>

አቶ ስብሐት ነጋን ጨምሮ 5 ተከሳሾች በህመም ምክንያት ዛሬ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ቀሩ...!!! (ነጋሪት)

አቶ ስብሐት ነጋን ጨምሮ 5 ተከሳሾች በህመም ምክንያት ዛሬ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ቀሩ…!!!
ነጋሪት

አሞናል በማለት አቶ ስብሐት ነጋ ፣ አቶ አባዲ ዘሙ፣ አቶ ዘሚካኤል አንባዬ፣ ዶ/ር ሙላት ይርጋ እና አቶ ቴድሮስ ሀጓስ ዛሬ ፍርድ ቤት አልቀረቡም።
የማረሚያ ቤት ተወካይ አምስቱ ተከሳሾች አሞናል በማለታቸው ምክንያት እንዳላመጣቸው አስረድቷል።
ቀሪዎቹ ማለትም ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም ፣ አንባሳደር አባይ ወልዱ ፣ ዶ/ር አብርሐም ተከስተ ፣ ዶ/ር ሰለሞን ኪዳኔ፣ አንባሳደር አዲስ አለም ባሌማ ፣ ወ/ሮ ሙሉ ገ/ እግዛብሔርን ጨምሮ 16 ተከሳሾች ግን በችሎት ተገኝተዋል።
16 ቱ ተከሳሾች የቀረቡት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ ሽብርና የህገመንግስታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።
ችሎቱ ዛሬ በተከሳሾች መዝገብ ላይ የተሰየመው የተከሳሾችን የክስ መቃወሚያ ውጤት ለመጠባበቅ እና ሱር ኮንስትራክሽንን ጨምሮ በክሱ የተካተቱ ድርጅቶች መጥሪያ እንዲደርሳቸው የተሰጠውን ትዛዝ ማረጋገጫ ውጤት ለመጠባበቅ እንዲሁም በ44 ኛ ተከሳሽ ለምርመራ የተያዘብኝ ሰነዶች ይመለሱልኝ ሲሉ ያቀረቡት አቤቱታ ላይ ትዛዝ ለመስጠት ነበር።
ችሎቱ ስራውን እንደጀመረ ዶ/ ር አብርሐም ተከስተ ሁለት ጠበቆቻችን ታስረዋል ቀሪዎቹም ከፍተኛ ስጋት ስላለባቸው አልመጡም ስለዚህ ጠበቆቻችን በሌሉበት ጉዳያችን ሊታይ አንፈልግም ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠን ያሉ ቢሆንም የተከሳሾች አንደኛው ጠበቃ ክፍላይ መሐሪ ግን ዘግይተው በችሎት ተገኝተዋል።
ይሁንና ጠበቃው ባለፈው ቀጠሮ በዕስር ላይ ይገኛል በተባለው አንደኛው ጠበቃ ላፖቶፕ ኮምፒዩተር ላይ የክስ መቃወሚያ መኖሩን ተከትሎ የክስ መቃወሚያውን አግኝተው በተረጋጋ መልኩ ተወያይተው ማቅረብ አለመቻላቸውን ጠቅሰዋል።
አዲስ መቃወሚያ ለማቅረብ የታሰሩት ጠበቆች ሀሳብ አካቶ አሟልተው ለማቅረብ እንደሚቸግራቸው አክለዋል።
በዚህም ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው የጠየቁ ሲሆን ፍርድ ቤቱም የክስ መቃወሚያውን ብቻ ለመጠባበቅ ለጥር 30 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ሰቷል።
ተከሳሽ ወ/ሮ ሙሉ ገ/እግዛብሔር ልጃቸው እንደታመመችና እንደታሰረች በመግለጽ በአጃቢ ወጥቼ እንድጠይቃት ይፈቀድልኝ ሲሉ አመልክተዋል።
ወ/ሮ ኬርያ ኢብራሂም በበኩላቸው ማስታወሻ ደብተራችን ለምርመራ እየተወሰደብን በመሆኑ ማስታወሻ ደብተር እና በቋንቋችን ስልክ ማውራት እንዲፈቀድልን ይታዘዝልን ሲሉ አመልክተዋል።
ዶ/ር ሰለሞን ኪዳኔ በበኩላቸው በማረሚያቤት በተለያዩ ቦታዎች የታሰርን መሆኑን ተከትሎ ተሰብስበን ለመወያየት ባለመቻላችን ተገናኝተን  ለመወያየት ይፈቀድልን ብለዋል።
በተጨማሪም የተሰጠንን የክስ ቻርጅ ሲዲን ለመመልከት ኮምፒዩተር ይፈቀድል ሲሉም ዶ/ር ሰለሞን አመልክተዋል።
ለምርመራ የክስ ቻርጁና ማስረጃ የተካተተበት ሲዲና ፍላሽ በማረሚያ ተወስዶ የተመለሰ ቢሆንም ተቀንሶ ወይም ሌላ ተካቶ ሊሆን ስለሚችል ብለን አልተቀበልንም በድጋሚ አዲስ ፍላሽ ይሰጠን ሲሉም ተከሳሾቹ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።
በተነሱ አቤቱታዎች ላይ ብቻ ትዛዝ ለመስጠት ፍርድ ቤቱ ለታሳስ 27 ቀን የቀጠረ ሲሆን ማረሚያ ቤቱም አቤቱታ ያቀረቡ ተከሳሾችን ብቻ ነጥሎ እንዲያቀርብ ትዛዝ ሰቷል።
የ44 ኛ ተከሳሽ ዘሚካኤል አንባዬ ባለፈው ያቀረቡት ለምርመራ የተወሰደብኝ ሰነዶቼ ይመለሱልኝ አቤቱታን በተመለከተ ጠበቃው ትዛዝ እንዲሰጥ የጠየቁ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ ባሉበት ትዛዝ እንደሚሰጥ በምላሽ ሰቷል።
በክሱ የተካተቱ ድርጅቶች መጥሪያ እንዲደርሳቸው በድጋሚ ፍርድ ቤቱ ትዛዝ ሰቷል።
Filed in: Amharic