በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከእናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ
ጥር ፲፪ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም እንደ ሃይማኖታቸው የአምልኮ እና ቀኖና ሥርዓት ታቦተ ሕጉን ወደ መንበረ ክብሩ ለመመለስ በማኅደረ መለኮት ወይብላ ማርያም ቤተክርስቲያን በታደሙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች ላይ በጸጥታ ኃይሉ የተፈጸመው ግድያ ኢ ሕጋዊ፣ ኢ ሃይማኖታዊና የሞራል አልባነት ድርጊት ነው። ጥንቱንም ላለፉት ዓመታት የመስቀልና የጥምቀት በዓላት በሚከበሩበት ጊዜ “ጠብ ያለሽ በዳቦ” ምክንያት እየፈለጉ ወከባ መፍጠር፣ ማሰር፣ መደብደብ ሕጋዊነት እስኪመስል ድረስ በተደጋጋሚ ሲፈጸም የቆየ ተግባር ቢሆንም በወይብላ ማርያም ያለፈውን ዓመት ጨምሮ መሰል ድርጊቶች በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የጸጥታ አካላት እየተፈጸመ ነው።
በክልሉ የተጠና በሚመስል መልኩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት አብያተ ክርስቲያንን ማቃጠል፣ ካህናትን እና ምዕመናኑን መግደል፣ ማፈናቀል፣ ማሳደድ፣ ማሰር፣ ሀብት እና ንብረታቸውን መዝረፍ እና ማውደም ያለማቋረጥ የቀጠለ ሲሆን አንድም ቀን የክልሉ መንግስት ስለጉዳዩ የተጨበጠና ተአማኒነት ያለው ማብራሪያ ሲሰጥም ሆነ ይቅርታ ሲጠይቅ አይታይም፤ በአሁኑም የተፈጸመው ግድያ፣ ድብደባ፣ ወከባና እስራት ባለፉት ጊዜያት በተለያዩ አካባቢዎች በክልሉ በአትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ላይ ሲፈጸሙ የነበሩት ሕገወጥ ተግባራት አንዱ አካል ተደርጎ የሚወሰድ ነው። አሁንም በሃይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ በጸጥታ ኃይሉ የተፈጸመው ግድያ በዓሉ በሰላም እንዳይጠናቀቅ ከመፈለግ የመነጨ፣ የጭር ሲል አልወድም መንፈስና ጫፍ የወጣ የአክራሪነት መገለጫ ነው።
ሃይማኖት ለእኛ ለኢትዮጵያውያን እስትንፋሳችን መሆኑ እየታወቀ በየጊዜው ጸብ እየጫሩ ፓለቲካዊ ጉዳዮቻቸውን ሃይማኖታዊ ቀርጽ እንዲኖረው ለማስያዝ እየተሔደ ያለበት ርቀት በጊዜ ካልታረመ መዘዙ ከባድ ውጤቱም የከፋ መሆኑ የማይቀር ጉዳይ ነው።
ፓርቲያችን እስከአሁን በደረሰው መረጃ ሕይወታቸው ያለፈ ምእመናን ያሉ ሲሆን በርካቶችም ከቀላል እስከ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። ስለሆነም:-
፩. ይህ ድርጊት በተደጋጋሚ እየተፈጸመ የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ ብሎ እንዳልሰማ የሆነውና ድርጊቱን ማስቆም ያልቻለው ኦሮምያ ክልል መንግስት ሰለጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጥ ሕዝብንም በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቅ፤
፪. ድርጊቱን ባነሳሱ እና በፈጸሙ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ፣ የሕግ ውሳኔውም ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግ፤
፫. ለተጎጂ ቤተሰቦች እና ለሃይማኖቱ ተከታዮች የሞራል ካሳ እንዲከፈል፤
፬. ያለአግባብ የታሰሩ ምዕመናንም በአስቸኳይ እንዲፈቱ ፓርቲያችን በአጽንዖት ያሳስባል።
በመጨረሻም ለሟች ቤተሰቦችና ለመላው የኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች መጽናናትን እንመኛለን።
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ።
እናት ፓርቲ
ጥር ፲፫ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ