>

"ገናን/ልደትን በቅዱሳኑ መንደር በላስታ ላሊበላ እናሳልፍ! (ውብሸት ሙላት )

“ገናን/ልደትን በቅዱሳኑ መንደር በላስታ ላሊበላ እናሳልፍ!
ውብሸት ሙላት 

እመኪና መድሃኔ ዓለም (በስውሩ ፈርጥ፣በአቡነ ዮሴፍ ተራራ ጉያ)
የአቡነ ዮሴፍ ተራራ ከእጸዋቱ፣ ከእንሰሳቱና ከአእዋፉ በተጨማሪ አስደናቂ ቤተ ክርስቲያናትን ይዟል፡፡ በጣም የሚታወቁት ይምርሃነ ክርስቶስ፣አሸተን ማርያምና ገነተ ማርያም ናቸው፡፡ ገነተ ማርያም የተገነባው በዐጼ ይኩኖ አምላክ ሲኾን ይምርሃነ ክርስቶስ በራሱ በንጉሠ ነገሥቱ ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ ነው፡፡ አሸተን ደግሞ በንጉሠ ነገሥቱ በቅዱስ ላሊ በላ ነው፡፡
ከእነዚህ በተጨማሪና እምብዛም ዕውቅና የሌላቸው ነገር ግን በአሠራር ጥበባቸውም የዘመኑን የኪነ ሕንጻ ጥበብ የሚያሳዩም ለቱሪስት መስህብም የሚሆኑ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት አሉ፡፡ ቁጥር አንድ ተጠቃሹ እመኪና መድሃኔ ዓለም ነው፡፡ እመኪና መድሃኔ ዓለምም እየተባለ ይጠራል፡፡ በተለያዩ ድርሳናትም እንዲሁ በሁለቱም ስም ሲጠቀስ ይስተዋላል፡፡
እመኪና መድሃኔ ዓለም ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው ትረካ መሠረት የተገነባው በ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው፡፡ የእናትና ልጅም ታሪክም አለው፡፡
ይሁን እንጂ በርካታ የጥናት  ውጤቶች እንደሚሉት ከሆነ በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዐጼ ይኩኖ አምላክ ነው የተገነባው፡፡ አሠራሩ እንደ ይምርሃነ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን በዋሻ ውስጥ ነው፡፡ ዋሻ ውስጥ ግንብ መገንባት ራሱን የቻለ ጥበብ ይፈልጋል፡፡ እመኪና መድሃኔ ዓለምም ከይምርሃነ ክርስቶስ ጋር የሚቀራረብና ከእዚህ የቀጠለ ጥበብና አሠራር የያዘ ይመስላል፡፡
በርካታ የውጭ አገር ተመራማሪዎች በዋሻ ውስጥ ውሃ እያለ፣ የዋሻው ወለል ያልተስተካከለና ተጨማሪ ማስተካከያ ስለሚፈልግ፣ እንዲሁም በዋሻው ውስጥ ዝናብና ጸሐይ ስለማይኖር ከዚያው ጋር በሚስማማ ሁኔታና ከግምት ያስገባ አሠራርን ይጠይቃል፡፡
የአገራችን ሳይሆኑ የውጮቹ አጥንተውታል፡፡ የአገር ውስጥ ባለሙያው ካለማጥናቱ ባለፈም፣ መንግሥትም ይሁን በቱሪዝም ዘርፉ ላይ የተሠማሩት ሲያስተዋውቁት አይታይም፡፡ ሚዲያውም ቢሆን ጆሮ ዳባ ልበስ እንዳለው ነው፡፡
እመኪና መድሃኔ ዓለም፣ ከላሊበላ ከተማ በእግር አምስት ሰዓት ገደማ፣ ከገነተ ማርያም (ከኩል መስክ) ደግሞ 2 ሰዓት አካባቢ በእግር ቢኬድ ይደረሳል፡፡ የተራራ ጉዞ ማዘጋጀት፣ለገናና ለሌሎችም በዓላት ጊዜ ተጓዦችን በፓኬጅ ወደ እመኪና መድሃኔ ዓለም እንዲሄዱ ቢበረታቱ ተጓዡ እንደሚጨምር፣ እያደርም የውጭ ቱሪስቶች የጉዟቸው አካል እንዲያደርት ማስተዋወቅ ያስፈልጋል፡፡
(Michael Gervers, “An Architectural Survey of the Church of Emakina Madihane Alam (Lasta,Ethiopia)”,በሚል የጻፈውን እና Institute of Ethiopian Studies በ Warsaw University ባደረገው ጉበኤ ላይ የቀረበውን ሥራ ቢመልከቱ መጠነኛ ግንዛቤ ያገኛሉ፡፡
ለበረከት ይሁን።
Filed in: Amharic