>

"ተመድ በኢትዮጵያ ላይ የጠራው ስብሰባ አግባብነት የለውም....!!!" (የእስራኤል አምባሳደርና አንጋፋው ዲፕሎማት ኤቪ ግራኖት) 

“ተመድ በኢትዮጵያ ላይ የጠራው ስብሰባ አግባብነት የለውም….!!!”
የእስራኤል አምባሳደርና አንጋፋው ዲፕሎማት ኤቪ ግራኖት 

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) በኢትዮጵያ ላይ የጠራው ስብሰባ አግባብነትና ተቀባይነት የሌለው ድርጊት መሆኑን በኢትዮጵያ የቀድሞው የእስራኤል አምባሳደርና አንጋፋው ዲፕሎማት ኤቪ ግራኖት ተናገሩ።
የአውሮፓ ኅብረት ለመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ላይ እንዲወያይ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት በነገው ዕለት ውይይት ያደርጋል።
የተጠራው ስብሰባ ከዚህ ቀደም ምክር ቤቱ ከኢትዮጵያ አቻ ተቋሙ ጋር በጋራ ያጠኑትን ጥናትና ጥናቱንም ተከትሎ ያቀረቡትን ምክረ ሃሳብ የሚዘነጋ መሆኑን መንግሥት ገልጸዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግሥት በምክር ቤቱ ገለልተኛነት ላይ ጥያቄ በማንሳት ከመርህ ውጪ የፖለቲካ ማስፈጸሚያ እየሆነ መምጣቱን ጠቁሟል።
በኢትዮጵያ የቀድሞ የእስራኤል አምባሳደርና አንጋፋው ዲፕሎማት ኤቪ ግራኖትም የተጠራው ስብሰባ የኢትዮጵያን ሁኔታ ያላገናዘበና አግባብነት የሌለው መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን መንግሥት ባህሪና በአንጻሩ ደግሞ አሸባሪው የሕወሓት ቡድን የሚፈጽመውን ግፍ በቅጡ ካለመገንዘብ የተጠራ ስብሰባ መሆኑንም አስረድተዋል።
በተጓዳኝም ምዕራባውያኑ “የእነሱ አካሄድ ብቻ ትክክል” እንደሆነ በማስመሰል በሚያራምዱት የተሳሳተ አቅጣጫ የሚያካሂዱት ስብሰባ መሆኑንም ነው ያነሱት።
ምዕራባውያኑ በአፍሪካ አንዳንዴም በመካከለኛው ምስራቅም ጭምር የራሳቸውን አመለካከት ለመጫን የሚሞክሩት አካሄድ በኢትዮጵያም ላይ ዳፋው ደርሷል ብለዋል።
የአገራትን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ካለማወቅ የመነጨ መሆኑን ጠቁመው ኢትዮጵያም እንዲህ ያለውን ጫና በአግባቡ እየመከተች መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያም ለእንዲህ ያሉ ጫናዎች አልበገር ባይነት በታሪክ የተመሰከረ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሚመራው መንግሥት የአገሪቱን ሉዓላዊነትና የሕዝቡን አንድነት ለማስጠበቅ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል።
በመሆኑም ከአሜሪካ መንግስትና አንዳንድ የምዕራብ አገራት የሚታየው ጣልቃ ገብነትና ጫና የኢትዮጵያን መንግሥት ትክክለኛ አካሄድ ማደናቀፍ እንደማይችሉ ገልጸዋል።
ምዕራባውያኑም አካሄዳቸውን በመቀየር በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ወደ ሥልጣን ለመጣው መንግሥት ተገቢውን እውቅና ሊሰጡ ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለዓለም ሰላምና ደኅንነት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረከተች አገር መሆኗን ጠቁመው የጠቅላይ ሚኒስትሩም የኖቤል ሽልማት ይህንን አማላካች ነው ብለዋል።
ያም ሆኖ ከዚሀ በተቃራኒ የቆመው የሕወሓት አሸባሪ ቡድን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት በሚጻረር መልኩ መንቀሳቀሱ እንዳስገረማቸው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ከምዕራባውያኑ ዓለም ለሚሰራጨው ፕሮፓጋንዳ የኢትዮጵያ መንግሥት ጆሮ መሥጠት እንደሌለበት ገልጸዋል።
ለፕሮፓጋንዳ ይሄ ነው የሚባል መልስ የለም ያሉት አምባሳደር ኤቪ ግራኖት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሕዝቡ ይበጃል የሚለው ሥራ ላይ  ትኩረት በማድረግ  የውጭ ጣልቃገብነትና ጫናውን ከመቋቋም ባለፈ የውስጥ ኢኮኖሚ አቅም እንዲጎለብት ትኩረት አድርጎ መሥራት አለበት ብለዋል።
(ኢ ፕ ድ)
Filed in: Amharic