መንግሥት መገንጠልን ጨምሮ የትኛውንም አጀንዳ ያማከለ ብሔራዊ ውይይት ለማድረግ ዝግጁ ነው….!!!
አቶ ሬድዋን ሑሴን
የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ የሆኑት አቶ ሬድዋን ሑሴን ናቸው። አቶ ሬድዋን ከቱርኩ አናዶሉ ኤጀንሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ መንግስት ይህን የሚያደርገው ውስጣዊ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መሆኑን ጠቅሰዋል። ሁሉንም አጀንዳዎች ወደ ጠረጴዛ ያመጣል በተባለው ብሔራዊ ውይይት ላይ ከመንግስት ጋር ውጊያ ውስጥ የሚገኘው የሕወሓትን ተሳትፎ በተመለከተ የተጠየቁት አቶ ሬድዋን፣ ለመናገር እንደሚቸግር ጠቁመው ቡድኑ የትግራይ ሕዝብ ብቸኛው ወኪል እንዳልሆነም አስታውሰዋል።
ሚኒስትር ዲኤታው መንግስት ከዚህ ቀደም ከሕወሓት ጋር እርቅ ለማካሄድ ጥረቶችን ማድረጉን ያስታወሱ ሲሆን፣ ቡድኑ የሰላም አማራጮችን አስቸጋሪ ማድረጉንም አመልክተዋል። በሌላ በኩል አቶ ሬድዋን በዚሁ ቆይታቸው፣ በኢትዮጵያ ባለው ግጭት የተወሰኑ የምዕራብ አገራት ብዙኃን መገናኛ ብዙኃን ለሕወሓት ድጋፍ ማሳየታቸውን ገልፀዋል። የኢትዮጵያ እና ሱዳንን ወቅታዊ ጉዳይ ያነሱት አቶ ሬድዋን ሑሴን፣ ሁለቱ አገራት በአሁኑ ጊዜ የየራሳቸው ፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ እንደሚገኙ በማስታወስ፣ ትንሽ ያሉትን ይህን የድንበር ጉዳይ ከጀርባ ሆኖ ማን ሆኖ እንደሚያባብሰው እናውቃለን ሲሉ ተናግረዋል።