>

የዛሬው ማስተባበያ አቅራቢ ጄኔራል አበባ ታደሰ ነው ! ህዝቡ እየሳቀ መታዘብ ነው...!!! (ምኒልክ ምኒልክ)

የዛሬው ማስተባበያ አቅራቢ ጄኔራል አበባ ታደሰ ነው ! ህዝቡ እየሳቀ መታዘብ ነው…!!!
ምኒልክ ምኒልክ

መንግስት አከባቢ በአንድ ጉዳይ ዙሪያ ተደጋጋሚ መግለጫ፣ ቃለመጠይቅ፣ የካድሬ ጫጫታ የመሳሰሉት ሲሰማ የሆነ ሊደበቅ የተፈለገ አሊያም የሆነ ችግር አለ ማለት ነው።
ሰሞኑን ወታደራዊ ማዕረግ እና ሽልማትን በተመለከተ ከፊልድ ማርሻሉ ጀምሮ እስከ ፓርቲ ካድሬ ድረስ ሲነግሩን ከርመው ወደዚህ ሳምንት አሸጋግረውት ለጥምቀት እረፍት ወስደው ዛሬ ደግሞ ጄኔራል አበባው ዲዲዲዲዲ በብሄሩ አይደለም የሚል ፕሮፓጋንዳ ሰርቶ ወደ መንግስት ሚዲያ ሰፈር ተደባልቋል። ይህን ያህል በዚህ ጉዳይ ላይ መድከሙ ለምን አስፈለገ። መንግስት ካመነበት እኮ አንድ መልስ በቂ ነው። መግለጫ፣ ቃለመጠይቅ፣ የካድሬ ጫጫታ የመሳሰሉት ጋጋታ አያስፈልግም፤ የዚህ ሁሉ ጋጋት በጉዳዩ ላይ ችግር እንዳለ አመላካች ነው። ስለዚህ በማዕረግ አሰጣጡና በሽልማቱ ጉዳይ ላይ ችግር አለ ብሎ ያሰበውን አካል ከማሳመን ይልቅ ችግሩ እንዳለ የበለጠ ያመላክታል።
ሌላው በኦሮሚያና በቤንሻንጉል የሚደርሰው እልቂት ጉዳይ ነው። ዜጎች አማራ በመሆናቸው ብቻ በማንነታቸው እየተገደሉ ነው፤ ይህን በተመለከተ ገዳዮቹ እልቂት ሲፈጽሙ የመንግስት ሚዲያዎች በክልሎቹ ታጣቂዎቹ እንደተደመሰሱና እንደተማረኩ አድርገው ዘገባዎችን ይሰራሉ፤ ይህ ደግሞ በሕዝብ ላይ እልቂት ከፈጸሙት ታጣቂዎች ወንጀል ተነጥሎ አይታይም። የሃሰት ፕሮፓጋንዳ እንዳይሰራ እየታገልን ባለንበት በዚህ ወቅት ላይ በመንግስት ሚዲያዎች መጋዘን የከረሙ የድሮ መሳሪያዎችን እያወጡ ማረክን ገደልን የሚለው የመንግስት ፕሮፓጋንዳ ሊቆም ይገባል። መንግስት ነገን ትዝብት ላይ ሊጥሉ ከሚችሉት የሚዲያ ፍጆታዎች ራሱን ሊያገል ይገባል። ህዝብ ዝም ሲል አያውቅም ማለት እንዳልሆነ ልንገነዘብ ይገባል።   
 
“ሠራዊቱ የሚለካው በግዳጅ አፈፃፀሙ እንጂ በብሔሩ አይደለም”-ጀነራል አበባው ታደሰ
“የኢትዮጵያ ሠራዊት የሚለካው በስራው ስኬት እና በግዳጅ አፈፃፀሙ እንጂ በብሔሩ አይደለም” ሲሉ የመከላከያ ሠራዊት ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል አበባው ታደሰ ገለጹ።
ከዚህ በፊት በነበረው የብሔር ተኮር የሠራዊት ግንባታ ዋጋ የከፈለው ራሱ ሠራዊቱ ነው ያሉት ጀነራል አበባው ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያዊነትን የተላበሰ እና በሞያው ብቁ የሆነ ሠራዊት እየተገነባ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በቅርቡ የተካሄደው ወታደራዊ የማዕረግ እና የሜዳልያ ሽልማት በግዳጅ አፈፃፀም ላይ የተመሰረተ፣ በየደረጃው ላሉ እዞች ማዕረግ የተሰጠበት፣ የሠራዊቱ አመራሮችን የሚመጥን እና የሠራዊቱን ሞራል የገነባ እንደነበር ገልፀዋል።
በመጀመሪያው ምዕራፍ ከአሸባሪው ህወሓት ጋር የተፋለመው የኢትዮጵያ ሠራዊት፤ ከጠላት የሰው ኃይል ቁጥር እና ትጥቅ ያነሰ ነገር ግን ኢትዮጵያዊነትን ስንቁ ያደረገ እንደነበርም ተናግረዋል።
ከአሸባሪው ህወሓት ጋር እየተደረገ ያለው ጦርነት አልተጠናቀቀም ያሉት ጀነራል አበባው ሠራዊቱ የምዕራፍ አንዱን ጦርነት አጠናቅቆ ለቀጣይ ግዳጅ እየተዘጋጀ መሆኑን ገልፀዋል። አሸባሪው የህወሓት ቡድን አሁንም ትንኮሳውን እንዳላቋረጠም ነው ጀነራሉ የተናገሩት።
አሸባሪው ህወሓት ተቆጣጥሯቸው ከነበሩ አካባቢዎች በማስወጣት የተገኘው ድል ሕዝባዊ ድል ነው ያሉት ጀነራሉ የጠላትን የማድረግ አቅም ያዳከመ እና ከፍተኛ የሰው ኃይል እና የንብረት ኪሳራ ያደረሰ መሆኑንም ገልፀዋል።
በጋሸና፣ ሚሌ እና በመሐል ግንባሮች ፈታኝ ውጊያዎች ተደርጎ እንደነበር የገለፁት ጀነራሉ ሠራዊቱ ከፍተኛ ጀብዱ የሠራባቸው እንደነበሩም ተናግረዋል። ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሩ የወሰደው ቁርጠኝነት የሠራዊቱን ዝግጁነት አቅም ያሳደገ መሆኑንም ኢዜአ ዘግቧል።
Filed in: Amharic