>

"ለትግራይ ህዝብ እርዳታ ጭነው ሲጓዙ የነበሩ በርካታ ተሽከርካሪዎች ወደኃላ ተመለሱ...!!!" (DW)

“ለትግራይ ህዝብ እርዳታ ጭነው ሲጓዙ የነበሩ በርካታ ተሽከርካሪዎች ወደኃላ ተመለሱ…!!!”
DW

 

• ” ወደታች ከባድ መሳሪያ እየጣሉ ነው። እንኳን የእርዳታ መኪኖች እና እዛ ያሉ የሚሸሹ ማህበረሰብ አባላት በትራንስፖርት እንዳይሸሹ አድርጓቸዋል ፤ … የፌዴራል መንግስት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ” – 
አቶ አብዶ አሊ
 
• ” የኢትዮጵያ ጦር ከዚህ ቀደም በተወሰነው ውሳኔ ባለበት ፀንቶ ነው የሚገኘው። በአካባቢው ላይ ምንም አይነት የመከላከያ ሰራዊት እንቅስቃሴ በሌለበት ነው የሽብር ቡድኑ ትንኮሳ እየፈፀመ ያለው ” – 
ወ/ሮ ሰላማዊት ካሳ
 
• ” … ለህዝባችን ሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ እንፈልጋለን ለጥቃቅን ጀብዱ ፍላጎት የለንም። ዓለምአቀፉ ማህበረሰብም ትኩረት ነፍጎናል ” – አቶ ጌታቸው ረዳ
 
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (UN) የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ፅህፈት ቤት ህወሃት በአፋር በኩል እየፈፀመ ባለው ጥቃት ለትግራይ ህዝብ የሰብዓዊ እርዳታ ጭነው ወደ ትግራይ ክልል፣ መቐለ በመጓዝ ላይ የነበሩ የዓለም ምግብ ፕሮግራም (WFP) ተሽከርካሪዎች ከግማሽ መንገድ በኋላ ወደኋላ ለመመለስ መገደዳቸውን አሳውቋል።
በተከፈተው ጥቃትም በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን ሰዎች መፈናቀላቸውን አመልክቷል።
የህወሃት መሪዎች ድርጊት ለአደገኛ የፖለቲካ ቁማር ሲሉ ሰላማዊ ህዝብን ለረሃብ እየዳረጉ መሆኑን የሚያሳይ ሁነኛ ማስረጃ ነውም ብሏል
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (UN) የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ፅህፈት ቤት።
የህወሓት ቡድን የተለያዩ መሰረታዊ የእርዳታ ቁሳቁሶችን የጫኑ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ ዘልቀው እንዳይገቡ አፋር ክልል አብአላ ውስጥ ታግደው ተይዘዋል ብሏል።
ህወሓት ከሰመራ ታጅበው ወደ ትግራይ ሊገቡ ነበር የተባሉት 27 የጭነት ተሽከርካሪዎች ወደ መቐለ እንዳይገቡ ተደርገዋል የሚል ክስ አሰምቷል።
በጉዳዩ ዙሪያ የኢትዮጵያ መንግስት ምላሽ የሰጠ ሲሆን ህወሓት የመከላከያ ሰራዊት እንቅስቃሴ በሌለበት በአፋር ክልል አብአላ ላይ በከፍተው ጥቃት ለትግራይ ህዝብ እርዳታ ጭነው ወደ ትግራይ ሊገቡ የነበሩ ተሽከርካሪዎች ወደኃላ ለመመለስ ተገደዋል ብሏል።
የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሰላማዊት ካሳ ለቪኦኤ በሰጡት ቃል ፥ ” ይሄ አካባቢ በዋናነት ወደ ትግራይ የእርዳታ ማስገቢያ መንገድ ነው። ይህንን አካባቢ ሆን ብሎ በማጥቃት አሁንም የትግራይን ህዝብ ለረሃብ ለማጥቃት እየሞከረ መሆኑን ነው የሽብር ቡድኑ ድርጊት የሚያሳየው። በዚህ ጥቃት በዓለም ምግብ ፕሮግራም በኩል ወደ ትግራይ ሊገቡ የነበሩ በርካታ የጭነት ተሽከርካሪዎች ህወሓት በከፈተው ጥቃት እንዲመለሱ ተገደዋል ” ብለዋል።
ህወሓት አብአላ ላይ በከፈተው ጥቃት 50 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን ነገር ግን ቁጥር ለማጣራት ጥረት እየተደረገ መሆኑ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልፀዋል።
” የኢትዮጵያ ጦር ከዚህ ቀደም በተወሰነው ውሳኔ ባለበት ፀንቶ ነው የሚገኘው። በአካባቢው ላይ ምንም አይነት የመከላከያ ሰራዊት እንቅስቃሴ የለም ” ያሉት ወ/ሮ ሰላማዊት ” ነገር ግን ጦሩ በሌለበት በሽብር ቡድኑ ምክንያት የተለያዩ ትንኮሳዎች እየተፈፀሙ ነው ፤ ይህን የሚያደርገው እና ጥቃት የሚፈፅመው ወደ ትግራይ የሚገባውን እርዳታ ለማስተጓጎል ነው ” ብለዋል።
ለሬድዮ ጣቢያው ቃላቸው ከሠጡ የአፋር ክልል ነዋሪዎች መካከል አንደኛው ህወሓት በአብአላ ከተማ ላይ ብቻ በ6 ግንባር ጦርነት መክፈቱን ፣ በበርሀሌ በኩል አሰዳ ላይ ጦርነት መክፈታቸውን ፣ከአብአላ ወደዚህ መጋሌላይም ጦርነት መክፈታቸውን አስረድተዋል።
እየተደረገ ያለው ከባድ ጦርነት ነው ያሉት ነዋሪው ከባድ መሳሪያ ስለታጠቁ ህዝብ በሚበዛበት አካባቢ እየተኮሱ ይገኛሉ ብለዋል። ” ህፃናት ፣ ሴቶች … በርካቶች ተፈናቅለዋል። አቅም የሌላቸው እዛው እያለቁ ነው ” ሲሉ ገልፀዋል።
ነዋሪው በጦርነቱ ምክንያት የህወሓት ታጣቂዎች አብአላን ገብተው ሙሉ በሙሉ መያዛቸውን ፣ መጋሌ 3 ቀበሌ መያዛቸውን መረጃ እንዳላቸው ለሬድዮ ጣቢያው ተናግረዋል።
የአፋር ክልል አደአር መንግስት ኮሚኒኬሽን ኃላፊ አቶ አብዶ አሊ ፥ ህወሓት ከአማራ እና አፋር አካባቢዎች በጦርነት እንዲወጣ ከተደረገ በኃላ አብአላ እና አካባቢው ላይ የከባድ መሳሪያ ጥቃት መሰንዘር ከጀመረ ወር እንዳለፈው ገልፀዋል።
” የአካባቢው ጥበቃ ሚሊሻዎች፣ የወረዳ ፖሊሶች ላይ ነው ጦርነት እያካሄደ ያለው ” ያሉት አቶ አብዶ ” በአካባቢው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የለም ” ብለዋል።
በመድፍ እና በከባድ መሳሪያ ጥቃት እየፈፀመ ያለው ሲቪል ሰዎች ላይ ነው ሲሉ አክለዋል። ይህን የሚያደርገው ባጋጠመው ሽንፈት ለመበቀል እና ብቸኛድን የእርዳታ ማስተላለፊያ መንገድ ለመዝጋት ነው ብለዋል።
የህወሓት ታጣቂዎች ዘልቀው ስለገቡባቸው ቦታዎች በተመለከ አቶ አብዶ አሊ ፥ ትግራይ በሚያዋስኑ 5 ወረዳዎች በሙሉ ጦርነት ከፍተው እንደሚገኙና ጦርነቱ መቀጠሉን ገልፀው ፤ አብአላን በከፊል መቆጣጠራቸውን መረጃ እንዳላቸው ገልፀዋል።
ቡድኑ ከዚህ ቀደም ከነበረው ጦርነት በተለየ መልኩ በተለያየ ግንባር የነበረ ኃይሉን በሙሉ እና ለዚህ ጦርነት ሲያሰለጥናቸው የነበሩ ወታደሮቹን ከባድ መሳሪያዎቹን አሰልፎ በሁለተኛ ምዕራፍ ነው ጦርነት የከፈተው ብለዋል።
የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ ፥ የአብአላው ጦርነት በአፋር ታጣቂዎች እና በኤርትራውያን አጋሮቻቸው ነው የተቀሰቀሰው ብለዋል። ” እንደተነገረን ከሆነ ከሰመራ ታጅበው ወደ ትግራይ ሊገቡ የነበሩ 27 መኪናዎች ወደ ትግራይ መግባት ነበረባቸው ሆኖም እንደማስተባበያ የቀረበው የአፋር ክልል መንግስት በአካባቢው ጦርነት በመኖሩ ከለከለ የሚል ነው። ይህ መንግሥት ሳያውቀው ይፈፀማል የሚል እምነት የለኝም፤ ለህዝባችን ሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ እንፈልጋለን ለጥቃቅን ጀብዱ ፍላጎት የለንም። ዓለምአቀፉ ማህበረሰብም ትኩረት ነፍጎናል ” ብለዋል።
የአደአር ወረዳ የኮሚኒኬሽን ኃላፊ አቶ አብዶ አሊ አቶ ጌታቸው የሰነዘሩትን አስተየት አጣጥለውታል።
ቡድኑ ከሁሉም ግንባሮች ሸሽቶ ወደ መቐለ ከከተተ በኃላ እንዳለ ወደ አብአላ እና አፋር ግንባር ነው ጦሩን ያዞረው የመጀመሪያውን ጥቃትም የከፈተው የእርዳታ ማስተላለፊያ በሆነው መንገድ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
” እስካሁን ድረስም ከተማውን በከባድ መሳሪያ እየደበደበ ነው ያለው። አብአላ ዝቅታ ቦታ ላይ ነው ያለችው እነሱ ከፍታ ቦታ ላይ ነው ያሉት ከከፍታው ነው ወደታች ከባድ መሳሪያ እየጣሉ ያሉት። እንኳን የእርዳታ መኪኖች እና እዛ ያለው የሚሸሹ ማህበረሰብ አባላት በትራንስፖርት እንዳይሸሹ አድርጓቸዋል። በእግራቸው ነው እየሸሹ ያሉት ” ብለዋል።
ጉዳዩን በአፋር ክልል ብቻ የሚቀረፍ ባለመሆኑ የፌዴራል መንግስት ትኩረት እንዲሰጠው መልዕክት ተላልፏል።
Filed in: Amharic