>

ብልጽግና ወንጌል ሃሰተኛ ትምህርት ብቻ አይደለም ....!?! (ደረጄ ከበደ)

ብልጽግና ወንጌል ሃሰተኛ ትምህርት ብቻ አይደለም ….!?!
ደረጄ ከበደ

ስለብልጽግና ወንጌል ሰባኪዎች ስናነሳ ብዙዎቻችን “ሃሰተኛ ወንጌል አስተማሪዎች” በሚል ሰይመን እናልፋቸዋለን። ጉዳዩ ግን ከዛ እጅግ የከፋ ነው። 
“ብልጽግና ወንጌል ፓንዚ ስኪም (ponzi scheme) የሚባለውን የፍሮድ (Fraud) አይነት መቶ በመቶም ባይሆን በአብዛኛው ይመስለዋል። ፖንዚ ታተርፋላችሁ በሚል ቅስቀሳ ሰዎች ለፍተው ያፈሩትን ገንዘብ ኢንቨስት (invest) እንዲያደርጉ ካደረገ በሁዋላ ሃሰተኛ ዶኩሜንት እየሰራ ትርፍ አትርፋችሁዋል ይላቸዋል። ሰዎችም የበለጠ እናተርፋለን በሚል ያለ የሌለ ሃብታቸውን ፖንዚውን ለሚያስኬደው ሰው ሲገብሩ ኖረው በመጨረሻም እንደተጭበረበሩና ሙልጭ እንደወጡ ይረዱታል።
በአሚሪካን ሃገር ታሪክ በትልቅነቱ ቁጥር አንድ የሆነው ፓንዚ የተካሄደው በበርናርድ ሎሬንስ ሜዶፍ (Bernard Lawrence Madoff) ሲሆን፣ ያ ሰው 64.8 ቢሊዮን የደረሰ የኢንቬስተሮች ገንዘብ ያጭበረበረበትን አውታረ-መረብ ሳይነቃበት ከ 17 አመታት በላይ አስኪዶታል ። ሜዶፍ ሲያዝና ፍርድ ቤት ሲቀርብ፣ ሲፈረድበትም አሚሪካ ነበርኩ፣ ተከታትዬዋለሁ። ፍርድ ቤት የ 150 አመት እስራት ፈርዶበት በእስርቤት እንዳለ ሚያዝያ 14/ 2021 አርፎአል።
ብልጽግና ወንጌል፣ በመንፈሳዊ ስም በተለበጡ ተቁዋማት ስር የተከማቹ በርናርድ ሜዶፎች፣ መጸሃፍቅዱስን ከፍተው፣ ምእመና ገንዘባቸውን ለትርፍ ኢንቨስት እንዲያደርጉ በማባበልና በማታለል፤ ከደሃ እስከሃብታም በላባቸው ያፈሩትን ገንዘብ እንዲሰጡና በምላሹ ከሰማይ 100 እጥፍ ገንዘብ እንደሚያገኙ የሚያሳምን ፓንዚ ነው። ያ ብቻ ሳይሆን ገንዘባችሁን ከሰጣችሁ አትታመሙም በሚል ማታለያ ብዙዎችን ማራቆቻ መንገድ ነው። ብልጽግና ወንጌል መጸሃፍ ቅዱስን ባለመረዳት ወይም ካለማወቅ በተሳሳቱ ሰዎች የተፈጠረ ጽንሰሃሳብ ሳይሆን፣ ሆን ተብሎ የሰዎችን ገንዘብ እንደበርናርድ ሜዶፍ እየዋሹ የመዝረፍን አጭበርባሪነትን፣ መሰሪነትንና ሌብነትን ያካተተ በብዙ አመታት ጽኑ እስራት የሚያስቀጣ ወንጀል ነው። የብልጽግና ወንጌል ትምህርትን ከወንጀል ተርታ ያሰለፈው፣ ሰባኪዎቹ ከምእመናኑ የሰበሰቡትን ገንዘብ ወደግል ባንክ ሳጥናቸው በማስገባታቸው ነው። ያ ተግባራቸው ብልጽግና ወንጌል ሰባኪዎችን “በርናርድ ሎሬንስ ሜዶፎች” አድርጎአቸዋል
እናም ዛሬ የሃገራችን ፕሮቴስታንት ተቁዋም፣ ምስኪኑን ህዝብ በመንግስት እውቅና በሚዘርፉ፣ የአቢይ አህመድ የቤተመንግስት ቡና አጣጭ በሆኑ፣ በወንጌል ስም ፓንዚ እያኪያሄዱ ባሉ ወንጀለኞች ተበክላለች። በቦዲጋርድ በአደባባይ ታጅበው የሚንቀሳቀሱ፣ ህግና ሞራል ያለው መንግስት ቢኖር ኖሮ ጸጉራቸውን ተላጭተው እንደ በርናርድ ማዶፍ በ 150 አመት የእስራት ፍርድ ወህኒ መበስበስ ይገባቸው የነበሩ፣ በእግዚአብሄር የሚሳለቁ የህብረተሰብ ካንሰሮች፥ ያለስጋት እየፉዋለሉ ነው።
የአሳ ግማቱ ከአናቱ እንደሚባል አራት ኪሎ በወስላታዎችና በቁማርተኞች ተሞልቶ፣ አገር እንዳትጠፋ፤ ቤተክርስትያን የአስረሽ ምቺው መድረክ እንዳትሆን፣ የሚያግድ ከልካይ የለም/አይኖርምም። የመንግስት ወንጀለኞችን አቃፊነት፣ የፖሊቲካውን ሰፈር ብቻ ሳይሆን የመንፈሳዊውንም ጎራ በስርአተ አልበኞችና በወንጌል ሸቃጮች በክሎት እያየን ነው።
Filed in: Amharic