>
5:33 pm - Thursday December 6, 0677

መንግስት  ጋዜጠኞቹ  የሚገኙበትን ቦታ “በአስቸኳይ ለቤተሰቦቻቸው እና ለሕግ አማካሪያቸው ያሳውቅ” (ኢሰመኮ) 

መንግስት  ጋዜጠኞቹ  የሚገኙበትን ቦታ “በአስቸኳይ ለቤተሰቦቻቸው እና ለሕግ አማካሪያቸው ያሳውቅ”
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)  መግለጫ፤ 

የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋዜጠኛ ክብሮም ወርቁ እና ታምራት ነገራ  የሚገኙበትን ቦታ “በአስቸኳይ ለቤተሰቦቻቸው እና ለሕግ አማካሪያቸው እንዲያሳውቁ” በጥብቅ አሳሰቧል። በእስር ላይ የሚገኙት ሁለቱ ጋዜጠኞች በቤተሰቦቻቸው የመጎብኘት መብታቸውን እንዲያረጋግጡም ጠይቋል።
የአሐዱ ሬድዮ አርታኢ የሆነው ጋዜጠኛ ክብሮም በፍርድ ቤት የዋስትና መብት ከተፈቀደለት ከህዳር 9 ጀምሮ፤ ኮሚሽኑ መገለጫውን እስካወጣበት እስከ ትላንትናው ዕለት ድረስ የተያዙበት ቦታ ለቤተሰቦቻቸው አለመነገሩን ጠቅሷል። ባለፈው ሳምንት አርብ ታህሳስ 1 በፖሊስ ቁጥጥር የዋለው የ“ተራራ ኔትወርክ” የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን መስራች እና ዋና አዘጋጅ ታምራት ነገራም በተመሳሳይ ሁኔታ ያሉበት ቦታም አለመታወቁን ኮሚሽኑ አመልክቷል።
ኢሰመኮ የሁለቱም ጋዜጠኞች “የቤተሰብ ጥየቃ መብታቸው ያልተከበረላቸው ከመሆኑም በላይ ያሉበት ሁኔታ አለመታወቁ ኮሚሽኑን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያሳስበው ነው” ብሏል። “በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታም ውስጥ ቢሆን ታሳሪዎች ያሉበት ሁኔታ ሊታወቅና በቤተሰብ እና በሕግ አማካሪ የመጎብኘት መብቶች ሊጣሱ አይገባም” ሲልም አክሏል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋሙ በትላንትና መግለጫው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አተገባበር በተመለከተ ባለፈው ህዳር ወር ያስተላለፈውን ጥሪ በድጋሚ አስታውሷል። ኮሚሽኑ በወቅቱ ባወጣው መገለጫ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሰብአዊ መብቶችን መርሆች ባከበረ መልኩ መተግበሩን የሚመለከታቸው አካላት በቅርብ ሊከታተሉ እና ሊያረጋግጡ እንደሚገባ አሳስቦ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
Filed in: Amharic