>

CPJ  ጋዜጠኞች እንዲፈቱ  ጠየቀ...!!! (DW)

CPJ  ጋዜጠኞች እንዲፈቱ  ጠየቀ…!!!

DW

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት ያሰሯቸዉን ጋዜጠኞች በሙሉ ባስቸኳይ እንዲፈቱ ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ጠየቀ።በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ CPJ ተብሎ የሚጠራዉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ኮሚቴ እንደሚለዉ የኢትዮጵያ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከደነገገ ካለፈዉ ጥቅምት ማብቂያ ወዲሕ ኢትዮጵያ ዉስጥ 14 ጋዜጠኞች ታስረዋል።ከታሰሩት መካከል ሁለቱ የኢትዮጵያ መንግስት በሚቆጣጠረዉ የኢትዮጵያ ማሰራጪያ ጣቢያ (EBC) የራዲዮ ትግሪኛ ቋንቋ አዘጋጆች የነበሩ ናቸዉ።ሌሌቹ ኡቡንቱ ቲቪ የተባለዉ የዩቱዩብ ጣቢያ ዋና አዘጋጅ፣የተራራ ኔትወርክ ዋና አዘጋጅ፣የሮሐ ቲቪ ተባባሪ መሥራች፣ለአሶስየትድ ፕረስ የሚሰራ ቪዲዮ አንሺ፣ አንድ ፎት ግራፍ አንሺ፣ ለመንግስት የሚወግነዉ የፋና ብሮድ ካስቲግ ኮርፖሬሽን ሪፐርተር ይገኙበታል።ዛሬ የተሰራጨዉ የCPJ መግለጫ እንደሚለዉ ሌሎች 6 ጋዜጠኞቹ መታሰራቸዉን ከዚሕ ቀደም መዘገቡን ጠቅሷል።
ኮሚቴዉ የጋዜጠኞቹን ስም፣የስራ ልምድ፣ የታሰሩበትን ሁኔታ፣ ጊዜ፣ከቤተሰቦቻቸዉና ወዳጆቻቸዉ የቀረበለትን አቤቱታ፣ ፍርድ ቤት መቅረብ አለመቅረባቸዉን ባካተተዉ ዝርዝር መግለጫ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ያላቸዉን የተለያዩ የመንግስት ባለስልጣናን ማነጋገሩን ና ለማነጋገር መጣሩን አስታዉቋል።በከሰሐራ በረሐ በታች በሚገኙ ሐገራት የCPJ ተጠሪ ሙቶኪ ሙሞ እንደሚሉት የኢትዮጵያ መንግስት ባለፈዉ ጥቅምት ያወጀዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ ፀጥታ አስከባሪዎች ሰዎችን እንደፈለጉ እንዲያስሩና የሕግ ሒደትን እንዲጥሱ ሰፊ ስልጣን ይሰጣል፤ ተቺ ጋዜጠኞችነን ሙሉ በሙሉ ያግዳልም።
«የኢትዮጵያ መንግስት በሥራቸዉ ምክንያት የታሰሩ ጋዜጠኞችን በሙሉ እንዲፈታና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የመናገር ነፃነትን ለመደፍለቅ መጠቀሙን ማቆም አለበት» ይላሉ ሙሞ።እዚያዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚገኙ የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪዎችና ማሕበራት እንዳሉት የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ካሰሯቸዉ ጋዜጠኞች አንዳዶቹ እስከ ትናንት ድረስ ያሉበት አልታወቀም።ሌሎቹ ፍርድ ቤት አልቀረቡም።ፍርድ ቤት ቀርበዉ እንዲለቀቁ ከተወሰነላቸዉ በኋላ ተመልሰዉ የታሰሩም አሉ።
የኢትዮጵያ መንግስት የሚቆጣጠረዉ የሐገሪቱ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)ከታሰሩት ጋዜጠኞች መካከል የክብሮም ወርቁ፣ የታምራት ነገራ፣ የመዓዛ መሃመድ እና  የእያስጴድ ተስፋዬን  ጉዳይ ለማጣራት የሚመለከታቸዉ ካላቸዉ ባለስልጣናት ጋር እየተነጋገረ መሆኑን አስታዉቋል፡፡በተለይም ታምራት ነገራ በፖሊስ ከተያዘበት ካለፈዉ ሳምንት  አርብ ጀምሮ እና ከጥቅምት 16 ጀምሮ የታሰረዉ ባለፈዉ ኅዳር 9 ቀን በፍርድ ቤት የዋስትና መብት ከተፈቀደላቸው ጊዜ ጀምሮ የተያዙበት ቦታ ለቤተሰቦቻቸው አለመነገሩን አስታዉቆ ኮሚሽኑ «አሳሳቢ» ብሎታል።
CPJ ባለፈዉ ሳምንት ባወጣዉ መግለጫ ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በማሰር ከሰሐራ በረሐ በስተደቡብ ከሚገኙ ሐገራት ሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ አስታዉቆ ነበር።ያለፈዉ መግለጫው በወጣበት ወቅት ኢትዮጵያ ዉስጥ የታሰሩት ጋዜጠኞች ቁጥር 9 ነበር።
Filed in: Amharic