>

እውነት በነውር አይሸፈንም !! (ሐብታሙ አያሌው)

እውነት በነውር አይሸፈንም !!

ሐብታሙ አያሌው

ታላቁ እስክንድር  በእስር ቤት ሳለ የኢትዮጵያን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ  በተለያየ መንገድ እየተከታተለ በየዕለቱ በሚጎበኙት በኩል እራሱን updated እያደረገ  በማይመች ሁኔታ ውስጥ ሆኖ አቋሙን በየሳምንቱ በጽሑፍ እያቀረበ ሲያስደምመን የነበረ ነው።
ከእስር ቤት በወጣ ማግስት ልጄን ሚስቴን ሳይል፣ እረፍት ማድረግ  ሳያምረው  አፋር ሰመራ፣ ባህርዳር ፣ ጎንደር ዳባት… እየተንከራተተ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በአካል ጎብኝቶ ፣ አጽናንቶ የቻለውን ያህል ድጋፍ አድርጎ… ስለኢትዮጵያ ሲሉ የተሰውትን አክብሮ፣ የቆሰሉትን ጎብኝቶ  የሕዝብ ልጅ መሆኑን በተግባር አረጋግጧል ።
በእስር ቤት ሳለ “አንድ የትግራይ እናት ከምትራብ የህወሓት ጎተራ ቢሞላ እመርጣለሁ” ባለበት ከፍታው ከእስር ቤት ሲወጣም  የትግራይ ህዝብ ኢትዮጵያዊነት በማንም አልፎ ሂያጅ የሚነጠቅ አለመሆኑን በግልፅ ተናግሯል።
ህወሓት ለኢትዮጵያ  የክፍለ ዘመን ችግር መሆኑን አስምሮ ለውጥ ሳይሆን ተረኝነት የተጠናወተውን የአብይ አህመድ መንግሥትም አምርሮ ተችቷል።  የህወሓት ታካኪዎች ህወሓትን ለመታደግ የሚያደርጉትን መንደፋደፍ በቁርጥ አቋሙ ቀዝቃዛ ውሃ ስለቸለሰበት፤  በተለይም የትግራይ ህዝብና ህወሓትን  አንድ አምሳል አድርገው የፖለቲካ ጫወታ ለመጫወት እየሞከሩ ላሉት እራስ ምታት ሆኖ በመገለጡ  በድፍረት ለመወረፍ ሲንደፋደፉ ከርመዋል።
ታላቁ እስክንድር እንደ ሰው ጥቂት እረፍት አድርጎ ከቤተሰቡ ተገናኝቶ ከወዳጆቹ ጋር የሚመክርበት ጊዜ ቢኖረው እመኛለሁ።  ነገር ግን መረጃ  የሌለው ችኩል  በማስመሰል አቋሙን ለማጣጣል የሞከሩ በራሳቸው ይፈሩ እላለሁ።  በቂ መረጃ ይዞ በየሳምንቱ ሲገልፀው በነበረ አቋሙ ሲደመም ለነበረ  እውነቱ አይጠፋውም።  ያልተከታተለ ካለ ግን  ወደ ኢትዮ 360 ሚዲያ ዩቱዩብ ቻናል ጎራ ብሎ   ወይም የባልደራስን የፌስቡክ ገፅ ጎብኝቶ  መደመም ይችላል።  እውነትን መጋፋት ነውር ነው።
Filed in: Amharic