>

“ፊልድ ማርሻልነት በዘራችሁ አይድረስ!!” (ዳግማዊ ጉዱ ካሣ)

“ፊልድ ማርሻልነት በዘራችሁ አይድረስ!!”

 

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ


ከወያኔ በላይ ሀፍረተ-ቢስ፣ ከወያኔ በላይ ዋሾና አጭበርባሪ፣ ከወያኔ በላይ ራሱ የገደለውን ሰው አፋልጉኝ ባይ ወደር-የለሽ አስመሳይ፣ ከወያኔ በላይ ተጨፈኑ ላሞኛችሁ ባይ፣ ከወያኔ በላይ የከረፋ ዘረኛ … በዚህች ምድር ይኖራል ብዬ ፈጽሞውን አልገመትኩም ነበር – ለካንስ ጊዜና አጋጣሚ ግምትን ያዛባሉ፡፡ ለ27 ዓመታት ካለተወዳዳሪ ብቻውን ይፈነጭበት በነበረው የኢትዮጵያ የዘር ፖለቲካ ወያኔ ካላንዳች ይሉኝታና ሀፍረት እንደፈለገው ይፈነጭ ስለነበር ሌላ ከእርሱም ይበልጥ አጭበርባሪ ሊኖር መቻሉን የማወቅ ዕድል አልነበረኝምና በሤራና በሸፍጥ እንዲሁም በማስመሰልና በቆርጦ ቀጥልነት እነሱን የሚያስከነዳ ለዚያውም በራሳቸው ጓዳ የተወለደና በእብለትና በዘረኝነት የሀሰት ትርክት ተኮትኩቶ ያደገ ሃሳዊ መሢሕ ወደሥልጣን ማማ ይወጣል ብዬ እንኳን በውኔ በህልሜም አይቼው አላውቅም፡፡ ከመለስ የበለጠ እባብ ይፈጠራል ብሎ ማን ሊጠረጠር ይችላል! የመለስ ንቀት ከአቢይ ጋር ሲነጻጸር የመለስ ለከት ነበረው፤“የባሰ አለ አገርህን አትልቀቅ” ነው ነገሩ፡፡ 

አሁን በገሃድ እንደምናየው ታዲያ “ከመምህሩ ደቀ መዝሙሩ” እንዲሉ ሆነና ከወያኔ ማሕጸን የተገኘው አቢይ አህመድ የኢትዮጵያን ብቻ ሣይሆን የመላውን ዓለም የአስመሳዮችና የአጭበርባሪዎች ሪከርድ በጣጥሶ የጣለ በማስመሰልና በውሸት ንግግር የአንደኞች አንደኛ፣ የቁንጮዎች ቁንጮ ሊሆን በቃ፡፡ የሚገርም ተፈጥሮ ነው፡፡ ማስመሰልና መዋሸት አያስቀኑም እንጂ ቢቀናባቸው ኖሮ የመጀመሪያው ቀኚ እኔው ነበርኩ፡፡ የሚደንቀው ሌላው ነገር አቢይ ሲዋሽና ሲያምታታ ወይ ሲያጭበረብር ከመንገድ ላይ ቁጭ በሉዎች ወይም ማጂራት መቺዎች እጅግ በሚልቅ ሁኔታ አንዳችም ዝግንን አይለውም፡፡ ለርሱ መዋሸትና ማስመሰል የተፈጥሮ መክሊቱ ስለሆነ በሀፍረትና በይሉኝታ ሊሸማቀቅ ይችል የነበረው እውነትን የሚከተል ቢሆን ነበር፡፡ ተፈጥሮን ደግሞ ተመክሮ አይመልሰውም፡፡ እናም ይህ አቢይ በምንም ዓይነት ትምህርትና ተግሳጽ ወደኅሊናው ስለማይመለስ ለኢትዮጵያ ትንሣኤ ዋናው ቅድመ ሁኔታ የሰውዬው ከሥልጣን መባረርና ወደፍርድ መቅረብ ነው፡፡

ሣተናው የሕወሓት ልጅ አቢይ አህመድ ሰሞኑን በሰዓታት ልዩነት ሁለት ለጊነስ ቡክ ኦፍ ሪከርድስ የሚበቁ አስደማሚ ተግባራትን ፈጽሟል፡፡ አንደኛው በቀደምለት የተሰማኝን የገለጽኩበት የወንጀለኞች መፈታት ሲሆን በማግሥቱ ደግሞ ይበልጥ ይግረማችሁ ብሎ በዓለም ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ ወታደራዊ ሹመትና ማዕረግ መስጠቱ ነው፡፡ እንደሦስተኛ አስነዋሪ ድርጊት ሊቆጠርለት የሚገባ አንድ ነገርም መጥቀስ ይቻላል፡፡ እሱም የነስብሃት ነጋን መፈታት ሲሰማ አቢይ ራሱ መደንገጡን በአራዶች ቋንቋ ምንም “ሳይሸምመው” በአደባባይ የተናገረው ነው፡፡ ውሸትና ግነት ገደብ አጣ፡፡ አጉል ድፍረትና ሕዝብን መናቅ ወሰን ጠፋለት፡፡ 

ስለሀገር የሚወሰኑ ታላላቅ ድንጋጌዎችንና አንዳንድ ወሳኝ ጉዳዮችን ልክ እንደማንኛውም ተራ ዜጋ ማታ በቴሌቪዥን መስኮት ይሰማ እንደነበር ገልቱው ቤተ መንግሥት ጠባቂ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከወያኔ አለቆቹ በስልክና በብጣሽ ወረቀት የሚሰጠውን ትዕዛዝ ከሚያስፈጽምበት ቤተ መንግሥት በወጣ ሰሞን ተናግሮ ነበር፡፡ ይህኛው ግን ማንን እንደሚያታልል እዬቆዬ ሲያስበው ለራሱም ግራ ሳይገባው አይቀርም ራሱ ወስኖ በራሱ አጋፋሪዎች ከእስር የፈታቸውን ሰዎች ከእስር መፈታታቸውን እንዳላወቀና ከሚዲያ ሲሰማ ግን እንደማንኛውም ተራ ዜጋ ክው ብሎ እንደደነገጠ መግለጹ የሰውዬው ሥነ ልቦናዊና አእምሯዊ ጤንነት አደጋ ላይ ለመውደቁ ትልቅ ማስረጃ ነው፡፡ እርሱ ካልፈታቸው ማን ፈታቸው? የሀገሪቱ መሪ ማን ነው? መፈታታቸውንስ ከየትኛው ሚዲያና ከማን አንደበት ሰማ? እንዲያው ቢዋሽ ቢዋሽ እስከዚህን መዋሸት ነበረበት ወይ? እንደዚያ መበጥረቅንስ ምን አመጣው? ማንን ለማታለል? በዚህ የሕጻን ሥራ ከራሱ በስተቀር ማንንም ማነሁለል አይችልም፡፡ ለማንኛውም የዚህን አስቀያሚ ግለሰብ ነገር ለታሪክ ፍርድ ልተወውና ወደአስቂኙ ሹመቱ ልለፍ፡፡

ምንም ዓይነት መዝገብ ማገላበጥ አይኖርብኝም፡፡ የማንኛችንም ተራ ዕውቀት ነው፡፡ በሲቪሉም ሆነ በወታደራዊው ጠገግ አንድ ዜጋ ምን ሲያደርግ ለከፍተኛ ሹመትና ማዕረግ እንደሚደርስ ብዙዎቻችን በጥራዝ ነጠቅም ቢሆን እናውቃለን፡፡ ከዚህ ነጥብ አኳያ የሰሞኑን የአቢይ ወታደራዊ ሹመት ስናጤነው የለየለትና አንቱ የተባለ ዕብደት እንጂ የጤንነት አይደለም፡፡ 

ሲጀመር በሀገር የርስ በርስ ጦርነት አንድ ሰው የፈለገውን ያህል ንብና ተርብ ይሁን ወንድሙን ለገደለ ወይ ላስገደለ ወንድም የፊልድ ማርሻል ወታደራዊ ማዕረግ አይሰጥም፤ እንዲህ ያለ ቧልትና ፌዝም የትም የለም፡፡ ፊልድ ማርሻልነት የቡና ቁርስ አይደለም – እስከዚህም ሊቀለድበት አይገባም፡፡ የዓለማችንን ፊልድ ማርሻሎች ቁጥር ለማወቅ መዛግብትን ብናገላብጥ ምናልባት ከጥቂት መቶዎች አያልፍም ይሆናል፡፡ ለምሣሌ አፍሪካዊቷን ናይጄሪያ ጨምሮ በርካታ የዓለም ሀገሮች ፊልድ ማርሻልም ሆነ ማርሻል የሚባል ማዕረግ ሰጥተው አያውቁም፤ ፓኪስታን አንድ ጊዜ ብቻ ሰጥታለች፤ ትልቋ ሀገር ህንድ ሦስት ወይንም ሁለት ብቻ ናቸው ያሏት፡፡ አሜሪካ በዚህ ማዕረግ ከናካቴው አትጠቀምም፡፡ ከብዙዎቹ የዓለም ፊልድ ማርሻሎች ደግሞ የተወሰኑት ባለቤቶቹም ሳያውቁት ከሞቱ በኋላ ነው የተሰጣቸው፡፡ ከኢዲ አሚን ዳዳ የተኮረጀው የአቢይ የማዕረግ አሰጣጥ አንድም ብዙዎቻችን ጠንቅቀን ለምናውቅለት ዓላማ ነው፤ አንድም ወታደራዊ ደምብና ሥርዓትን ካለማወቅ የሚመነጭ ድንቁርና ነው፣ አንድም “ያሻኝን ባደርግ ማን ምናባቱ ያመጣል?” ከሚል ትዕቢትና ዕብሪት የመነጨ ነው – ሁሉም ግን አቢቹን ገደል የሚከቱት የ“አኪለስ ተረከዞች” ናቸው፤ እርሱ በድድብና ሞራ አንዴውኑ ኅሊናው ስለተሸፈነ ምንም ቢሉት አይገባውም፡፡ እንጂማ ወንድሞቼና እህቶቼ – ኢትዮጵያ ከግብጽና ከሱዳን ጋር አልተዋጋችም፤ ኢትዮጵያ ከኬንያና ከታንዛኒያ ወይንም ከማሊና ከቻድ ጋር አልተዋጋችም፡፡ ምኑ ነው ታዲያ ፊልድ ማርሻል የሚያሰጠው? በየትው ውጤታማ የጦርነት እስትራጂ ተመዝኖ? በየትኛው ጀብድና ወደር የሌለው ጀግንነት? እንዴት ተቀልዷል በል! ሆ!!

ሲቀጥል ያ ሁሉ ሹመትና ማዕረግ የተሰጠው ወታደራዊ መኮንን በበላይ ትዕዛዝም ይሁን በውስጣዊ ፍርሃት ከመቀሌና ከሽሬ ፈርጥጦ ወደአዲስ አበባ በመሸሽ ላይ እያለ የኦሮምያ ክልል አጥር የሆነውና እዚያ ወዲያ ግድም የሚገኘው የሸኖና ጫጫ ኮረብታ ነው ያገደው፡፡ እንዳሯሯጡ ቢሆንማ የሆነ ኃይል ምናልባትም ለሌላ አሻጥር አስቦ መከላከያን እዚያ ባያቆመውና ወያኔ ወደኋላዋ ባታፈገፍግ ኖሮ ኢሉባቦር ጎሬን አልፎ ዩጋንዳ ድረስ እንደሚሸሽ ጥርጥር የለኝም፡፡ ለዚህ ዓይነቱ ወታደራዊ አመራር መንግሥቱ ኃይለ ማርያም አሥመራ ውስጥ ያደረገውን የከፍተኛ ማዕረግ ትከሻ ላይ ተለጣፊ ምልክቶችን በመቀስ እየበጣጠሱ ወደ ተራ ወታደርነት ማውረድ እንጂ ትከሻ ሰባሪና ወገብ ለማጭ ማዕረግ ደናቁርት የኦሮሙማ ሰብኣዊ (ሂውማን) ሮቦቶች ላይ መቆለል ተገቢ አልነበረም፡፡ አቢይ ይህን ያደረገበትን ምክንያት ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ እንዲህ ማድረጉ አማራን በማውደም ረገድ ወታደራዊ መኮንኖቹ እጅጉን አስደስተውታል፣ እርካታ በእርካታም አድርገውታል ማለት ነው፡፡ የወታደሮቹን ሽሽትና ማፈግፈግ ሳነሳ ታዲያ መከላከያችን ፈሪና ቦቅቧቃ ነው እያልኩ አይደለም፡፡ ያቺ የአፈግፍጉና ሽሹ፣ መሣሪያቸሁንም ለወራሪው አስረክቡ የምትል ቴክኒክ ሆነ ተብሎ በነሽመልስ አብዲሣና በነአቢይ አህመድ የተቀናበረች አማራንና አካባቢውን የማውደም ዕቅድ አካል ናት፡፡ እንጂ ስንቅና መሣሪያ እያስረከቡ መፈርጠጥ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ነባር ባህል እንዳልሆነ አውቃለሁ፡፡ አሁን የያዘ ይዞት ነው፡፡ ይሄኔ ደግሞ ስንቱ የመከላከያ አባል በሆዱ “እ!” እያለ ቀን ይጠብቃል – ያም ቀን ይመጣል፡፡

ለማንኛውም የአማራን ወታደሮች በዘዴ ማስጨፍጨፍና አማራን ዘሩን ማጥፋት የሚያሾም የሚያሸልም ከሆነ እርግጥ ነው ለብርሃኑ ጁላ ፊልድ ማርሻልነትም ሲያንሰው ነው፡፡ የአማራን ማኅበረሰብ በዐረመኔዎች ማውደምና ታሪክ የማይረሳው ነውር በአማራ ላይ እንዲፈጸም ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር የጄኔራልነት ማዕረግ የሚያስጥ ከሆነ ኦሮሙማዎች በከዚህ መልስ የበተኑት ከፍተኛ ወታደራዊ ማዕረግ ሲያንሳቸው ነው፡፡ በአማራው አካባቢ ይገኙ የነበሩ ከአራትና አምስት ሽህ የሚበልጡ ትምህርት ቤቶችን፣ የመንግሥትና የግል ድርጅቶችን፣ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን … እየነቃቀሉ ወደትግራይ ማስጋዝና ማጓጓዝ ያልተቻለውን ነዳጅ አርከፍክፎ እንዲቃጠሉ ማስድረግ የሚያሸልም ከሆነ ከኦህዲድ ወታደሮች ይበልጥ ሊሸለም የሚገባው ዐውሬ ማለቴ አሻጥረኛና ዘረኛ አዋጊ መኮንን በዓለማችን አይገኝም፡፡ እንጂ አማራ ላይ የታወጀን የዕልቂት ዐዋጅ ለማስፈጸም ከሽሬና እንደርታ የተመመን የወያኔ መንጋ ወታደራዊ ሽፋን በመስጠትና አማራን እንዳይዋጋ በመከፋፈል፣ የጦር ሥልቱንም በማኮላሸት አማራንና ሀብት ንብረቱን ማውደም ከፍ ሲል እንደጠቆምኩት ማዕረግን ያስገፍፍ፣ ለከፍተኛ የዲስፕሊን ቅጣትም ይዳርግ ነበር እንጂ ለሹመት አያበቃም – ይህ አካሄድ በማዕረጎች ላይም በሚዘገንንና በሚመር ሁኔታ እንደመቀለድ ይቆጠራል፡፡ ማዕረጎች ባለቤት ቢኖራቸው ኖሮ ይሄኔ አቢይን ዘሄግ ላይ በገተረው ነበር፡፡ አቢይ አማራን አበሳጨሁ ብሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተተፋ እንደሆነ አልገባውም፤ የአእምሮ በሽተኛም ስለሆነ አይገባውም፤ ሀገሪቱን በደመነፍስ እያካለበ በአፍ ጢሟ ሊደፋት አንድ ሐሙስ ብቻ ቀርቶታል፡፡ እግዜር ይድረስላት እንጂ እንደርሱና እንደአጠቃላይ የኦሮሙማ አገዛዝ ቢሆን ኖሮ እስካሁንም በሕይወት የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ባልታዬ፡፡ ይህ ሁሉ በሀገርና በሕዝብ ላይ የሚቀለድ ቀልድ ትልቅ ዋጋ እንደሚያስከፍላቸው ቢያውቁ ኖሮ ደግሞ ከወዲሁና አሁኑኑ አደብ መግዛት ይጀምሩ ነበር፡፡ ነገር ግን የተጠናወታቸው ፀረ-አማራነት መጥፎ ጠባይ ሳያስቀብር አይተዋቸውምና በስህተት ላይ ስህተት እየደረቡ የመቃብራቸውን ጉድጓድ አርቀው በመቆፈር ላይ ይገኛሉ፡፡ አንድ የማኅበረሰብ አካል ከሌሎች ጋር በአንድነት ተፋቅሮና ተከባብሮ መኖር እየቻለ በየተራ መቀባበርን ከመረጠ መንገዱን ጨርቅ ያድርግለት በማለት በለስ እንዲቀናው ከመመኘት ውጪ ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ ዛሬ የቀበረ ነገ መቀበሩን ግን አይዘንጋ፡፡ አንዳንድ እልከኞች ደግሞ ጉድጓድ ሲቆፍሩ የደነደነ ጅልነት ይታይባቸዋል – ቀድሞ የሚገባበትን ባለማወቅ ጉድጓዱን በጣም ያርቁታል፡፡ እባካችሁ ለሰው ወጥመድ መዘርጋትን እንጠየፍ፡፡ ሰውም እንሁን፡፡

ዋናው መልእክቴ ይህ የማዕረግ ዕድገት በዓለም የሌለ በዓይነቱም የመጀመሪያም ምናልባትም የመጨረሻም ሊሆን የሚችል አስደናቂ ክስተት መሆኑን መጠቆም ነው፡፡ ሰዎቹ ማፈር አያውቁም እንጂ ሌላው ቀርቶ እነዚህ ፊልድ ማርሻልና ጄኔራል ተብዬ የኦሮሙማ ወታደራዊ ሰዎች ይህን ሹመት ከማግኘታቸው በፊት በሽሽት ወቅት ሲሮጡ ያላባቸው ጎርፍ መሰል ላብ መድረቅ ነበረበት፡፡ በሽሽቱ ጊዜ የፈሰሰው ላብ በቅጡ ሳይደርቅና ጦርነቱም ተፋፍሞ በቀጠለበት አሸናፊውም ገና ባልለየበት በአሁኑ ወቅት ይህን መሰል ሹመት መስጠት እንኳንስ ለእኛና ለሌላው ታዛቢም ግራ አጋቢ ነው – እንዲህ ያለ ማዕረግ መስጠት ቢቻልም እንኳን ማለቴ ነው፡፡ የማዕረግ ተሸላሚዎችም ወገብና ትከሻ እንዲሁም አእምሯዊ አቅም መፈተሸ ይኖርበት ነበር፡፡ አንዳንዶቹ እኮ በቀለም ትምህርትም ሆነ በማኅበራዊ ተሞክሯቸው ገና ምኑንም የማያውቁ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ወታደራዊ መኮንኖች ደግሞ – ምናልባትም ብዙዎቹ ወይንም ሁላቸውም ቢባል እምብዝም በማያሳፍር ሁኔታ – በቀለም ትምህርታቸው ልክ እንደአለቃቸው ብዙም የገፉ አይደሉምና ስማቸውን ሳይቀር በወጉ ለመጻፍ የሚቸገሩ ሳይሆኑ እንደማይቀሩ መገመት ለጎላ ስህተት የሚዳርግ አይደለም – (የግዥና የስጦታ ዲግሪዎችን ለጊዜው እንርሳቸው፤ ዋናው ዲግሪው የሚዘረዝረውን ክሂሎት ይዞ መገኘት ነውና)፡፡ ለነዚህ እንግዲህ ይህን መሰል – ፊልድ ማርሻልነትን ያህል ታላቅ ማዕረግ መስጠት ብዙ አስተያየት ሰጪዎች እንዳሉት ትከሻቸውን ማጉበጥ ነው፡፡ ስሙ ሲጠራ ሰምተውትም የማያውቁትን ማዕረግ ማሸከም በሀገርም በዜጎችም መቀለድ ነው፡፡ ፈረንጆቹ ራሳቸው ጥርሳቸውን ተነቅሰው እንዴት ከት ብለው እንደሚስቁብን ይታያችሁ፡፡ “ከርስ በርስ ጦርነት ለሸሹ ወታደራዊ መኮንኖች የማዕረግ ዕድገት ሰጡ” ተብሎ ሲወራ ያው እኛም የዚህችው አገር ዜጎች መሆናችን አልቀረምና ማፈራችን አይቀርም፡፡ በነገራችን ላይ ይህ የፊልድ ማርሻልነት ማዕረግ በከፈትኛ ዲስፕሊን መታነጽም እንደሚጠይቅ አንብቤያለሁ፤ ማዕረጉን ወስደው የተነጠቁ የመጥፎ ጠባይ ባለቤቶች እንደነበሩም ተረድቻለሁ፡፡ እናም ምድረ ማይም ደንቆሮ ዘረኛና ጎጠኛ ፊልድ ማርሻል እየተባለ ይህን ዕንቄ ማዕረግ አዛባ ላይ ጥሎ ማርፈጥፈጥ ትልቅ ወንጀል መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል፡፡ የማይባህ ማዕረግ በዘርህ አይድረስ፡፡ 

…. ይህን አቢይ የሚሉትን ሰውዬ ግን እግዜር ይይለት፡፡ በስንቱ ነው የሚያጨሰን! በስንቱ ነው አንጀታችንን የሚያሳርረው፣ አንገታችንንም የሚያስደፋው?! ፈጣሪን ምን ያህል ብንበድለውና ብናስከፋው ይሆን ይህን ምስለ-ዲያቢሎስ የሰጠን? አሃ፣ ለነገሩማ በሥነ ቃላችን “እግዜር ሲቆጣ ሽመል አይቆርጥም፤ ያደርጋል እንጂ ነገር እንዳይጥም” እንደምንለው ሁሉ መጽሐፉም “እግዚአብሔር አንድን ሕዝብ ሊቀጣ ሲፈልግ ጨካኝ ንጉሥን ያግሣል” ይላልና የሀገራችን ትንሣኤ ከአሁኑ በበለጠ ብዙ ዋጋ ሳያስከፍለን በዚሁ በቃችሁ ይለን ዘንድ አጥብቀን ወደርሱ እንጸልይ፡፡ ጌታ የለመኑት የማይነሳ፣ የነገሩትንም የማይረሳ ነውና ከልብ እንጩህበት፡፡ በቃ፡፡ 

ማን ነበረች እንዲህ ያለችው ግን …. 

አንድ እግር በርበሬ መንቀል አቅቷችሁ፤

አቃጥሎ ለብልቦ አንድዶ ይፍጃችሁ፡፡

Filed in: Amharic