>
5:26 pm - Tuesday September 17, 4543

“ጌታዋን የተማመነች በግ ....!!!” (እውነቱ በለጠ)

ጌታዋን የተማመነች በግ ….!!!”

እውነቱ በለጠ

አሸባሪው የትህነግ ቡድን በሥልጣን ላይ በቆየባቸው እነዛ 27 የግፍና የሰቆቃ ዓመታት የኢትዮጵያዊነትን መሰረት ለመናድ ሲሰራ ኖሯል፡፡ለዚህ አንዱ ማሳያ ደግሞ የኢትዮጵያዊነት መሰረት በሆኑት ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች መካከል ልዩነቶችን በመፍጠርና በመከፋፈል አንደኛው በሌላኛው ላይ እንዲነሳና ግጭት እንዲፈጠር በማድረግ ወንድማማችነት ትርጉም እንዲያጣ አድርጎ ኖሯል፡፡
ስልጣኔን ይቀናቀነኛል ብሎ በሚያስበው ብሔር ላይ አላስፈላጊ ስም በመስጠት እርስ በእርስ መተማመን እንዳይኖር ፣በቀላሉ መፈታት የሚችሉ ልዩነቶችን በማወሳሰብ ለግጭት መንስኤ እንዲሆኑ በማድረግ በሌላ በኩል ለተፈጠሩ ግጭቶች የመፍትሔው አካል ስልጣን ላይ ያለው ህወኃት ብቻ እንደሆነ አድርጎ ማሳየትና ልክ አይደለም የሚል ዜጋ ካለ የጥፋት ሰይፉን በንጹሃን ላይ በማንሳት የስልጣን ዘመኑ ዕድሜ እንዲኖረው ያደረገ የሽብር ቡድን ነው፡፡
ኢትዮጵያን ሊያፈርሷትና በነበር  ሊያስቀሯት ቆርጠው የተነሱትን ባንዳዎች በሙሉ በማፈራረስ ኢትዮጵያዊያን ከጫፍ እስከ ጫፍ በወንድማማችነትና በሰላም የሚኖሩባት፣ አንድነቷ በጽኑ መሰረት ላይ የተገነባች ኢትዮጵያን ፈጥሮ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ዛሬ ላይ ለህይወታችን ሳንሰስት ከጠላት ጋር ፊት ለፊት በመግጠም ላይ እንገኛለን፡፡ አገርን ከጠላት ለመጠበቅ ሁሌም ዝግጁ ነን፡፡
ከጫካ ምስረታው ጀምሮ የተንኮል ሴራውን እየጋተ ለሽብር ቡድንነት የበቃው የትህነግ ቡድን የኢትዮጵያዊያንን አልገዛም ባይነትና ልማት ፈላጊነት ከሚያሳስባቸው የውጭ ኃይሎች ጋር በመጣመር ኢትዮጵያን ለማፍረስና ህዝቦቿን ለመበታተን ሌት ተቀን እንቅልፍ አጠው እየሰሩ ቢሆንም ዕቅዳቸው ግን ሊሳካ የማይችል የሞኝ ህልም ሆኖ ይቀራል፡፡
ስመ ጥሩና ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን እንዲሁም ምንጊዜም ከጎኑ የማይለየው ደጀን የሆነው ህዝባችን እስካለ ድረስ ጠላቶቿ ይፈርሳሉ እንጂ ኢትዮጵያ ማፍረስም ሆነ የእጅ አዙር ቀኝ ግዛት ዕቅዳቸው መቼም ሊሳካላቸው አይችልም፡፡
የምዕራባዊያን የጥቅም ተጋሪ የሆነው አገር ሻጩ  ህወኃት ከኢትዮጵያዊነት እሳቤ ውጭ በሆነ ምልኩ ንጹሃንን በግፍ መጨፍጨፉ ሳያንሰው፣የሰማንያ እና ዘጠና ዓመት የሆናቸውን መነኮሳትንና አቅመ ደካማ አረጋዊያንን በቡድን መድፈሩ እንደ በቀል ቢቆጥረው፣በአምልኮ ስፍራዎች ላይ አጸያፊ ድርጊቶችን መፈጸሙ ሳያሸማቅቀው፣ግዙፍ ማሽኖችን ፈተው መውሰዳቸው ሳያንስ፣ዓለም ላይ አሉ የተባሉ የሽብር ቡድኖች እንኳ ያልፈጸሙትን ግፍ የፈጸመው አሸባሪ የህወኃት ቡድን ይሄ ሁሉ አልበቃ ብሎት ዛሬም የግፍ ስራውን ቀጥሎበታል፡፡
“ጌታዋን የተማመነች በግ ላቷን ውጭ ታሳድራለች” እንዲሉ አሸባሪው የህወኃት ቡድን በገንዝብ አቅማቸው የተማመኑ፣በዘመናዊ መሳሪያቸው ሁሉን ማድረግ የሚችሉ የሚመስላቸው፣በሚዲያ ዲፕሎማሲያቸው ጫና ማሳደር እንችላለን ብለው የሚያስቡትን ምዕራባዊያን በመተማመን ዛሬም ድረስ ዕቅዱን ለማሳካት ይታትራል፡፡
የኢትዮጵያን የጀግንነትና የአልደፈርም ባይነት ታሪክ ዓለም ያውቀዋል፤ኢትዮጵያዊያን አገር በጠላት በተደፈረች ጊዜ ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን በመተው ቅድሚያ ለአገር በሚል ለነጻነት መታገላቸውና የህይወት መስዋዕትነት መክፈላቸው ሁሌም የሚዘከር አኩሪ መለያችን ነው፡፡የሕዝቡን አንድነት መበታተን አይደለም፤ያሰበን ጠላት እንኳ እንዴት መመለስ እንደምንችል አሳምረን እናውቀዋለን፡፡
የምዕራብ አገራት ተላላኪ የሆነው አሸባሪው የሕወኃት ቡድን ዕቅድ በማክሸፍ ብሔራዊ ክብሯና ሉዓላዊነቷ የተረጋገጠ፣ለማንም የማታጎበድድ ነጻ አገር እንዳለችን በውድ ልጆቿ መስዋዕትነት እናሳያለን፤ምክንያቱም አገር የሁሉም ነገር መሰረት ናትና፡፡
አሸባሪው የህወኃት ቡድን ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ እንድትፈርስ ከሚሹ ምዕራባዊያን ጋር አብሮ መስራቱ ለጊዜው ፋታ እንዲያገኝ ያስችለው ይሆናል እንጂ የማታ ማታ ዳግም በማይመለስበት ሁኔታ እስከወዲያኛው መሸኘቱ አይቀሬ ነው፡፡ያኔ ጠላት ያፍራል፤ አንገቱን ይደፋል፣ኢትዮጵያዊያን በጋራ ክንዳቸው ጠላትን መደምሰስ እንደሚችሉ ዓለም ይማርበታል፣ያኔ ብሔራዊ ክብሯና ሉዓላዊነቷ የተጠበቀች አገርን ዳግም ለዓለም ህዝብ እናሳያለን፡፡
ስግብግቡና አሸባሪው የህወኃት ቡድን የዜጎች ንብረቶችን ከማውደም ጀምሮ በአማራ በአፋር ክልሎች ላይ ያደረሰውን ገደብ የለሽ ውድመት በባንዳነቱ ትውልዱ የሚኮራበትን ሳይሆን አፍሮ አንገቱን የሚደፋበት ታሪኩን እያሰፈረ ነው። ባንዳ መጨረሻው ውርደትና ሞት ነው፡፡
Filed in: Amharic