>
5:21 pm - Sunday July 21, 2999

ቅድስት ኢትዮጵያ ስትድን ብቻ ሁሉህም ትድናለህ - አለዚያ ከቆራጣ ሀሳብህ ጋር ሁሉህም ጠፊ ነህ....!!! (ሸንቁጥ አየለ)

ቅድስት ኢትዮጵያ ስትድን ብቻ ሁሉህም ትድናለህ – አለዚያ ከቆራጣ ሀሳብህ ጋር ሁሉህም ጠፊ ነህ….!!!
——-
ሸንቁጥ አየለ

–ሀገር በቁርጥራጭ ሃሳብ አይመራም::ህዝብም በቆራጣ ሀሳብ አይድንም::የትኛዉም ነገድም በቆራጣ ሀሳብ አሸናፊ አይሆንም::ብታሸንፍ እንኳን ቆራጣ ሀሳብ ላይ ቆመህ ከሆነ የድል ጉዞህ ቆራጣ ነዉ::
-የትግራይ አክራሪ ፖለቲከኞች በኢትዮጵያዊነት ጥላቻ ናዉዘዉ:የአማራ ህዝብ ካልጠፋልን ብለዉ:የተዋህዶ እምነት አከርካሪዉ ካልተሰበረልን ብለዉ የትግራይን ወጣት 17 አመታት ወደ እሳት ማግደዉ አሸነፉ::ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን 27 አመታት መሯት:: ግን ሃያ ሰባት አመታት ሙሉ የቆሙትም የተመሩትም የሚያስቡትም በቆራጣ ሀሳባቸዉ ላይ ቆመዉ ነበር::እናም መጨረሻ ሆዳቸዉን ቁንጣን እስኪይዘዉ በልተዉ እና በስካር ናላቸዉ ዞሮ ኢትዮጵያን ለመከራ ዳርገዋት እንወደዋለን የሚሉትንም የትግራይን ህዝብ ለመከራ ዳርገዉት ክስልጣናቸዉ ተባረሩ::ሆኖም አሁንም የሚዋጉት እና እንታገላለን የሚሉት እዚያዉ ቆራጣ ሀሳባቸዉ ላይ ቆመዉ ነዉ::አሁንም ከበሯቸዉን የሚደልቁት የአማራ ህዝብ እና የትግራይ ህዝብ ተላት ነዉ::ትግሬ የሚያተርፈዉ አማራ ሲጠፋ ነዉ እያሉ ነዉ::መረገም ብቻ ሳይሆን በመርገምት ዉስጥ የመርገምት ካንሰር ላይ እየተንከባለሉ እንደመቀጠል ነዉ::
–የኦሮሞ አክራሪ ፖለቲከኞች ከትግራይ አክራሪ ፖለቲከኞች የባሰ ቆራጣ ሀሳብ ላይ ቆመዉ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዉያንን ማተራመሱን ይዘዉታል::ከትግራይ አክራሪ ፖለቲከኞች ስህተት የተማሩት አንዳች ነገር የለም::ቆራጣ ሀሳብ ላይ ቆመዉ ኢትዮጵያን ሆነ የኦሮሞን ህዝብ ለታላቅ መከራ እያዘጋጁት ነዉ::ዛሬ እነሱ የአማራን ነገድን:የተዋህዶ እምነትን እና ልዩ ልዩ አነስተኛ ነገዶችን ከኦሮሚያ ቀፍቅፈዉ እያጠፉ በጎን ደግሞ ኦሮሚያ የሚሉትን የነሱ የልቦለድ ሀገርን ማበልጸግ ላይ አተኩረዋል;::አማራ እና ቀሪዉ ኢትዮጵያዊ ነገድ ረፍት ሳያገኝ እነሱ ረፍት አግኝተዉ ሊኖሩ መሆኑ ነዉ::የቅዠት ህልም ነዉ::ይሄም መረገም ብቻ ሳይሆን በመርገምት ዉስጥ የመርገምት ካንሰር ላይ እየተንከባለሉ እንደመቀጠል ነዉ::
-አሁን ወደ አማራ ብሄረተኛ ፖለቲከኞች እንመለስ እና እንፈትሻቸዉ::ለምሆኑ ከኦሮሞ አክራሪ ፖለቲከኞች እና ከትግሬ አክራሪ ፖለቲከኞች ምን ተማሩ? የተማሩት ነገር ቆራጣዉን ሀሳብ ነዉ ወይስ የቆራጣዉን ሀሳብ ስህተት ላለመድገመ የተሻለ ሀሳብ ተምረዋል? እዉነቱን ለመነጋገር አብዛኞቹ የአማራ ብሄረተኞች ከሁለቱ አክራሪ ብሄረተኞች የተማሩት ነገር ቆራጣዉን ሀሳብ ነዉ::የተረገመዉን ሀሳብ ነዉ::አብዛኞቹ የአማራ ብሄረተኞች እራሳቸዉን በአማራ ክልል ላይ ብቻ ወስነዉ መላዉ ኢትዮጵያን ግን የመዘንጋት በሽታ ዉስጥ ተዘፍቀዋል::ከ51% የሚሆነዉ አማራ ከአማራ ክልል ዉጭ ቢኖርም ስለዚህ ህዝብ አያገባንም ብለዉ ይሄን የራሳቸዉን ወገን አደራጅተዉ ለማታገል እንቢ ብለዋል::ከብአዴን እስከ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲሁም ዳርዳሩን እስክስታ እስከሚመቱት አቀንቃኞች ስለ ኢትዮጵያ ያላቸዉ ግንዛቤ ቆራጣ እና መርገምታዊ ሲሆን ስለ ራሳቸዉ ነገድ ስለ አማራ ህዝብም ያላቸዉ ሀሳብ ቆራጣ ነዉ::ኢትዮጵያን በመላዉ ለማዳን ዳተኝነት ብቻ ሳይሆን ምን አገባኝ ይታይባቸዋል::አንዳንዶቹም ኢትዮጵያን እስከ መራገም የሚራመዱም ተነስተዋል::መርገምት የሚጀምረዉ ከአንደበትህ ከምታወጣዉ መርገምታዊ ቃል ነዉ::
-ከትግሬ ነገድ:ከአማራ ነገድ እና ከኦሮሞ ነገድ ዉጭ ያሉ የዬ ነገዱ ፖለቲከኞችም ታላቁ በሽታቸዉ በነገዳቸዉ ሀሳብ ብቻ ላይ የቆመ ቆራጣ ሀሳብ ላይ ቆመዉ ስለ ሀገራቸዉ ኢትዮጵያ አያገባንም ማለታቸዉ ነዉ::ደካማ እና ሽባ ብቻ ሳይሆኑ ጨርሶም አያገባንም ብለዉ በነገዳቸዉ ቆዳ የሀሳብ አድማሳቸዉን ጠቅልለዉ የተኙ ምናምንቴ ፖለቲከኞች እና ልሂቃን ሆነዋል::
-የኢትዮጵያን አንድነት እናራምዳለን የምትሉ አጭበርባሪዎች እና ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት እንደተፈጠረች አድርጋችሁ በትንታኔ ሰነዳችሁ በማቅረብ እና በማሰብ አንዱን ነገድ ለአንዱ አካባቢ እንደ መጤ አድርጋችሁ የምታቀርቡ እንደ ኢዜማ/ግንቦት ሰባት/ አይነት ምስለኔዎች የኢትዮጵያን የአንድነት ፖለቲካ ለቃችሁ ዘወር በሉ::እናንት ከነገድ ፖለቲካ አራማጆች የባሳችሁ የምስለኔ ፖለቲካ እና የተጠቂነት ፖለቲካ የምታራምዱ ናችሁ::እናንተ ግባችሁ ስልጣን ብቻ ነዉ::የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ህዝብ:ጥንታዊ ህዝብ እና የእግዚአብሄር ህዝብ መሆኑን የካዳችሁ እና የጎሳ ፖለቲካ አራማጅ ሀይሎች ላይ ሄዳችሁ በመለጠፍ የስልጣን ፍርፋሪ የምትለቃቅሙ ናችሁ::እናም የናንተ አይነቱ የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ህዝብ:ጥንታዊ ህዝብ እና የእግዚአብሄር ህዝብ መሆኑን የካደ የአንድነት ፖለቲካ ሀይልም በቆራጣ ሀሳብ ላይ የቆመ ነዉ::ከመርገምታዊነትም የከፋ መርገምት እንደ እናንተ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት እየማሉ በተግባር ግን በካንሰራማዉ የጎሳ ፖለቲካ አስተሳሰብ መመራት ነዉ::
–በቆራጣ ሀሳብ ታንቆ የመቀመጥ ዳተኝነትም አብዛኛዉን ህዝቡ ወሮ እና ጠፍሮ ይዞታል::የእሱ ነገድ ያሸነፈ ሲመስለዉ እዉነትን:ፍትህን:እኩልነትን:የህግ የበላይነት እና ወንድማማችነትን በእግሩ እረግጦ በመርገምት ከተመቱት የጎሳ ድርጅቶቹ ጋር ተሰልፎ ለጥቅማጥቅም እስክስታ የመምታት መርገምት ይዞታል::ይሄም የአብዛኛዉ ህዝብ ዳተኝነት እና ካንሰራማዉን የጎሳ ፖለቲካ ያለመጠዬፍ ባህሪ ለሰላሳ አመታት ቅድስት ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሄር ዘርግታ መዳን እንዳታገኝ ትልቅ መሰናክል ሆኗል::እናም ከየነገዱ የተዉጣጣህ ህዝብ ሆይ እራሳህን መርምር::አለዚያ ግን በመርገምት ሀሳብ እና በቆራጣ ሀሳብ ባንተ ስም ተሰባስበዉ አሸነፍን የሚሉ የነገድህ ፖለቲከኞች የመርገምት ዘመንን ዉስጥ የምትመላለስ እና አገር አልባ አድርገዉህ የምትኖር ብቻ ሳይሆን የእርስ በርስ መጠፋፋትህን እርግጠኛ ሂደትም በደንብ እያሳመርከዉ መሆንህን እወቅ::ምርጫዉ ያንተ ነዉ::
–ለማንኛዉም እያንዳንድህ ኢትዮጵያን ሀገርህን በምልዓት ሳታድን ማንኛህም አትድንም::አስተሳሰብህን በቆራጣ ሀሳብ ሸብበህ ይዘህ :ስለኢትዮጵያ አያገባኝም ብለህ :ሀገራዊ ራዕይህን ገለህ ያፈለገ ያህል አክራሪ ሆነህ ድል ብታገኝ እንኳን ድልህ በቆራጣዉ ሀሳብህ የተቆረጠ:ዘላቂነት የሌለዉ እና ሰንካላ ነዉ::ድል የምትለዉም ላንተም ለመላዉ ኢትዮጵያዊም መርገምት ነዉ::
–ቅድስት ኢትዮጵያ ስትድን ብቻ ሁሉህም ትድናለህ::አለዚያ ከቆራጣ ሀሳብህ ጋር ሁሉህም ጠፊ ነህ::ወንድማማች ሆነህ ወይም የሰፈረ ልጅ ሆነህ ተደራጅተህ ብትነሳ እኳን ወይም የአንድ ወረዳ ሰዎች እንኳን ተደራጅታችሁ ብትነሱ ራዕያችሁን ከመነሻዉ ኢትዮጵያን ለማዳን አድርጉት::ያን ጊዜ የድርጊት መርሃ ግባችሁም በምልዓት የተሞላ በመሆን ቅድስት ኢትዮጵያን ወደማዳን ይመራችኋል::ቅድስት ኢትዮጵያ ስትድን ሁሉህም ትድናለህ::
ኢትዮጵያን እግዚአብሄር ይባርካት !
Filed in: Amharic