በመጪው ጊዜያት ይደረጋል ለተባለው ብሔራዊ ምክክር ለሚቋቋመው ኮሚሽን የኮሚሽነሮች ምርጫ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመመልመሉን ሂደት የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ተቃወመ፡፡ ኦፌኮ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት እና ለህ/ተ/ም/ቤት በጻፈው ደብዳቤ፤ በብዙ ወገኞች ዘንድ ተቀባይነቱ ጥያቄ ውስጥ መግባት የሌለበት ያለው የምክክሩ አመቻች ኮሚሽነሮች ምርጫ የገዢው ፓርቲ አብዛኛ ድምጽ በሚሰማበት ምክር ቤት ከሚሆን አማራጭ ማስተካከያ ይደረግበት ብሏል፡፡ በደብዳቤው የሚመረጡት ኮሚሽነሮች ገለልተኝነት በዓለማቀፉ ማህበረሰብ ጭምር ተዓሚ እንዲሆኑም ተጠይቋል፡፡
አገራዊ ውይይቱ ከሰላማዊ ተቃዋሚዎች በተጨማሪ ሥርአቱ ላይ አኩርፈው ብረት ያነሱትን ኃይሎችም ካላካተት የሚፈለገውን ውጤት ያመጣል ብሎ እምነት ልጥልበት እንደማይችልም ፓርቲው አመልክቷል፡፡ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ለኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት እና ለኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፌ ጉባኤ ጽ/ቤት የጻፈው ደብዳቤው አራት ነጥቦች ላይ ያተኮሬ ነው፡፡ ፓርቲው ብሔራዊ የመግባባት ውይይቱ ሂደት ላይ ማስተካከያ እንዲደረግ የጠየቀበትና ዶይቼ ቬለን ጨምሮ ለመገናኛ ብዙሃን የላከው ጽሁፍ አብይ ማጠንጠኛው በቀጣይ የተወጠነው ብሔራዊ ምክክር ፍጹም ገለልተኛ በሆነ አካል እንዲመራ ነው የሚጠይቀው፡፡ ዶይቼ ቬለ ስለ የማስተካከያ ጥያቄው ደብዳቤ የፓርቲው ም/ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹን ተጨማሪ ማብራሪያ ጠይቋል፡፡
አቶ ሙላቱ ገመቹን ገለልተኛ ያሉት አወያይ እንዲመረጥ ፓርቲያቸው የሚያቀርበውንም ምክረ ሀሳብ ጠየቅናቸው፡፡ ኦፌኮ በደብዳቤው ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ መሰል የውይይት መድረኮች የይዘጋጅ ጥያቄዎችን ማቅረቡን አስታውሶ፤ አሁንም የምክክር መድረኩ አካታችነትና የመሪዎቹ ገለልተኝነት ላይ ጥርጣሬ መግባት እንደሌለበት በጻፈው ደብዳቤ ጠይቋል፡፡
መንግስትም ሆነ ገዢው ፓርቲ በሚደረገው ብሔራዊ ምክክር እንደ አንድ ተሳታፊ እንጂ እንደ አመቻች አሊያም አወያይ እራሱን እንደማያቀርብ እና ለሚቋቋሞው ኮሚሽን ገለልተኝነት ቁርጠኛ መሆኑን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ከዶይቼ ቬለ ጋር ቆይታ ያደረጉት የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ተናግረው ነበር፡፡ ኦፌኮ በዛሬው መግለጫ መንግስት መሰናክሎችን በማስወገድ ለብሔራዊ ምክክሩ ባለድርሻ አካላትን እንዲያነቃቃ፣ የመንግስት ሚዲያዎች እና ባለስልጣናት ውይይቱን ማበረታታት ላይ እንዲያተኮሩ እና በፖለቲካ አቋም ልነት የታሰሩ ያሏቸው እንዲፈቱም ጠይቋል፡፡