>

"ተመድ በትግራዩ ግጭት የተፈጸሙ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚያጣራ ገለልተኛ መርማሪ ኮሚሽን ለማቋቋም ወሰነ...!!!" (ዋዜማ ራዲዮ)

“ተመድ በትግራዩ ግጭት የተፈጸሙ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚያጣራ ገለልተኛ መርማሪ ኮሚሽን ለማቋቋም ወሰነ…!!!”
ዋዜማ ራዲዮ

– የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ካውንስል ዛሬ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ባደረገው ልዩ ስብሰባ በትግራዩ ግጭት የተፈጸሙ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚያጣራ ገለልተኛ መርማሪ ኮሚሽን ለማቋቋም የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ በድምጽ ብልጫ ማጽደቁን አስታውቋል። ካውንስሉ ዓለማቀፍ መርማሪ ኮሚሽን ለማቋቋም የወሰነው በ21 ድጋፍ፣ በ15 ተቃውሞ እና በ11 ድምጸ ተዓቅቦ ነው።
የካውንስሉ አባል የሆኑ የአፍሪካ ሀገራት ግን ካውንስሉ ልዩ ስብሰባ መጥራቱን እንደሚቃወሙት በጋራ አስታውቀው ነበር። የአፍሪካዊያኑ ቡድን በስብሰባው ላይ በገለጸው የጋራ አቋም፣ ኢትዮጵያን አስመልክተው ለካውንስሉ አዲስ የውሳኔ ሃሳብ ያቀረቡ አካላት የውሳኔ ሃሳባቸውን እንደገና እንዲያጤኑት ጠይቋል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከተመድ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ጋር በጋራ በጦርነቱ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን እንደመረመሩ እና የኢትዮጵያ መንግሥትም ዝርዝር እውነታውን እየደረሰበት እንደሆነ የጠቀሰው የአፍሪካዊያኑ ቡድን የካውንስሉን ልዩ ስብሰባ መጥራት ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እየተደረገ ባለው አሕጉራዊ የሽምግልና ጥረት ውስጥ ጣልቃ መግባት ነው በማለት ወቅሷል።
የአፍሪካዊያኑ ቡድን አክሎም፣ የካውንስሉን ስብሰባ እና ግጭቱን ፓለቲካዊ ማድረግ መቆም እንዳለበት፣ ግጭቱ በኢትዮጵያ ሉዕዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት እና ዲሞክራሲ ላይ አደጋ የጋረጠ እንደሆነ እና ቡድኑ የአፍሪካ ሀገራትን መበታተን በጽኑ እንደሚቃወም ገልጧል። የካውንስሉ አባል ከሆኑት 13 የአፍሪካ ሀገራት መካከል፣ ኤርትራ፣ ሱማሊያ፣ ሱዳን፣ ሊቢያ፣ ሴኔጋል እና ናሚቢያ ይገኙበታል። [ዋዜማ  ራዲዮ]
Filed in: Amharic