>

ህዝብ እና ታሪክ ኢ-መደበኛ አይባልም! (ታደለ ጥበቡ)

ህዝብ እና ታሪክ ኢ-መደበኛ አይባልም!

ታደለ ጥበቡ


ፋኖነት በሀገር ሕልውና ላይ የተቃጣን አደጋ ለመመከት ሲታገል የኖረ፤ እየታገለም ያለ፤  የፋሽስት ጣሊያን አገዛዝን በመቃወም ለነጻነት፣ ለእኩልነት እና ለፍትሕ የተዋደቀ፤ እየተዋደቀም ያለ እንጂ ኢ-መደበኛ አደረጃጀት አይደለም።

“ፋኖ” ከ1928 ዓ.ም የጣሊያን ወረራ በኋላ ሀገርን ነፃ ያወጣ የአርበኞች መጠሪያ፣ ከእኔ በላይ ለሀገር፣ ለህዝብና ለሰንደቅ ዓላማ ብሎ ያለፈ ትውልድ ስም መጠሪያ እንጂ ኢ-መደበኛ አደረጃጀት አይደለም።

“ፋኖነት” አርበኝነት፤ ፋኖነት ለሃገር ክብር ዘብ መቆም፣ ፋኖነት ከራስ በላይ ለሚልቅ የሕዝብ ጥቅምና ፍቅር ሕይወትን አሳልፎ መስጠት እንጂ ኢ-መደበኛ አደረጃጀት አይደለም።

ጀግንነትን፣ አሸናፊነትን፣ ኢትዮጵያዊነትን፣ አንድነትን፣ ፅናትን፣ አልሞ ተኳሽነትን፣አይበገሬነትን፣ ለነፃነት መሞትን፣ በነፃነት መኖርን፣ የወረስነው ከፋኖ ሆኖ ሳለ ይሄን ማኅበራዊ ውርስና  ትውልድ ዘለል እሴት “ኢ-መደበኛ” ብሎ መፈረጅ  ታሪክን ጥላሸት መቀባት ነው።

ዛሬ ‘ፋኖ’ ቢደራጅ  ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ለሰውነት፣ ለክብርና ለነፃነት ነው የተዋደቀው። ወያኔ የተደራጀው “ከባላባታዊ ሥርዓትና ከኢምፐርያሊዝም ነፃ የሆነች የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ሪፓብሊክ” ለማቋቋም ሲሆን፣ ኦነግ በወለጋ ጫካ የሸፈተው ኦሮሞን ከኢትዮጵያ ነጻ ሊያወጣ፣ ሊገነጥልና የኦሮሚያ ሪፐብሊክ መንግሥት ለመመስረት ነው።

ፋኖ’ ደግሞ እንደሌሎቹ ዐማራን ከኢትዮጵያ ለመነጠልና ለመገንጠል ዓላማ ይዞ ተደራጅቶ አያውቅም። እንዲህ ያለ የስነልቦና ውቅር የለውም።

“ፋኖ” በኦሕዴድ ድጋፍ እንደሚያገኘው ኦነግ ሸኔ፣ ባንክ አልዘረፈም፣ ሴት ተማሪ አላገተም፣ የመንግሥት አመራር አልገደለም፣ መንገድ አልዘጋም፣ ህዝብ አላፈናቀለም፣ ህዝብ አልዘረፈም፣ ንፁሐንን አልገደለም፣ በጉልበት የወሰደው ቀበሌ ሆነ ወረዳ የለም፣ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችን አልገደለም፣ መኪና አላቃጠለም፣ ድርጅት አላወደመም፣ የውጭ ዜጎችን አላገተም፣ ሀገሪቱ በሕወሓት ስትወረር እንደ ኦነግ ሸኔ ርዳ ተራዳ  በሚል በጎን አገሩን አልወጋም።

ይልቁንስ፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅ በሕወሓት ተደፈረ፣ ቀዬውን አረከሰው የሚል የክተት አዋጅ ሲታወጅ፣ ፋኖ  እንደ ነብር ተቆጥቶ፣ እንደ አንበሳ እያገሳ ነበር የተነሳው። የአባቱን ነፍጥ አንስቶ፣  በደም የተቀበላትን አርንጓዴ ቢጫ ቀይ ሠንደቅ ከፊት አስቀድሞ፣ ለሀገር አንድነት በዱር በገደሉ ተዋደቀ፣ ደሙን አፈሰሰ፣ አጥንቱን ከሰከሰ። ጠላቱን እንደ አገዳ እየቆረጠ ጣለው፣  እንደ ቅጠል እያረገፈ ወደመጣበት ሸኘው።  ይሄን ሁሉ  መሰዋእትነት ዘንግቶ የተሰው ፋኖዎች አፅም እንኳን ገና ሳይበሰብስ “ኢ-መደበኛ” አደረጃጀት ብሎ መፈረጅ  ውለታ-ቢስነት ነው።

እንደኔ እይታ የዐማራ ሕዝብ ውርስና ቅርስ የሆነውን “ፋኖ” በኢ-መደበኛ አደረጃጀት የተፈረጀበት ምክንያት፣

1. አሁንም  ከኦህዴድ ብልፅግና ሆን ተብለው በሚቀረፁ አጀንዳዎች፣ የዐማራን ሕዝብ ኅብረተሰባዊ እረፍት በመነሳት ከአገራዊና ቀጠናዊ ፖለቲካ ለመነጠል፣

2. የዐማራ ህዝብ በመንፈስና በዓላማ አንድ እንዳይሆን፣ እንደ ብል ውስጥ ውስጡን ቦርቡረው ሲያበቃ  በጎጥ አቧድኖ ድንጋይ ለማወራወር፣

3. ኦሕዴድ እንኳን ከኦነግ  ሆነ ከሌሎች ፅንፈኛ ኃይሎች ጋር በገዳ ሥርዓት ችግሩን እየቀረፈ፣ በወንጀል ተጨማልቀው የታሰሩ ሰዎችን በመፍታት ውስጣዊ አንድነቱን እያጠናከረ ባለበት በዚህ ወቅት፣ በዐማራ በኩል ደግሞ ከሽምግልና በፊት የጦርነት ነጋሪት የተጎሰመው በክልሉ  በጎራ የተከፋፈለ የኃይል አሰላለፍ እንዲኖር ስለሚፈልግና ያነን ተከትሎ በሚፈጠር ግርግር ዐማራን ያለ መሪ ለማስቀረት ነው።

አሁንም የምለው ከጋራ ህልውናችን የሚበልጥ ምንም ነገር ስለሌለ  በነ’ዘመነ ካሴ  የሚመራው የዐማራ ሕዝባዊ ሠራዊት ከዐማራ የክልል አመራሮች ጋር በልዩነት ነጥቦች ላይ ቁጭ ብለው በዝግ መምከር ይኖርባቸዋል። እንኳን እንዲህ ያለ ቀላል ጉዳይ ቀርቶ ሕወሓት እንኳን  ድሮ በአሸባሪነት ከፈረጀው “ኦነግ” ጋር ሳይቀር ወዳጅነት ፈጥሮ እንደተነሳብን ማስታወስ ያስፈልጋል።

ስለዚህ አሁን ሁላችንም ጠብ አጫሪነትን እናርግብ፣ ነገሮች በውይይትና በመነጋገር እንዲፈቱ እናበረታታ፣ ወንድማማቾችን እናቀራርብ። በለው፣ ቁረጠው፣ ፍለጠው፣ ዋ ትነካውና እንተያያለን በማለት የሚፈታ ችግር እንደለለ ይታወቅ። ምክንያቱም  እየተቀጣጠለ ባለ እሳት ነዳጅ መጨመር እሳቱን ያበረተዋል እንጂ አያጠፋውም፣

በተለይ  በማህበራዊ ሁኔታ፣ በእድሜ፣ በኢኮኖሚ፣ በባህል፣ በዕውቀት፣ በሀቀኝነት፣ የሚታወቁና በተሻለ ሁኔታ ከበሬታ ያላቸው ሽማግሌዎች ተመርጠው ችግሩን እንዲፈቱ ሥራ እንሰራ!

Filed in: Amharic