እያወዛ አዋቂ መስሎ፣ አላዋቂወችን በደረቁ የሚላጭ የመርካቶ ዱርየ ነው፡፡  ዙርያውን የከበቡት ደግሞ አርባ ሚሊየን ብር ባካውንቴ ውስጥ ያስገባልኝን ሰው አላውቅም፣ ሁለት ሚሊየን ብር ታክሲ ውስጥ ጥየ ወረድኩ እያሉ ዓይናቸውን በጨው አጥበው የሚዋሹ ኦነጋዊ ኪስ አውላቂወች ናቸው፡፡     

ዐብይ አሕመድ አዋቂ የሚመስል አላወቂ መሆኑን በይፋ የሚመሰክርበት ደግሞ ፀራማራ ተግባሩ ነው፡፡  እርካብና መንበር የተሰኘው መጽሐፉ በግልጽ እንደሚያሳየው፣ የዐብይ አሕመድ ሂወት ሙሉ በሙሉ የሚሽከረከረው የስልጣን አራራውን በማርካት ዙርያ ነው፡፡  ለዐብይ አህመድ ስልጣን ይጠቅም የነበረው ደግሞ በነቂስ የደገፈውን የአማራን ሕዝብ ይበልጥ አጠናክሮ፣ ግማሽ አማራ በመሆኑ ምክኒያት የሚጠራጠሩትን ኦነጋውያንን እንዲቆጣጠርለት ማድረግ ነበር፡፡  በተቃራኒው ግን ላይጠራጠሩት የማይችሉትን ኦነጋውያንን እንዳይጠራጠሩት በማሰብ አማራን ጨፍጭፎ ባማራ በመተፋት ከሁለት ያጣ ጎመን ሆነ፡፡   

ሰፊው የአማራ ሕዝብ ሊያመልከው እየዳዳው እንደ መሲህ ወይም ሙሴ ሲመለከተው፣ የኢትዮጵያዊነት ምሰሶ በሆነው በአማራ ሕዝብ እየታገዘ፣ የጎጠኝነትን ወንዝ አሻግሮ፣ ኢትዮጵያን ወደ ቃልኪዳን ምድር በማስገባት ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ መጎናጸፍ ሲችል፣ ጥቂት የኦሮሞ ጽንፈኞችን ለማስደሰት ሲል ብቻ ራሱን በራሱ አዋረደ፡፡  እንደ ፈጣሪ አምኖት ደረቱን ለጥይት ሊሰጥለት ዝግጁ የነበረው ሰፊውን የአማራን ሕዝብ ጥሎ የማያምኑትን ኦነጋውያንን አነሳ፡፡  እንደ አህያ ስጋ አልጋ ሲሉት ዐመድ አለ፡፡   

ዐብይ አሕመድ፣ ዐብይ አሕመድ

ያህያ ሥጋ ባልጋ ሲሉት ባመድ፡፡ 

ዐብይ አሕመድ ጥራዝ ነጠቅ ጥቅሶችን እየጠቀሰ አዋቂ መስሎ ለመታየት እንደሚሞክረው እውነትም አዋቂ ቢሆን ኖሮ፣ እሱ ያገኘውን ዓይነት እድል አግኝተው ዕድሉን በትክክል በመጠቀም ዘላለማዊ ታላቅነትን ከተቀዳጁት ከታላላቁቹ ሰወች ከነ አጼ ቴድሮስና ከነ ቀዳማዊ ናፖሊዮን ትልቅ ትምህርት መቅሰም ይችል ነበር፡፡ 

ለምሳሌ ያህል አጼ ቴድሮስ የተነሱት ያጎቴ የራስ ኃይሉ ግዛት (ቋራ) ይገባኛል ብለው እንጅ ጦቢያን አንድ ለማድረግ አስበው አይመስለኝም፡፡  የእቴጌ ምንትዋብን የጦር መሪ የደጃች ወንድይራድን ሠራዊት ድል ሲመቱት ግን፣ የቋራ ብቻ ሳይሆን የድፍን ጦቢያ በር ወለል ብሎ ተከፈተላቸው፡፡  ያጼ ቴድሮስ ታላቅነት ደግሞ በሩ ወለል ብሎ መከፈቱን መገንዘባቸውና እድሉን በደንብ መጠቀማቸው ነው፡፡  ይህ ደግሞ የታላላቅ ሰወች ልዩ ተሰጥኦ ነው፡፡  አጼ ቴድሮስ ለትልቅ ሥራ የታጩ ታላቅ ሰው ባይሆኑ ኖሮ፣ ደጃች ወንድይራድን ድል ካደረጉ በኋላ በቋራ ዙርያ ያሉትን ሰፋፊ ግዛቶች ወደ ቋራ በማጠቃለል በቋረኞች እየተሞገሱና እየተወደሱ በመንደላቀቅ እድሜ ልካቸውን ይገዙ ነበር፡፡  እሳቸው ግን ለትልቅ ተልዕኮ የተመረጡ ትልቅ ሰው መሆናቸውን ስለሚያቁና በጽኑ ስለሚያምኑበት፣ በትንሿ ቋራ ተወሰነው ከሚንደላቀቁ በትልቋ ጦቢያ መማቀቅን መረጡ፡፡  ባጸደ ሥጋ ተጎሳቁለው፣ ባጸደ ነፍስ ተቀማጠሉ፡፡  

ናፖሊዮን ቦናፓርት ደግሞ ግብጽ ላይ በፈጸመው ወታደራዊ ጀብዱ በመላ ፈረንሳውያን የሚወደስ ጀግና ቢሆንም፣ ፓለቲከኛነቱን የጀመረው ግን የኮርሲካን ደሴት ከፈረንሳይ ለመገንጠል የተነሳ ኮርሲካዊ ጎጠኛ  (Corsican separatist) በመሆን ነበር፡፡  የፈረንሳይ አብዮት ያስከተለው ትርምስ ግን የኮርሲካን ብቻ ሳይሆን የመላዋን የፈረንሳይን ዕጣ የሚወስንበትን እድል ሰጠው፡፡  ታላቁ ናፖሊዮንም እድሉን በመጠቀም ጎጠኛነቱን እርግፍ አድርጎ ትቶ ፈረንሳይን ትልቅ በማድረግ ኮርሲካንም ትልቅ ለማድረግ ተነሳሳ፡፡  የኮርሲካ ብቻ ሳይሆን የመላ ፈረንሳይ ብሎም የዓለማችን ድንቅ ሰው ሆነ፡፡

አብይ አህመድ ግን ለትልቅ ሥራ የተፈጠረ ትልቅ ሰው ስላልሆነ፣ ጎጠኝነቱን ሙጥኝ ብሎ ኦሮሙማ ላይ ሲርመጠመጥ አጋጣሚው አመለጠው፡፡  አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንም አታለይነቱን ነቁበትና መቸም ላይመልሱ ፊታቸውን አዞሩበት፡፡  ኢትዮጵያውያንን በሙሉ ከፍ ማድረግ ሲችል፣ አልሮሞወችን (non-oromos) ጥየ ኦሮሞወችን ብቻ ከፍ አደርጋለሁ በማለት ዜሮ ድምር ጨዋታ (zero sum game) ለመጫወት ሲፈልግ የጨዋታ ሜዳው ተቆፋፈረበት፡፡  አልኦሮሞወችን ብቻ ሳይሆን የኦሮሞወችንም ይዞ የሚሞት ይዞ ሟች ሆነ፡፡ 

 

Email: መስፍን አረጋ

mesfin.arega@gmail.com

Filed in: Amharic