>

በባሕላችን መርዶ እንኳ የሚነገርበት ሥነ ሥርዓትና የተመረጠ ሰዓት አለው! (ዳንኤል ሽበሽ)

በባሕላችን መርዶ እንኳ የሚነገርበት ሥነ ሥርዓትና የተመረጠ ሰዓት አለው!
ዳንኤል ሽበሽ

“በሐዘን ለጎበጠች እናት ትንቢት አትናገር! ወይም አይነገርምም” ይባላል። ለእኛ ለኢትዮጵያውያን በዚህን ወቅት ስለ ምህረትና ይቅርታ ለማስተማር፣ ስለ ጀግንነት ለማስታወስ መሞከር በቁስላችን ላይ እንደመቀለድ መሆኑ ይገባናል ። ምክንያቱም ሰሚ አታገኝም ።
… አይደለም የታሰሩት ይቅርና የተገደሉት እንኳ እንዲነሱ የእኛ እስትንፋስ ቢፈለግ ሰፊ ልብ ያለን ሚሊዮኖች ኢትዮጵያዊያን ነን ። አቦይ ስብሀት በእጃቸው ካተና ለምን ጠለቀ? ብለን የተበሳጨነው እንደት ይረሳል? ለምን ጽማቸውንና ጸጉራቸውን ተስተካክለው ፣ ሙሉ ሱፍ ልብስ ለብሰው ወደ ሕዝብ ፊት አልቀረቡም? የተማረከንና አቅም ቢስ ሰውን ማዋረድ ተገቢ ነው ወይ? ብለን የሞገትን ብዙዎች ነን ። ስብእና እና ክብርን መንካት ከአባቶቻችን ስላልወረስን ነው ያን ስንል የነበረው።
ነገር ግን ለሁሉም ወግ አለው። ለሁሉም #ወቅት አለው። ለሁሉም #ጊዜ አለው። ለሁሉም #ቦታ አለው ። “ተመካክረው የፈ*ት አይገማም” የሚባል ተረትም አለና እስቲ ተከተሉኝ ።
ክቡርነትዎ የጫጩቷን ከውስጥ ሰብራ መውጣቷን እንጂ ጫጩቷ ሰብራ እንዲትወጣ የውጪው ሙቀትና ግፊት ምን ያህል ጉልበት እንደነበረው በውል የተረዱ አይመስለኝም ።
“ያልተነካ ግልግል ያውቃል” እንዲሉ እንዲህ አይነት ውሳኔ የወሰኑ አካላት ሕመሙ በውስጣቸው ስለሌላቸው መሆኑ ግልጽ ነው ። ለምን ቢባል አብዘኛዎቹ ብልጽግናዊያን ምን ደረሶባቸው? ምናቸው ተነክቶባቸው? ከኬጂ እስከ ፒኤችዲ በዜሮ ወጭ ተምረው፣ መብራት፣ ውሃ፣ ትራንስፖርት ፣ የኑሮ ውድነት ወዘተ ሳይነካባቸው፣ የፖሊስ ጡጫ፣ የፌዴራል ፖሊስ ርግጫ ሳይደርስባቸው፣ ወፌ ላላን እንደ ሰበር እየሰሙ የመጡ … ናቸውና ታዲያ እንደት በተበዳይ ልክ ይታመማሉ?
… ይህ ዜጋኮ በደስታውም በሐዘኑም ደም እምባ ያለቀሰ ዜጋ፤ ትላንት “ዐቢይ፣ዐቢይ ሲባል ዐቢይ ፆም መስሎኝ…” ብሎ ቅኔ ለተቃኘ ፍቅር ለሆነ ሕዝብ፤ ለማ፣ለማ ብሎ ስንኝ የቋጠረ ሕዝብኮ ነው ። ሕዝብኮ ይህን ሁላ ዋጋ ሲከፍል የእናንተን ድሪቶ ደምና አጥንት ቆጥረው አይደለም። በእምባ፣ በሳቅ የተቀበለ ሕዝብኮ ነው ።  የመንግሥት ሚና መሆን የነበረበት በዳይንና ተበዳይን ማገናኘት እንጂ በማንአለብኝነት የወሰነው ውሳኔ ከብልጽግና አልፎ ሀገርን፣ ፍቅር ሰጥቶ በጀርባ የተወጋ ሕዝብን ዘቅዝቆ የሰቀለ መሆኑን መረዳቱ ለቀሪው ጉዟችን መልካም ይመስለኛል ።
በጣም የሚያስተዛዝበን ደግሞ ዋናውም ሆነ ሌሎች የየክልሎች ብልጽግናዎች ምንም ባላሉበት ሁኔታ የኦሮሚያ እና የአዲስ አበባ ብልጽግና በጉዳታችን እየተሳለቁ የድጋፍ መግለጫ መስጠታቸው ነው ። ባጠቃላይ በሰው ህመም ደግ መባል ነገ ለህመምህ የሚጮኸውን ያሳጣልና ከሕዝብ ጋር መታረቁ ፋይዳው ዘለግ ያለ ነው ። በጨፍላቂነትና በማንአለብኝነት ሐዲድ ተጉዞው በመቃብሩ ላይ የሚጻፍ «ወርቃማ ጥቅስ» ያፃፈ ማንም የለም!
በመጨረሻም ፦ ኢትዮጵያ የዐቢይም የአቦይ ስብሀትም ብቻ አይደለችም ። ወገን ሆይ «በሐዘናችን ላይ አናተኩር!» «ስብራታችንን በውስጣዊ ወገሻ እንጠግን» ፣ «ቁጣችን በልክ ይሁን!» እንደማመጥ፣ እንተባበር፣ እንረጋጋ! ሰከን ብለን አዋጭውን መንገድ በጥልቀት እናስብ!»
Filed in: Amharic