>

ህወሃት ግጭት ካልቀፈቀፈ መኖር አይችልም፤ (ነጋሪት)

ህወሃት ግጭት ካልቀፈቀፈ መኖር አይችልም፤
ጦርነት ካላካሄደ፣ የትግራይ ህዝብ ጥያቄዎቹን በጆንያ ተሸክሞ ይመጣል…!!!
ነጋሪት

 የተራረፈና የጠወለገ ሃይሉን አሰባስቦ፣ ለመልሶ ማጥቃት እየተዘጋጀ እንደሆነ እንሰማለን። ህወሃት የሰዎች በህይወት መኖር የሚከፋው፣ በመሞታቸው ደግሞ የሚደሰት አይነት ድርጅት ነው።
ህወሃት ከሲኦል አፍ የተረፉ ወጣቶችን፣ መልሶ ወደ ሲኦል ለመላክ የሚያደርገው ዝግጅት ቢያንስ ሶስት አላማዎችን ታሳቢ ያደረገ ነው፦
አንደኛው፣ ለፈረንጆቹ እስትንፋሳቸው እንዳልወጣ ለማሳየትና የድርድሩን ስራ እንዳይዘነጉት ለማሳሰብ ነው። ጌታቸው ረዳ በዛን ሰሞን ” ነጮቹ በእኛ ስቃይ ላይ ቆመው ገናን ያከብራሉ” ብሎ አማሮ ሲጽፍ ነበር።
ሁለተኛው፣ ጦርነት ካላካሄደ፣ የትግራይ ህዝብ ጥያቄዎቹን በጆንያ ተሸክሞ ይመጣል። ጥያቄዎቹን ለመመለስ ደግሞ ደብረጺዮን አይኑን በሻሽ ሸፍኖ አብይ አህመድን ደጅ መጥናት አለበት፤ ደጅ መጥናት ብቻ ሳይሆን፣ አብይ የሚያዝለትን ኪኒን መዋጥም አለበት። በእነ ደብረጺዮን አይን ጦርነት አለማካሄደም ሆነ አብይ አህመድን ደጅ መጥናት እኩል ዋጋ ያስከፍላሉ። ስለዚህ ሶስተኛ አማራጭ መፈለግ አለበት። ያም አማራጭ ትግራይን በማያቋርጥ ጦርነት ውስጥ መክተት ነው። የማያቋርጥ ጦርነት ካካሄደ፣ ህዝብ ” ጦርነት ላይ ናቸው” ብሎ ለጊዜው አይነሳበትም። ቢነሳበትም “ለደህንነት ሲባል እርምጃ ወስጃለሁ” እያለ፣ እየገደለ፣ ጸጥ ያሰኘዋል። ይህ  የመሞቻ ጊዜን ትንሽም ቢሆን ያራዝማል።
ሶስተኛው አላማ፣  ታጣቂውን ከሞራል ውድቀት ለመከላከል ነው። ህወሃት ከኮምቦልቻ የእርዳታ መጋዝን ብቻ የዘረፈው ምግብ፣ ሰራዊቱን ቢያንስ ለሶስት ወራት ያክል ይመግብለታል። ከዚያ በኋላ ግን ታጣቂዎቹ የሚመገቡት አይኖራቸውም። በደንብ የማይመገብ ወታደር ደግሞ የውጊያ ሞራሉ ይወድቃል። ሞራሉ መውደቁ ብቻ ሳይሆን፣ ውስጥ ለውስጥ ማጉረምረምና መጥፋት ይጀምራል። አላማ የሌለውን ሰራዊት ሞራል ለመጠበቅ፣ ጥሩ ቀለብ ወሳኝ ነው። ህወሃት የቀለብ እጥረት የሚያመጣበት ችግር ለመከላከል ታጣቂዎቹን በማያቋርጥ ጦርነት ውስጥ መክተት አለበት። ጦርነት ውስጥ ከከተታቸው 50 በመቶ የመሞት፣ 50 በመቶ ደግሞ ቀምቶ የመብላት እድል ይኖራቸዋል። ጦርነት ውስጥ ካልከተታቸው ግን በረሃብ የመሞታቸው እድል 100 በመቶ ይሆናል። ስለዚህ ይህን የአንበሳና ጎፈር ጨዋታ እየተጫወቱ እድልን ከመሞከር ውጭ ሌላ አማራጭ የለም።
መንግስት የሚውስዳቸው የመልስ ምቶች እነዚህን ምክንያቶች ( አላማዎች)ታሳቢ ያደረገ እንደሚሆን አምናለሁ። የተራበን ወይም ልራብ ነው ብሎ የሚሰጋን ስብስብ መቼ ነው ማጥቃት ያለብኝ ብሎ አስቦ ቅድመ ዝግጅት እያደርገ እንደሆነ እገምታለሁ። ህወሃት በፈረንጅ ላይ ያለው እምነቱ እየተሸረሸረ ነው። የህወሃት ህልውና በጆ ባይደን ሳይሆን በአብይ አህመድ እጅ ላይ ነው። ፈረንጆችም  አሜሪካ) ይህን ታሳቢ አድርገው በኢትዮጵያ ላይ ሌላ ዘዴ እየሸረቡ እንደሆነ እገምታለሁ። በሌላ ጽሁፍ እመለስበታለሁ።
Filed in: Amharic