>

"ወደ ትግራይ ለመመለሳችን ድሮኖች አይነተኛ ምክንያት ናቸው....!!! "(ጻድቃን ገ/ተንሳይ)

“ወደ ትግራይ ለመመለሳችን ድሮኖች አይነተኛ ምክንያት ናቸው….!!! “–
ጻድቃን ገ/ተንሳይ

*. … የኢሳያስ ወታደሮችም በተወሰኑ የሰሜን ትግራይ አካባቢዎች እንዳሉ ናቸው። የኤርትራ ኮማንደሮች አንዳች አይነት ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ እያቀዱ ነው። የኤርትራ መኮንኖች የኢትዮጵያን መካናይዝድ ኃይል እየመሩ ነው ያሉት።

ከሳምንታት በፊት በርካታ የአማራ ክልል ከተሞችን ተቆጣጥሮ ከአዲስ አበባ ከ200 ኪሎ ሜትሮች ባነሰ ርቀት ውስጥ ደርሰው የነበሩት የህወሓት ኃይሎች አሁን ከ450 ኪሎ ሜትሮች በላይ ወደ ኋላ አፈግፍገው ወደ ትግራይ መመለሳቸውን ገልጸዋል።

ከሳምንታት በፊት የህወሓት ኃይሎች ወደ ዋና ከተማዋ አዲስ አበባ እየተቃረቡ በነበረበት ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እራሳቸው ወደ ጦር ሜዳ በመሄድ የአገሪቱን ሠራዊት ለመምራት መወሰናቸውን ተክተሎ የአማጺያኑ ግስጋሴ ተገትቷል።
በተከታታይም ከአፋር ክልል የተለያዩ አካባቢዎች፣ ከአማራ ክልል ከሰሜን ሸዋ፣ ከደቡብ ወሎ እንዲሁም ከሰሜን ወሎ ቁልፍ ስፍራዎች ተገፍተው ለመውጣት መገደዳቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት ገልጿል።
የህወሓት መሪዎች ግን በቀዳሚነት በስልታዊ ውሳኔ ይዘዋቸው የነበሩ ቦታዎችን መልቀቃቸውን ሲገልጹ ከቆዩ በኋላ፣ ካለፈው ሳምንት ማብቂያ ወዲህ ደግሞ “ለሰላም ዕድል” ለመስጠት ሲባል ኃይሎቻቸውን ከአፋርና ከአማራ ክልሎች ማስወጣታቸውን በመግለጽ ለንግግር ዝግጁ መሆናቸውን አሳውቀዋል።
የህወሓት ኃይሎች ወደ አዲስ አበባ እያመሩ በነበረበት ወቅት በትግራይ ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው ጦርነቱ ማብቃቱንና የኢትዮጵያ መንግሥት በመሸነፉ ለድርድር ከእነሱ ጋር ሊቀመጥ የሚችል ኃይል እንደሌለ ሲናገሩ የነበሩት ጄነራል ጻድቃን ገብረ ተንሳይ ከቢቢሲ ኒውስ አወር ፕሮግራም ጋር አጭር ቆይታ አድርገው ነበር።
ጄነራል ጻድቃን የቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራዊት ኤታማዦር ሹም የነበሩ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ የአማጺያኑ ወታደራዊ አመራር ዕዝ አባል ናቸው። የኢትዮጵያ መንግሥት ህወሓትን በሽብርተኛ ድርጅትንት የፈረጀው ሲሆን፣ ጄነራል ጻድቃን ደግሞ የጦርነቱ መጀመርን ተከትሎ በአገር መክዳት ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል።
ቢቢሲ ኒውስ አወር፡ በአሁኑ ጊዜ በጦርነቱ ዙሪያ የታየውን ለውጥ እንዴት ይገልጹታል?
ጄነራል ጻድቃን፡ በአሁኑ ጊዜ አብዛኛው ሠራዊታችን በሕገ መንግሥቱ በተረጋገጠው የትግራይ ግዛት ውስጥ ነው ያለው። የተወሰኑ አሁንም ወደ ትግራይ እየተመለሱ ያሉ ተዋጊዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ለደኅንነት ሲባልም እዚህም እዚያም እንዲቆዩ የተደረጉ አሉ። ዞሮ ዞሮ አብዛኛው ሠራዊታቸን ትግራይ ውስጥ ነው።
ልብ ሊባል የሚገባው ይህንን ፖለቲካዊ ውሳኔ የወሰንነው መላው ምዕራብ ትግራይ በኤርትራና በኢትዮጵያ ሠራዊትና በአጋሮቹ ኃይሎች ተይዞ ሳለ ነው። የተወሰኑ የኢሳያስ ወታደሮችም በተወሰኑ የሰሜን ትግራይ አካባቢዎች እንዳሉ ናቸው። የኤርትራ ኮማንደሮች አንዳች አይነት ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ እያቀዱ ነው። የኤርትራ መኮንኖች የኢትዮጵያን መካናይዝድ ኃይል እየመሩ ነው ያሉት።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ኃይሎቻችንን ለማስወጣት ወስነን አብዛኞቹን አስወጥተን ወደ ትግራይ የመለስነው ለሰላም ዕድል ለመስጠት ነው። ቢቢሲ ኒውስ አወር፡ ጄኔራል ጻድቃን ይህ ፖለቲካዊ ውሳኔ ነው ብለዋል። ብዙ ሪፖርቶች የሚያሳዩት ግን ተሸንፋችሁ ማፈግፈጋችሁን ነው። በተለይም የድሮን ጥቃት መቋቋም አለመቻላችሁ ነው ወደ ትግራይ እንድትመለሱ ያደረጋችሁ። አይደለም እንዴ?
ጄነራል ጻድቃን፡ ያ አንድ ምክንያት አይደለም አልልህም። ነገር ግን ብቸኛው ምክንያት አይደለም። ወደ አዲስ አበባ በምንገሰግስበት ጊዜ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ሂደቶች ከወታደራዊ አካሄዳችን ጋር ሊጣጣሙ አልቻሉም። የዲፕሎማቲክ ሁኔታዎች በሚፈለገው መልኩ እየሄዱ አልነበሩም። ይህም አንድ ምክንያት ነበር።በተለይ ግዙፍ ሠራዊታችንን በስንቅና ትጥቅ ሙሉ ለማድረግ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ረዥም ርቀት በሚጓዙበት ጊዜ ለድሮን ጥቃት ተጋልጠው ቆይተዋል። በዚህም ድሮኖቹ በግብአት አቅርቦታችን ላይ ተጽእኖ ፈጥረዋል።
ቢቢሲ ኒውስ አወር፡ የፌዴራል ኃይሎች ጥምረት በምዕራብ ትግራይ፣ የኤርትራ ሠራዊት በሰሜን ትግራይ አለ ብለውኛል። እንደዚያ ከሆነ ለምን እዚያ ላይ አላተኮራችሁም? አዲስ አበባ ለመገስገስ ምናልባት ጓጉታችሁ ይሆን?
ጄነራል ጻድቃን፡ አይደለም። ከመነሻው ግልጽ መሆን ያለበት ነገር አለ። አዲስ አበባን የመቆጣጠር ፍላጎት አልነበረንም። እርግጥ ነው ጦርነቱን በተቻለ ፍጥነት የማጠናቀቅ ጉጉት ነበረን።
በእኛ አስተሳሰብ ወደ ደቡብ ዘመቻ በማድረግ፣ በዚያውም የፖለቲካ ጥምረቱን በተቻለ ፍጥነት በማቀናጀት መንግሥት ሁሉን አቀፍ ለሆነ ንግግር እንዲቀመጥ እናስገድደዋለን ብለን ነበር። በዚህ መልኩ ጫና መፍጠር አቋራጭ ሆኖ ነበር የታየን። ይህን ብናደርግ ያለንበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ያቃልልልናል ብለን ነበር የገመትነው።
ቢቢሲ ኒውስ አወር፡ ብዙ ጊዜ ስለ ሁሉን አቀፍ ንግግር ያነሳሉ። ህወሓት በ30 ዓመት የሥልጣን ቆይታው የተነሳ በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዘንድ በጎ ስም የሌለውና የሚፈራ መሆኑ ላይ ምን ያህል ይስማማሉ? በቅርቡ ደግሞ በአፋርና በአማራ ክልል ውስጥ ወታደሮቻችሁ በፈጸሙት የጅምላ ግድያዎች፣ ሴቶችን መድፈርና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ምናልባትም የጦር ወንጀሎች የተነሳ ስማችሁ መልካም አይደለም። በዚህ የተነሳ አብዛኛው ኢትዮጵያ ህወሓት አስፈሪ ኃይል ስለሆነ መሸነፍ አለበት ብሎ በማመኑ ጉዳይ ላይ ምን ይላሉ?
ጄነራል ጻድቃን፡ የትግራይ ጦርነት ለትግራይ ራስን የመከላከልና ጭቆናን እምቢኝ የማለት ሕዝባዊ ጦርነት ነው። በጄኔቫ የመርማሪ ቡድን ለማቋቋም ተወስኗል። ቡድኑ በመላው ኢትዮጵያ እንዲሁም በእኛ ኃይሎች ተፈጽሟል ስለሚባለው ሰብአዊ መብቶች ጥሰት ዙርያ ምርመራ እንዲያደርግ ነው የተቋቋመው። ያንን በጸጋ ተቀብለናል።
በአማራና በአፋር የእኛ ኃይሎች ስለፈጸሙት ጭፍጨፋዎች ጠይቀኸኛል። እንደተባለው ጥሰት ተፈጽሞ እንኳ ቢሆን በትግራይ ላይ የተፈጸመው ሰብአዊ ጥሰት እጅግ የከፋ ነው።
በኤርትራና በኢትዯጵያ ኃይሎች የተፈጸመው ሰብአዊ ጥሰት እጅግ ግዙፍና ዘግናኝ ነው። አሁን ማለት የምችለው በጄኔቫ የተወሰነው ውሳኔ ይበል የሚያሰኝ መሆኑን ነው። መጥተው ይመርምሩና ያን ጊዜ እንፍረድ።
Filed in: Amharic