>

“በለቅሶ የሚዘሩ በደስታ ይለቅማሉ....!!!”  መዝሙረ ዳዊት 125(125)፡5 ((ቀለብ ስዩም (የህሊና እስረኛ)፣ ቃሊቲ፣ ))

በለቅሶ የሚዘሩ በደስታ ይለቅማሉ….!!!
 መዝሙረ ዳዊት 125(125)፡5
ቀለብ ስዩም (የህሊና እስረኛ)፣ ቃሊቲ፣ አዲስ አበባ 

*….. በኢትዮጵያ ሠላም የሚሰፍነው መቼ ይሆን! ተስፋችን እስከምን ድረስ ነው? ብለን እንጠይቅ፤ ምላሹን በትክክል መወሰንና ማስቀመጥ ቢያስቸግርም መፃኢውን ለመገመት የመጣንበትን መንገድ በማስተዋል መመልከት ይገባል፡፡
 ሁሉም ሰው ሊገነዘበው እንደሚችለው ከዘመኑ መሳፍንት አንስቶ እስካሁን ድረስ የኢትዮጵያ ህልውና በመኖርና ባለመኖር አጣብቂኝ ገብቶ በየዘመኑ መናጥ ሆኖአል፡፡ በመናጥ ውስጥ ደግሞ መናጋት መውደቅና መነሳት ይኖራል፡፡ በሌላ አነጋገር እየተናጥን፣ እየወደቅንና እየተነሳን ቀጥለናል ማለት ነው፡፡ ከትናንት  እስከ ዛሬ ከራስ  ሚካኤል ስሁል እስከ ዘመነ ደብረጽዮን ባለው ጊዜ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን የውስጥ ቀጥተኛ ጠላቶች የትግራይ ተወላጆች ናቸው፡፡ እነዚህ ህዝቦች በአብዛኛው የአካባቢያቸውን የተፈጥሮ ሀብት ሙጥጥ አድርገው ግጠው በመጨረሻው ምክንያት ሁሌም የሌላውን ክልል የተፈጥሮ ሀብት መመኘትና ነጥቆም ለመውሰድ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አይበገሬዎቹ ኢትዮጵያውያን በባህሪያቸው የደረሰባቸውን ሁሉ ድባቅ በመምታት ተለይተው የሚታወቁ ህዝቦች ናቸው፡፡
 አንዳንድ ቅን አመለካከት ያላቸው ወገኖች ኢትየጵያዊነት በራሱ ፍትሀዊነት፣ ነፃነት፣ አሸናፊነት፣ ታሪካዊነት፣ ጥንታዊነት ከመሆኑም ባለፈ ለኢትዮጵያዊያን የቃል ኪዳን እምነታቸው ነው ሲሉ ይደመድማሉ፡፡ በእርግጥም ትክክል ናቸው፤ ማንም ተሳስታችኋል የሚላቸው የለም፡፡ ኢትዮጵያውያ የተቀደሱ፣ ፈጣሪ አምላካቸውን በፍቅር የሚያከብሩና የሚፈሩ፣ ኩሩና አይነኬ አርበኞች ናቸው፡፡ ከያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ደም ውስጥ አርበኝነት ይገኛል፡፡ በተለይም ኢትዮጵያ በአደጋ ውስጥ በምትሆንበት ወቅት ከያንዳንዱ ደም ውስጥ የሚገኘው የአርበኝነት ስሜት እንደ ቀትር ጸሐይ ይንተገተጋል፣ ይንተከተካል፡፡ የኢትዮጵያውያን አይሸነፌነት ምስጥርም መነሻው ይኸው ነው፡፡ በአጠቃላይም ይህችን ውድና ብርቅዬ ሀገር በየዘመናቱ ከተከሰቱ አደጋዎችና ከጠላቶችዋም ሴራ ሲታደጋት የኖረው የጎሣ ብሔርተኝነት ሳይሆን ኢትዮጵያዊ አንድነት ብቻ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ይህ የአንድነት መንፈስ አንደኛው የኢትዮጵያዊነት እሴት እንደሆነም ይታሰባል፡፡
 
1.  ኢትዮጵያዊነትን እንዴት እናስቀጥል!?
 የኢትዮጵያዊነት የአንድነት፣ የአሸናፊነትና የድል መንፈስ ከሠላሳ አመታት በላይ ከያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ ለማውጣት ሰፊ ዘመቻ ቢካሄድም ለካስሰ ተዳፍኖ ኖረ እንጂ እሳቱ ፈጸሞ አልጠፋም ነበር፡፡ ይህንን ደግሞ በአሁኑ ወቅት በሰሜኑ ሀገራች ክፍል ምእራባውያንና የትግራይ ባንዳዎች በከፈቱብን ጦርነት ውስጥ መመልከትና ማረጋገጥ ችለናል፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያዊነት በአባቶቻችንና በአያቶቻችን ዘመን በነበረበት ደረጃ ላይ ነው ለማለት አይችልም፡፡ በእኔም እምነትና አመለካከት ኢትዮጵያዊ ጠል ህዝብ አለ ለማት እቸገራለሁ፡፡ ኢትዮጵያዊ ጠልነት መነሻው ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ሲሆን ወደ ኢትዮጵውያን የሚዘመተው ደግሞ በልተው በማይጠግቡና ጠጥተው በማይረኩ ባንዳዎች አማካኝነት ይሆናል፡፡ እነዚህ ባንዳዎች የራሳቸውን የማይጠረቃ ሆድ ለመሙላት ሲሉ ለጠላት አድረው የገዛ ወገናቸውን መልሰው ይወጋሉ፡፡ የትናንሽ ጎጥ ተወካይና ጥቅም አስጠባቂ ነን በሚል የፖለቲካ ፓርቲ፣ አማፂ፣ ንቅናቄ፣ ግንባርና…. የመሳሰሉ የይስሙላህ ድርጅቶችን ያቋቁማሉ፡፡ በነፃነት ስም ባርነትን፣ በመብት ስም ከፋፋይነትንና ጠላትነትን ይሰብካሉ፡፡ እናም የኢትዮጵያዊነት ተግዳሮቾች ሁሌም የሚፀነሱትም ሆነ የሚወለዱት “መሪ” ነን በሚሉ ወገኖች ይሆናል፡፡
 እውነተኛ የሕዝብ መሪ እንደ ቴዎድሮስ ነፍሱን ለኢትዮጵያዊ አንድነት አሳልፎ ይሰጣል፡፡ እውነተኛ የህዝብ መሪ እንደ እምዬ ምኒልክ በጦርነትና በፍልሚያ ውስጥም ሆኖ ሳለ ቀጣዩ ትውልድ የተሻለ ሕይወት፣ የሐገር ፍቅር ስሜት፣ ልማትና እድገት ተጨንቆ ያስባል፤ ለቀጣይነቱም ሳያሰልስ ይሰራል፡፡
 አሁን ያለው ሁኔታ ግን ፈፅሞ ከእዚህ የተለየ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ምንም እንኳ ህወሓት በኢትዮጵያ ላይ የከፈተው የግፍና የእብሪት ጦርነት ለ27 አመታት በጎሣና በቋንቋ ተከፋፍሎ የነበረውን ህዝብ አንድ አድርጎታል፡፡ የጥቃት ጦርነት ኢትዮጵውያንን ወደ አንድነት ቢያመጣም ህወሓት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የሰራው የፖለቲካ ሴራ እጅግ ውስብስብና መጠነ—ሰፊ በመሆኑ ችግራችን ተቀርፎአል ለማለት አይቻልም፡፡
 እንደሚታወቀው በዘመነ ህወሓት ኢህአዴግ ወደ መንግሥታዊ ሥልጣኑ ሲመጣ የተወለደ አንድ ልጅ ዛሬ ላይ የ30 አመት እድሜ ይኖረዋል፡፡ ይህ የወጣትነቱን እድሜ አጠናቆ ወደ ጎልማሳነት በመሸጋር ላይ ያለ ትውልድ የኢትዮጵያን ትክክለኛ ታሪክ የማወቅ ውስንነት ቢኖርባቸውም፣ በተጨማሪም በትምህርት ስርአቱ ላይ በተፈጸመውም ደባ በትምህርትና እውቀት የጎለበተ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡  በእዚህም ምክንያት የሕወሓትን ሀሰተኛ የፈጠራ ትርክትና የተፈጠረውንም ሴራ በራሳቸው አእምሮ መርምረው መረዳት የሚችሉበት ሁኔታ በቂ ደረጃ ላይ አለመሆኑን እረዳለሁ፡፡
 ህወሓት ተደምስሶ በሀገሪቱም ሠላም ከሰፈነ አሁን ያለውም ሆነ ወደፊት የሚመጣው ትውልድ ጠያቂና አገናዛቢ እንዲሆን ከወዲሁ እየተሰራ ያለ ስራ የለምና መጪውን ተስፋ መገመት ያስቸግራል፡፡ እንዲያውም መጪውን ትውልድ በኢትዮጵያዊነት እሴቶች መቅረፅ ያለበት በሥልጣን ላይ ያለው ገዢ የፖለቲካ  ፓርቲ ከፍተኛውን ድርሻ መውሰድ ሲገባው ብልፅግና ግን አጋጣሚውን ተጠቅሞ እርሱም ህወሓት በሄደበት መንገድ ለመጉዋዝ የፈለገ ነው የሚመስለው፡፡ ይህንን የምለው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡
 በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ወደሚገኙ የተለያዩ ተቋማት ብናመራ የህወሓት ሰዎች የነበሩበት መቀመጫ በአጠቃላይ አሊያም በአብዛኛው በኦሮምኛ ተናጋሪዎች ተይዘው እናገኛቸዋለን፡፡ በመገናኛ ብዙሃን በኩል የምንሰማቸው የባለሥልጣናት ስሞች (በተለይም በመከላከያ ሰራዊቱ) የኦሮሞ ተወላጆች በመሆናቸውና ብዙ አሁናዊ ጉዳዮችን መንግሥት ህወሓት በሄደበት መንገድ እየተጉዋዘ ስለመሆኑ ጥርጣሬ ያሳድርብናል፡፡
 በእርግጥ በርካታዎች እንደሚሉት የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን የኢትዮጵያን እይታውን በተመለከተ እኔም ተግባሩን ሳይሆን በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ልጋራው እችላለሁ፡፡ ይሁን እንጂ የአማራ የፖለቲካ ሀይሎች ወደፊት ሌላ “ጁንታ” ይሆንብናል የሚል ሥጋት እንዳላቸው አንዳንድ አመላካች ነገሮች ይኖራሉ፡፡ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከአማራ የክልል አስተዳዳሪነታቸው ተነስተው ወደ ፌዴራል መንግስት የመጡበት ምክንያት፡- “ማንም እየተነሳ የጎበዝ አለቃ (ፋኖ) መሆን በሚፈልግበት ሁኔታ ውስጥ እኔ ለመስራት እቸገራለሁ፡፡” የሚል አይነት አቋም በመያዛቸው ስለመሆኑ ውስጥ አዋቂ ምንጮች ይናገራሉ፡፡ በተደጋጋሚ ቢለመኑ እንኳን እምቢ ማለታቸውም ይወሳል፡፡
 ይህንን አንድ በሉ እነ ጄነራል አሳምነው ፅጌ በተገደሉበት ሰሞን ጠቅላይ ምኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በገደምዳሜ ንግግራቸው አምባገኑን የሕወሓት አገዛዝ አስወግደን ሌላ አምባገነን እንዳይፈጠር መጠንቀቅ እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተው ሲተቹም አዳምጠናቸዋል፡፡ የአማራ ክልል መስተዳድርን ካነሳሁ ላይቀር የታዘብኩትን ላካፍላችሁ፣ በዶ/ር አብይ ዘመን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አንድም ጊዜ ሳይቀየር የአማራ ክልል ፕሬዚዳንቶች ግን ከ5 ሰዎች በላይ መቀያየራቸውን ስመለከትና አሁን ላይ እየተሰራ ያለውን ሁኔታ ስመለከት አግራሞትና ጥርጣሬ ጨምሮብኛል፡፡
 በመሰረቱ ጠቅላይ ምኒስትሩና ካቢኒያቸው የኢትዮጵያን አንድነት አጠናክሮ ለማስቀጠል እንዲቻል በየደረጃው በሚገኙ የሥልጣን እርከኖች ላይ የኦሮሞ ተወላጆችን በመመመደብ ነው ወይ!? በጭራሽ እንደዚያ ሊሆን አይችልም፡፡ የአዲስ አበባን ነዋሪዎች በውል ለይተው የማያውቁ ከ18ሺህ በላይ የኦሮሞ ተወላጆችን አምጥቶ በአዲስ አበባ መስተዳደር ውስጥ ማሰማራትስ በምን መልኩ ነው ፍትሃዊና ተገቢነት ያለው አሰራር የሚሆነው!? ይህ ብቻ አይደለም፤ በበርካታ ምክንያቶች ዛሬ ላይ ሆነን ሀገር አጣብቂኝ ውስጥ ሁና መተቸት የማንፈልጋቸው እጅግ በርካታ ችግሮችም አሉ፡፡ ለአገርና ለህዝብ ጥቅም ሲባል ለጊዜው ወደ አደባባይ ባናመጣቸው እመርጣለሁ፡፡ በጅምላ እይታዬ ግን አንደኛውን ወገን እንደ የብረት አሎሎ ሰባሪ ሌላውን ደግሞ እንደ ሸክላ ተሰባሪ አድርጎ መቁጠር ተገቢም አሥፈላጊም አይደለም፡፡ ቢያንሥ-ቢያንስ ከህወሓት የእብሪት ውድቀት መማር መቻል ይኖርብናል፡፡
2.  ከአደጋ ጊዜ የሚታደገንን “መርከብ” እንሥራ!
 ኖህ የእግዚአብሔርን ድምፅ መስማት የቻለ፣ የሰው ልጅንና የእንስሳቱን ዘር ማስቀጠል የቻለ የምድራችን ታላቅ መሪ ነበር፡፡ ኖህ አለምን ከጥፋት ውሀ ለመታደግ የሚያስችለውን መርከብ ለመሥራት 40 አመታት ፈጅቶበታል፡፡ በተጉዋዳኝም ለአርባ አመታት ሰዎች ከርኩሰታቸው እንዲፀዱና በጥፋታቸውም እንዲፀፀቱ፣ ንስሀ እንዲገቡና ከሚመጣውም የጥፋት ውሀ እልቂት እንዲድኑ መክሯል፡፡ ይሁን እንጂ የእዚያን ዘመን ሰዎች፡- ምንም አይነት ጥቁር ደመና በሰማዩ ላይ ሳይታይ አለም በጥፋት ውሀ ትጠፋለች!” የሚለውን ማስጠንቀቂያ የምዋርት አሊያም የእብደት ንግግር አድርገው በመቁጠር በኖህ ላይ አፊዘዋል፣ ተሳልቀውበታልም፡፡ በእዚህም ምክንያት የኖህ ስብከት ሰሚ ያጣ ሆነ፡፡ ይሁን እንጂ ኖህ የአምላክን የማስጠንቀቂያ ድምፅ በእምነት ተቀብሎ ታላቁን አዳኝ መርከብ በመሥራቱ ራሡንና ቤተሰቡን፣ እንደዚሁም ዛሬ በምድራችን ላይ የሚርመሰመሱትን የእንሠሣቱንና የአራዊቱን ዘር ማስቀጠል ችሏል፡፡ ዛሬም ኖህን መሠል መሪ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ያስፈልገናል፡፡
 ይህን ምሳሌ በሁለት መልኩ እንመልከተው፡፡ የመፅሀፍ ቅዱስ ሊህቃን የኖህን መርከብ በክርስቶስ እየሱስ ይመስሉታል፡፡ ከአለማችን የጥፋት ውሀ እልቂት የዳኑት በኖህ መርከብ ውስጥ የገቡት ብቻ ሲሆኑ ከሚመጣው የእግዚአብሔር የቁጣ ቀን እልቂት የሚድኑትም በእየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅነትና አዳኝነት ያመኑት ብቻ ይሆናሉ፡፡ ይህ መንፈሣዊ ትርጉም እንደተጠበቀ ሆኖ ወደ ፖለቲካዊ ትርጉሙ ስንገባ ደግሞ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን እንደ ኖህ መርከብ የምንመለከታት “ኢትዮጵያ” ናት፡፡ ምንም ይሁን ምንም እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር አምላክ የምትዘረጋ ኢትዮጵያ ህልውናዋ ተጠብቆ መጉዋዝ ይኖርባታል፡፡ ለእዚህ ደግሞ ፍፁም የህዝብ አገልጋይ፣ ቆራጥና ታማኝ መሪ ማግኘት የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ እናም ጠቅላይ ምኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም ሆኑ ካቢኒያቸው ከኦህዴድ ብልጽግና አመለካከት ያለፈ አስተሳሰብ ሊያዳብሩ ይገባል፡ ሚዛናዊና ፍትሀዊ የሆነ የኢትዮጵያን የአንድነት ህልውና የሚያስጠብቁ፣ ከወገንተኝነት የፀዳ አመራር ያስፈልጋል፡፡ በአጠቃላይም የኖህን መርከብ (ኢትዮጵያን) መሥራት የህዝብና የመንግስት የጋራ ድርሻ ይሆናል፡፡ የጋራ ሀገራችንን ህልውና የማስጠበቅ ሀላፊነት የሁላችንም እስከሆነ ድረስ በግሌ የተሰማኝን ቅሬታዎች በቅንነትና በግልጽነት ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡
3.  ህወሓት ሲዘርፍ ቃርሚያ እንኳን አያስቀርም 
ወይን ለቃሚ አዝመራ ሰብሳቢ ቢመጣ በማሳው ላይ ቃርሚያ ይተዋል፣ ሌባ በሌሊት ቢገባ የሚፈልገው ብቻ ነው ሰርቆ የሚሄደው፡፡ ወያኔ ግን በአማራ ህዝብ ላይ የፈጸመው በደል መስፈሪያም መጠንም የለውም፡፡ ሊጡን ወይም ቡሆውን ከየቦሀቃው እየቀዳ ጠጣ፣ ጥሬ ዘንጋዳ ጥሬ ድንች በላ፣ በርበሬና ሽሮ በሽርጡ እየቋጠረ ወሰደ፣ ህጻናት ሽማግሌ፣ሴት ወንድ ሳይመርጥ የሚችለውን ሁሉ ደፈረ፣ ገደለ፣ አሰቃየ፣ መስጊድ ቤተክርስቲያን አፈራረሰ፣ በአንዳንዶቹም ውስጥ ተጸዳዳ፣ ትምህርት ቤቶችንና ጤና ጣቢያዎችን አወደመ፣ የተማሪዎችን መቀመጫ ወንበር ሳይቀር እየነቃቀለ ወሰዳቸው፣ አነደዳቸው፣ በሬና ላሞችን በቁመናቸው እየቆራረጠ በላቸው፡፡ የግለሰቦችን የሸቀጣ ሸቀፅጥ ሱቆች፣ እህሉን፣ ቁሳቁሱን ባሰማራቸው ተሸከርካሪዎች እየጫነ ወሰደ፣ መውሰድ ያልቻላቸውንም እያቃጠለ አወደማቸው፡፡ አንዳች ቃርሚያ አላስቀረም፡፡ ህወሓት ለአማራ ህዝብ ያለውን ጥላቻና የጠላትነት ስሜት ሙሉ በሙሉ ተግብሮታል፡፡
 በአጠቃላይም በአማራ ክልል ህይወት እንዳይቀጥል ለማድረግ ነበር ጥረቱ፣ በእዚህ ሁሉ ቁጥር ስፍር የለሽ የትውልድ ጠባሳና ጥቃት የአማራ ህዝብ ቀላል የማይባል የኢኮኖሚ ድቀትና ማህበራዊ ቀውስ ተጠቅቷል፡፡ ምናልባትም በሰላሳና አርባ አመታት ውስጥ ማገገም ከማይቻልበት ሁኔታ ላይ ተደርሷል፡፡
4.  ጦርነቱ በአማራና በአፋር ክልል ውስጥ እንዳይሆን ማድረግ አይቻልም ነበር!?
አንድ ነገር አይካድም፣ ኤርትራ፣ የአማራና የአፋር ክልሎች የትግራይ አዋሳኝ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ስለዚህ በአንድም በሌላ መልኩ ትግራይ ላይ  ሲዘንብ በአከባቢው አዋሳኝ ክልሎች ሊያካፋ ይችላል፡ የሆነው ግን እንዲህ አይደለም፣ ህወሓት 30 ዓመታት መንግስታዊ ሥልጣኑ ሲያከማች የነበረውን የጦር መሳሪያ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ያሰለጠናቸው ልዩ ሀይልና ሚሊሺያ ጋር ተዋግቶ መላውን የትግራይ ክልል በ15 ቀናት ውስጥ የተቆጣጠረው የኢትዮጵያ መከላከያ ሀይል፣ የአማራ ክልል ልዩ ሀይል፣ ሚሊሻና ፋኖ እያለ በምን አይነት ወታደራዊ ስልትና መለኪያ ነው መላውን የወሎ ምድር ሊቆጣጠር የቻለው? ይህንን አሁናዊ አነጋጋሪ ጉዳይ በጥያቄነት እናቆየውና ወደ ሁለተኛው ዙር መልሶ የማጥቃት ዘመቻ ስንገባ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የወሎን ምድር ከወያኔ ጦር ነጻ ማውጣት ተችሏል፡፡ ስለዚህ የወያኔ ጦር ከኢትዮጵያ ጦር ጋር በምንም አይነት መለኪያ የሚነጻጸር አይደለም ማለት ነው፡፡
በእርግጥ ጀግናው የወሎ ህዝብ በተቀነባበረ ሰው ሰራሽ ሴራ በሚመስልና ማህበራዊ ህይወትን መሰረት አድርጎ ወሎን ለክፉ ለጥቃት እንዳጋለጠው ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ህወሓት በቃል አቀባዩ በጌታቸው ረዳ አማካኝነት “ጦርነቱን በአማራ ክልል ውስጥ እንዲካሄድ እናደርጋለን!” በማለት የዛተውን ዛቻ ተግባራዊ ሲያደርገው ወደሁዋላ እያፈገፈጉ ጠላትን ሙሉ በሙሉ ወደ አማራ ክልል እንዲገባ መፍቀድ ህሊና የሚቀበለው አሳማኝ ምክንያት የለም፡፡ ክንውኑ ጠቀሜታም ጉዳትም ነበረው የሚሉ የተለያዩ ወገኖች አሉ፡፡ አንዳንዶቹም ድብቅ “ፖለቲካዊ ሴራም” እንዳለው ይናገራሉ፡፡ ምንም እንኳን ዝርዝር ጉዳዮች ውስጥ ገብቼ የሚባለውን ሁሉ ለመፈተሽ የጊዜው ሁኔታ ባይፈቅድልኝም ወደፊት ግን በዝርዝር መፈተሻችን አይቀርም፡፡ እስከዚያው አንጀቴ በሀዘን ተቆራምዶ መንፈሴም ይረበሻል፣ የልቤ ሰላም ይታወካል፣ የተፈናቃይ ወገኖቼ ርሀብና እርዛት ውርደትና ሰቆቃ በታየኝ መጠን ነፍስያዬ ክፉኛ ትታመማለች፡፡ ትሰቃያለችም፡፡
ፁሁፌን ከማጠቃለሌ በፊት በጦርነቱ ዙሪያ ሳላነሳው ብቀር የሚቆጨኝን ጉዳይ ላካፍላችሁ፡፡ ይህም የእነ አርበኛ እሸቴ ሞገስ እና የልጁን የአርበኛ ይታገስ እሸቴ በወራሪው ላይ የሰሩትን ጀብድ ስመለከት በዘመኔ ለዚያውም በዚህ ወር ውስጥ ለኢትዮጵያ አንድነት ሲሉ የተዋደቁትን አፄ ቴዎድሮስ፣ እምዬ ምኒልክንና በላይ ዘለቀን ጫማ ስር ሁነው የኢትዮጵያን ዳግም ከፍታ አሳይተውናል፡፡ የእናት ኢትዮጵያን ትንሳኤን አብስረውልናል ባይ ነኝ፡፡ ይህ ተጋድሎ የኢትዮጵያዊነትን ልክ ማሳያ ሆኖ ሲዘከር ይኖራል፡፡
በእዚህ ሁሉ የችግር ሰንሰለት ውስጥ ግን የኢትዮጵያ ብሩህ ዘመናትን ከመምጣት የሚያግዳቸው አንዳችም ምድራዊ ሀይል የለም፡፡ የኢትዮጵያ ፀሐይም ትወጣለች፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ፡- “በለቅሶ የሚዘሩ በደስታ ይለቅማሉ” (መዝሙር፡- 125(126)፡5) እንዲል አሁን እየደረሰብን ያለው መከራና ችግር ወደፊት ከተሰጠን ተስፋ ጋር ሲነጻጸር ምንም ማለት እንዳልሆነ እገነዘባለሁ፡፡
 ሁሉን ቻይ የሆንክ እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! ፈቃድህ ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያውያን ጋር ይሁን!…. አሜን
Filed in: Amharic