>

በአፋር ላይ የተከፈተውን ዳግም ወረራ አስመልክቶ ከአማራ ሕዝባዊ ኃይል-ፋኖ (APF) የተሰጠ መግለጫ

በአፋር ላይ የተከፈተውን ዳግም ወረራ አስመልክቶ ከአማራ ሕዝባዊ ኃይል-ፋኖ (APF) የተሰጠ መግለጫ

ህወሃት ከአራት ኪሎ ከተባረረበት ማግስት ጀምሮ ያደርግ የነበረውን የጦርነት ድግስ በቸልታ የተመለከተው የኢትዮጵያ አገዛዝ ወራሪው ኃይል የሀገራችን ትልቁ የመከላከያ ዕዝ ላይ ዘግናኝ ጥቃት እንዲፈፅም እና በመንግስት ትጥቅ ራሱን እንዲያደራጅ ትልቅ እድል ከመፍጠሩ በተጨማሪ በሀገር እና በህዝብ ላይ ትልቅ ውድመት እንዲደርስ ምክንያት ሆኗል።
ከዚህ ክስተት በቂ ትምህርት ወስደው ጦርነቱን በአግባቡ መምራት የሚገባቸው የፌደራል እና የክልል መንግስታት በቂ የመከላከያ ቀጠና (Buffer Zone) ሳይቆጣጠሩ እና ሳያዘጋጁ ትግራይን ለቀው በመውጣታቸው ህወሃት በአፋር እና አማራ ክልል ላይ አሰቃቂ ጥቃት እና ውድመት እንዲፈፅም አስችሎታል።
ፋኖን ጨምሮ በሁሉም የፌደራል እና የክልል የፀጥታ ኃይሎች ርብርብ በከፍተኛ መስዋዕትነት በመሸነፍ ላይ የነበረውን ወራሪ ኃይል ሁሉንም የአማራ ግዛቶች ለቆ ባልወጣበት ሁኔታ “…ትግራይ አንገባም…”፣ “…መከላከያ ባለበት ፀንቶ ይቆማል…” የሚል ውሳኔ ከመሰጠቱ ጎን ለጎን በሀገር ደረጃ እየተካሄደ ያለው የ”ድል” መልስ ድግስ እና ፌሽታ ህዝባችንን ለሌላ ዙር ሰቆቃ እያመቻቸው ይገኛል።
በገዥው ኃይል በኩል ህወሃት እያደረገ ያለውን የጦርነት እና ወረራ ዝግጅት የሚመጥን ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ  ስራ ካለመከናወኑም በተጨማሪ ህወሃት በመዳከም ላይ የነበረውን ኃይሉን አሰባስቦ እና አጠናክሮ የአፋር ህዝብ ላይ 2ኛ ዙር ወረራ በመፈፀም ከፍተኛ ውድመት እያደረሰ ይገኛል።
ለሚመራው ህዝብ ኃላፊነት የማይሰማው መሆኑን ከላይ በጠቀስናቸው ታሪካዊ ሁነቶች ያረጋገጠው የወቅቱ የኢትዮጵያ አገዛዝ የአፋር ህዝብ ላይ የተከፈተውን ጥቃትም እስካሁን ድረስ በቸልታ እየተመለከተው መሆኑን ለጥቃቱ በቂ ምላሽ ባለመስጠት አረጋግጧል።
በመሆኑም መላው ኢትዮጵያዉያን በተለይም የአማራ ህዝብ ከአፋር ህዝብ ጎን በመቆም የአፋር ህዝብ በህወሃት የተከፈተበትን ጥቃት እና የተጋረጠበትን የህልዉና አደጋ የመከላከል ታሪካዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪያችንን እያስተላለፍን የአማራ ሕዝባዊ ኃይል (ፋኖ) በማናቸውም መንገድ ከአፋር ህዝባዊ ሰራዊት ወንድሞቻችን ጎን በመቆም የህልውና ተጋድሏችሁን ለመቀላቀል ዝግጁ መሆናችንን እናረጋግጣለን።
አዲስ ትውልድ! አዲስ አስተሳሰብ! አዲስ ተስፋ!
 ጥር 18 ቀን 2014 ዓ.ም
ባሕር ዳር- ኢትዮጵያ
Filed in: Amharic