>

ኦብነግ በኢትዮጵያ ሊካሄድ በታቀደው ብሔራዊ ውይይት ላይ ለመሳተፍ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀመጠ (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

ኦብነግ በኢትዮጵያ ሊካሄድ በታቀደው ብሔራዊ ውይይት ላይ ለመሳተፍ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀመጠ
ኢትዮጵያ ኢንሳይደር

የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) በኢትዮጵያ በሚካሄደው አገራዊ ምክክር ለመሳተፍ መሟላት አለባቸው ያላቸውን ስድስት ቅድመ ሁኔታዎች አስቀመጠ። ኦብነግ በብሔራዊ ምርጫ ላይ ታይቷል ያለውን አይነት “ጉድለት” በአገራዊ ምክክር ላይ እንዳይደገምም አሳስቧል።
ኦብነግ ቅደመ ሁኔታዎቹን ያስቀመጠው የግንባሩ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከሰኞ ጥር 9 እስከ ሐሙስ ጥር 12፤ 2014 በጅግጅጋ ከተማ ሲካሄደው የቆየውን ስብሰባ ሲያጠናቅቅ ባወጣው መግለጫ ነው። የግንባሩ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በዚሁ ስብሰባው በሶማሌ ክልል፣ በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ቀንድ ያሉ ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ መወያየቱ ተገልጿል።
ከስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የውይይት አጀንዳዎች መካከል፤ በኢትዮጵያ ሊካሄድ የታቀደውን አገራዊ ምክክር የሚመለከተው አንዱ እንደነበር ኦብነግ በትላንትው ዕለት በትዊተር ገጹ ባሰራጨው መግለጫ አመልክቷል። ኦብነግ “ተዓማኒ ብሔራዊ ውይይት ከተካሄደ የሶማሌ ክልል ህዝብ የጋራ አተያይ እና አጀንዳ ማዘጋጀት ይገባዋል” የሚል አቋሙን በትላንትናው መግለጫው ቢያንጸባርቅም፤ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን የምስረታ ሂደት ላይ ግን የሰላ ተችቱን ሰንዝሯል።
“የኮሚሽኑን 11 አባላት ለመምረጥ የተጀመረው ሂደት እና ሂደቱን ለመምራት የቀረበው የአዋጅ ረቂቅ፤ ጎዶሎ እና ለአንድ ወገን ያደላ ነው” ሲል ተችቷል። ይህ አካሄድም ምክክሩ ከወዲሁ እምነት እንዲታጣበት አድርጓል የሚል አቋሙን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ገልጿል።
ዝርዝር ዘገባውን ለማንበብ ይህን ሊንክ ይጫኑ፦ https://ethiopiainsider.com/2022/5674/
Filed in: Amharic